ጥር 10 ፣ 2013

የጥምቀት በአል በኢትዮጵያ | ከጃንሜዳ እስከ ፋሲል ጥምቀተ ባህር

Ethiopia

የጥምቀት በዕል በአራት ከተሞች አከባበሩ ይህን ይመስላል

Avatar: Workineh Diribsa
Workineh Diribsa

I am Workineh, lecturer and researcher at Jimma University; journalist/correspondent for Addis Zeybe media.

ሰላም ፍሰሃ

Selam Fisseha is a graduate of Addis Ababa University Law School and a Mobile Journalist from Addis Ababa at Addis Zeybe.

ተስፋ በላይነህ

Tesfa Belayneh is a mobile journalist from the city of Gondar, working at Addis Zeybe

የጥምቀት በአል በኢትዮጵያ | ከጃንሜዳ እስከ ፋሲል ጥምቀተ ባህር

የጥምቀት በአል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተማዎች እንዷ የሆነችው አዲስ አበባ የዘንድሮውን በዓል ለማክበር ከወራት በፊት ጎንበስ ቀና ስትል ቆይታለች። በዓሉ ለከተማው ነዋሪዎች ከአንድ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነት አልፎ የአብሮነት መገለጫ ነው። በመሆኑም በዓሉን በጉጉት የሚጠብቁት የሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ሃገር ዜጎችም ናቸው። ለምሳሌ በ2010 ዓም የተለያዩ የውጭ ዜጎች ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመተባበር  ለታቦቱ ምንጣፍ በማንጠፍ እና በመጥረግ ሲያግዙ እና የበዓሉ አካል ሆነው አሳልፈው ነበር። ይህ ቀን እንኳን ኢትዮጵያዊያንን የዓለም ህዝብን አንድ የማድረጊያ ቀን ነው።  ለዚህም ነው በዓሉ የአብሮነት መገለጫ ጭምር ነው የሚባለው።

የጥምቀት በዓል ለሁለት ቀናት በድምቀት የሚከበር ሲሆን ጥር 10 የከተራ በዓል በመባል ይታወቃል። ለመሆኑ ከተራ ምንድነው?

እንደ ሀይማኖት አባቶች ከሆነ ከተራ ማለት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚፈሰውን ወንዞች አንድ ቦታ ላይ መገደብ ማለት ነው። የከተራ እለት ታቦታት ከየደብራቸው በምዕመናን እና በወጣት መዘምራኖች ታጅበው በዮርዳኖስ ባህረ ጥምቀት ወደ ተመሰለው ታቦተ ባህር ያቀናሉ። ታዲያ ሁሉም ደብር የራሱን ታቦት ሲሸኝ የተለየ ትርዒት በማዘጋጀት እና በማሳየት የታቦት ሽኝቱ በይበልጥ እንዲደምቅ ይደረጋል። መንገዱ በጠቅላላ በአረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት አሸብርቆ የታቦታቱን ሽኝት ልዩ ያደርገዋል ። የመዘምራኑ መንፈሳዊ  ሆኗል።

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” ይሉ ዘንድ ወጣት ሴቶች የሃበሻ ቀሚሳቸውን ለብሰው እና አጊጠው በአሉን ለማክበር በጃን ሜዳ በጠዋት ይገኛሉ። በተጨማሪም ወጣቶች በሚኖሩበት ሰፈር ስም አንድ አይነት ቲሸርት በማሰራት የአንድነት እና የፍቅር በአል መሆኑን በማሳየት በአሉን አብረው ያሳልፋሉ። ሁሉም ወጣት የሚናፍቀው ቀን እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ለታቦቱ የሚደረገውን የምንጣፍ በማንጠፍ እና በመጥረግ የሚደረገው ትብብር፣ የሃርሞኒካው ጭፈራ እና የሎሚ ዉርወራው አልፎም ደግሞ መተጫጨቱ ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የማህበረሰቡ አንድ ተጨማሪ ትውፊት ሆኗል። ደብሮች በየተራ የማዘጋጀት እድል ስለሚያገኙ ዝግጅቶቻቸውን ከሌሎች ደብሮች የበለጠ ለማድረግ የፈጠራ ፋክክር ይታይባቸዋል። በአሳለፍነው አመት ተረኛ የሆነው ደብር የተለያዩ ትዕይንቶች በማሳየት በአሉን ለየት ለማድረግ ሞኩሮ ነበር። የዘንድሮ ተረኛ አዘጋጅ ደብር የሆነው የፒያሳው አራዳ ጊዮርጊስ ልዩ ትዕይንቶችን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

የኮሮና ወረሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ፒያሳ ይገኝ የነበረው የአትክልት ተራ መገበያያ ስፍራ ወደ ጃን ሜዳ በመዘዋወሩ ስፍራው በጣም ቆሽሾ ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ቀናት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር እና ቦታውን በማፅዳት ወደ ቀድሞው ይዞታው ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል። የዘንድሮውን የጥምቀት በአል የማዘጋጀት ሃላፊነት የተጣለበት የፒያሳው አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የጥምቀት በአል አከባበር ኮሚቴ አስተባባሪ የሆነው ተስፋዬ ገለታ “ቦታው በሚገባ ፀድቶ ወደ ቀድሞው ይዞታው መመለስ ብቻ ሳይሆን በበለጠ በመፀዳቱ በዓሉን በጃን ሜዳ ለማክበር ዝግጁ ነን። እንደሚታወቀው ቀኑ ህዝብ የሚበዛበት ቀን በመሆኑ ድንገተኛ አደጋዎች እንኳን ቢከሰቱ የቀይ መስቀል አባላት ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ” ይላል።

ዳግም ተስፋዬ ይባላል ተወልዶ ያደገው እዛው ጃን ሜዳ አካባቢ ነው “ጃን ሜዳን ለማፅዳት ወጣቶች ተረባርበው ሳይ በጣም ደስ አለኝ ምክንያቱም ያኔ አትክልት ተራ ሆኖ ሳየው በጣም ከመቆሸሹ የተነሳ መቼም የሚፀዳ አይመስልም ነበር። አሁን ግን ፀድቶ ሳየው እና በዓልን ዘንድሮም ጃን ሜዳ ማክበር እንደምችል ሳስበው በጣም ደስ አለኝ” ይላል።

ሂሩት በቀለ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ እና በበዓሉ ላይ ከሚሳተፉት መዘምራን አንዷ ስትሆን የዘንድሮውን በአል አከባበር ለየት የሚያደርገው የኮረና ቫይረስ ወረሽኝ በመከሰቱ ነው ትላለች። “ኮረና ቫይረስ በመከሰቱ የተለየ ያደርገዋል። ለዚህም ተብሎ የከተራው እለት ታቦታት ከየአቅጣጫው ስለሚመጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከታቦቱ ፊት እና ኋላ በመሆን ህዝቡ እንዳይገፋፋ እና እርቀቱን እንዲጠብቅ ለማስተናበር ተዘጋጅተዋል፣ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ በራሪ ወረቀቶች ተዘጋጅተው ተበትነዋል ከጸጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር በአሉ በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ ዝግጅት ተጠናቋል” ስትል ትናገራለች። 

የኮሚቴው አስተባባሪ ተስፋዬ  በበኩሉ “በአሉ በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ ሁሉንም ዝግጅት መደረጉን ገልጾ ወደ 250 የሚሆኑ የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር የበአሉ እለት ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ለማስተናበር ተዘጋጅተው በአሉን እየተጠባበቁ ይገኛሉ” ብሏል።

በመጨረሻም የአብሮነት መገለጫ እና የቱሪስት መስህብ የሆነው ይህ በአል በአርሜንያውያን ኦርቶዶክሶች እና በግብፅ ኦርቶዶክሶችም ጭምር በኢትዮጵያ ለማክበር ይገኛሉ በማለት ሰላም ፍሰሃ ሪፖርት አድርጋለች። 

ሌላኛዋ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆና በተለያዩ ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል ጅማ አንዷ ናት።

ከበዓሉ ቀናት ቀደም ብሎ፣ ከተማን በተለይም የታቦት ማደሪያውን እና የፀበል መርጨት ስነ-ስርዓት የሚካሄድበትን ስፍራ የማጽዳቱ ስራ የአከባቢው ወጣቶች የየአመት ልማድ ነው።

የታቦታቱ ማደሪያው በደብረ በረከት ቅ/ዑራኤል ቤ/ክርስቲያን ሲሆን በከተራ ዕለት ማለትም በጥር 10፣ 17 ያህል ታቦታት ዲፖ በሚባለው አከባቢ ከተገናኙ በኋላ ወደ ስፍራው ይከትማሉ፡፡ በአከባቢው ማህበረሰብም ሽኝት ይደረጋል።

ጅማ የብዙ ብሔረሰብና ሀይማኖቶች መኖሪያ እንደመሆኗ፣ የታቦት ሽኝቱም ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ በተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ይከናወናል። በበዓሉ ዕለትም ቢሆን፣ በከተማው የሚገኙ ብሔረሰቦች የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜ እና ጨዋታዎችን ሲጫወቱ ላስተዋለ ጥምቀት ከሀይማኖት በላይ የሀገረ ባህልም ነው ያስብላል።

ከእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ እነዚህን ባህላዊ ትዕይንቶች ለመመልከት የሚመጡ ማህበረሰቦችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። በዓሉ የተነፋፈቁ የሚገናኙበት፣ ያላገቡም አቻቸውን የሚፈልጉበት መልካም አጋጣሚም ነው። በመሆኑም የጥምቀት በዓል በጅማ ከሃይማኖታዊ ክብረቱ ባሻገር፣ ያለው ማህበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ ነው ይለናል የጅማው ሪፖርተራችን ወርቅነህ ድሪብሳ። 

ልክ እንደ ሁል ግዜው ሁሉ በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በዓመት አንዴ በጉጉት የሚጠበቀው ጥምቀትን ለማክበር ሃዋሳ ከተማም አሸብርቃ ሽር ጉዱ ጨምሯል፡፡

 ታቦተ ህጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ የየአጥቢያው ምዕመን ተሰባስቦ፤ በተለምዶ ስሙ ጥምቀተ ባህር በአሁኑ መድሀኒአለም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ክብረ በዓሉ ይጀምራል።

ወጣቶች ከተማዋን የማፅዳት እና ከየአጥቢያው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ታቦተ ህጉ የሚያልፍባቸውን መንገዶች በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት አሸብርቀውታል።

በከተማ አስተዳደሩ የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ የሆነው አቶ መኩሪያ መኒሳ ጥምቀተ በአሉን ለማክበር ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው "በክፍለ ከተማ ከሚገኙ ከተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ጋር በመሆን የስጋት ቀጠናዎችን የመለየት እንዲሁም የስምሪት ስራዎችን በመስጠት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው" ብሏል በማለት ሙሉነህ ካሣ ከአዋሳ ሪፖርት አድርጓል።

በመቀጠል ታላቁን በዓል ለማሰናዳት ሽርጉድ እያለች ወዳለችው ወደ ጎንደር ከተማ አዲስ ዘይቤ አቅንታለች። በዘንድሮ የጥምቀት በዓል እንደወትሮው የውጭ እንግዶችን ብዙም እንደማይጠበቁ ነገር ግን የኤርትራ ልኡካን በእንግድነት እንደሚጠበቁ የጎንደር ከተማ ባሕልና ቱሪዝም እሴት ኢንደስትሪ ቡድን መሪ አቶ ልዕልና ገብረመስቀል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል:: 

የቡድን መሪው አያይዞ ከአገር ውስጥ በርካታ እንግዶች የሚጠበቁ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክኒያት መጠናቸው እንደሚቀንስ ተናግሯል:: ነገር ግን ከራያና ከወልቃይት ጠገዴ የሚጠበቀው ሰው ከእስካሁኑ ክብረበአላት በተለየ መልኩ መሆኑን ጠቅሷል:: 

"የቱሪስቱ መቀዛቀዝ በፊት ከነበረው ፍሰት አንፃር ሲታይ ከ60 እስከ 70 በመቶ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ይጎዳዋል" ይላል አቶ ልዕልና 

ለጥምቀት በዓል አከባበር ከተማ አስተዳደሩ፣ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምርያው ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን እና የተለያዩ አውደ ርእዮች የሚደረጉ መሆናቸውን ገልፅዋል።

"በዓሉን ለመታደም በርካት እንግዶች እየመጡ ነው:: ከመደበኛ በረራዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሌሎች የበረራ ሰአታትን ስለጨመረ በርካታ እንግዶች እየጎርፉ ነው" አቶ ልዕልና ይቀጥላል።

"ከጥር ሶስት 2013 ጀምሮ የንግድ ትርኢትና ባዛር፣ የግጥም በመሰንቆ መርሃ ግብር፣ የአደባባይ ሩጫ እና የባሕል አውደ ርዕይ እይተካሄደ ነው:: የከተማው እና የአካባቢው ኗሪም አደባባዮችን በማፅዳት በቡድን እየሆነ ባሕላዊ አልባሳትን እና ጭፈራዎችን እያሳዬ ለከተማዋ ድምቀት እየሆነ ነው" ብሏል።

ባለፈው አመት ጥር 2012 ዓ.ም የጥምቀት በዓል በጎንደር በደማቅ አከባበር ቢያልፍም በዕለቱ አሳዛኝ ክስተትንም አሳልፏል። ከጥምቀተ ባሕሩ ዙርያ ለመሸጋገርያነት በጊዜያዊነት የተሰራው የእንጨት ክምር መደርመሱና ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል። እስከ ሁለት ሺህ ሰው ለማስተናገድ ታቅዶ የተሰራው መወጣጫ ዘንድሮ እንደማይኖር እና በብረት የሚሰራ የእንግዶች መቀመጫ እንዲሁም እስከ ሁለት መቶ ሰው የሚይዝ መወጣጫ ብቻ እየተሰራ መሆኑን የአብያተ መንግስታት እና ቅርስ ጥበቃ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ስዩም ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል:: 

ዘንድሮ የፀበል መርጫ መሳርያ መገንባቱ ለየት የሚያደርገው ሲሆን አዲስ ዘይቤ የመወጣጫውን ጉዳይ አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገበት ቦታው ድረስ በመሄድ ለመምልከት ሙከራ አድርጋለች::  

የመወጣጫው ስራም መጠናቀቁን እና ለእንግዶች ዝግጁ መሆኑን ለማዬት ተችሏል በማለት ተስፋ በላይነህ ከጎንደር ገልጿል።

  

አስተያየት