ማንም ሰው የግል ቤቱን ምቾት፣ ጽዳት እና ውበት ይጠብቃል። ነገር ግን የቤቱን ምቾትና ውበት ጠብቆ መልሰን አካባቢያችንን እንበክላለን፤ ተፈጥሮ እናናጋለን፡፡ ይህንን የምናደርገው በአካባቢያችን ላይ ጉዳት በማድረስ ወይም ጥፋት በመፈጸም ሊሆን ይችላል። በግል ቤታችን እና አካባቢያችን መካከል ያለውን መስተጋብራዊ ግንኙነት በወጉ ያልተረዳን እስኪመስል ድረስ በአካባቢያችን ላይ ጉዳት እናደርሳለን፡፡ በቤታችን ውስጥ ሆነን የምንተነፍሰው አየር፣ የምንጠቀመው ውኃ እና ሌሎች ነገሮች ከቤት ውጭ ካለው አካባቢ የሚመጡ መሆናቸውን ያልተረዳን ይመስል ለግል ቤታችን የምናደርገውን እንክብካቤ በዙሪያችን ላለው አካባቢ እንነፍጋለን። ከመንፈግም በላይ ለግል ጉዳያችን ስንል አካባቢያችን እንጎዳለን። በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረስን በዚሁ ምክንያት ለሚደርስብን ቀውስ ፈጣሪን ወይም ሌላን አካል ስናማርርም እንሰማለን።
በጅግጅጋ ከተማ ይሄ ችግር በጣም እየተስፋፋ መቷል። በከተማው ከዋናዉ አስፋልት መንገድ ጀምሮ ስርዓቱን ያልጠበቀ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር አለ፣ ደረቅ ቆሻሻ ለፍሳሽ ከተዘጋጀ ቱቦ ጋር አገናኝቶ በመልቀቅ አካባቢን መበከል በየሰፈሩና አስፋልት ዳር የሚታይ ነዉ። በተለይ የዝናብ ወቅት አስፋልት ዳር ያሉ የዉሃ ማሰወገጃ ቱቦዎች በቆሻሻ ከመሙላታቸውና ከመደፈናቸው የተነሳ ዉሃ መንገዱን የሚዘጋበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።
አቶ ሀሰን አብዱላሂ የጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 12 ነዋሪ ነው ስለጉዳዩ አዲስ ዘይቤ አንስታ ስትጠይቀው የተሰማውን እንደዚህ በማለት በቁጭት ይናገራል። "በእርግጥ ችግሩ በእርግማን ወይም በፈጣሪ ቁጣ የመጣ ሳይሆን ባላዋቂነታችን ወይም አልጠግብ ባይነታችን እንዲሁም በቸልተኝነት በእኛው በራሳችን በአካባቢያችን ላይ በምንፈፅመው ጥፋት የምንቀበለው ቅጣት ሊሆን ይችላል” ብሏል። “ላለፉት ሰባት አመታት ለክልሉ መዘጋጃ አመልክተናል ሁሌም አንደ አይነት መልስ ነው ሲሰጠን የነበረው እሱም ፈጣሪ ካለ ይሰራላችኋል፣ የቆሻሻ ማሰወገጃ መኪናዎች ይመጣሉ በማለት ሲያታልሉን ቆይተዋል።”
አቶ ያሲን ባሽር የ 10 ቀበሌ ነዋሪ ነው። እሱም ከሃሰን ሃሳብ ጋር ይስማማል። "ከግለሰቦች፣ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከፋብሪካዎች እና ከተለያዩ ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎችን አየተበከለን ነዉ ያለነው የቤታችንን ውበት የጠበቅን መስሎን በተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚያመጡ ቆሻሻዎችን በሚያሳዝን መንገድ በየአቅጣጫው ተጥለው መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፤ በከተሞች አካባቢ ደግሞ ችግሩ የጎላ ነው" ይላል።
“የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በጣም የከፋ ሆኖ ከተመለከትኩባቸው አካባዎች መካከል የጅግጅጋ ከተማ አንዱ ነው። የአስፋልት መንገድ ዳርቻዎች በአረንጓዴ ልማት ተውበው ለመዝናኛነት አገልግሎት መዋል ሲገባቸው የቆሻሻ መጣያ ሆነዋል” ትላለች ማንያዩሻል አምባቸው። “የግለሰብ የመኖሪያ ቤቶች እና ለልማት የታጠሩ አጥሮች፣ የአስፓልት ዳርቻዎች፣ የውኃ መፋሰሻ ቦዮች ለቆሻሻ መጣያ አገልግሎት ተብለው የተሠሩ እስኪመስል ድረስ የቆሻሻ ክምር ተከማችቶባቸዋል። በየቤቱ የተጸዳውን ቆሻሻ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ በየአስፓልቱ እና በውኃ መፋሰሻ ቱቦዎች ከሚጥለው ባለፈ ከተለያዩ ድርጅቶች የተሰበሰበ የቆሻሻ ክምችት በጭነት መኪና በከተማው አቅራቢያ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ በተደራጀ መንገድ በምሽት ይወገዳል።”
አዲስ ዘይቤ ስለጉዳዩ መስማት ቀጥላለች ካነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አሚና ሁሴን አንዷ ናት፤ ወይዘሮ አሚና በከብቶቻቸው መዋያ፣ በእርሻ ቦታቸው እና በከተማው መግቢያና ውጭ አስፓልት ላይ የተደራጁ ግለሰቦች በጭነት መኪና ምሽት ላይ ቆሻሻ እንደሚደፉ ለአዲሰ ዘይቤ ትናገራለች። “በአካባቢው የተጣሉ ፕላስቲኮችን የበሉ ሁለት በሬዎች ማተዋል። በይዞታ ቦታችን ላይ የሚጣለውን ቆሻሻ ለመከላከል በአካባቢው ክትትል ሲያደርግ የነበረ ልጄ በቆሻሻው መጥፎ ሽታ የተነሳ በመተንፈሻ አካሉ ላይ ጉዳት ደርሶበት ከዓመት በላይ በሕክምና ላይ ይገኛል”፡፡ አካባቢው የአቅመ ደካሞች መኖሪያና ይዞታ በመሆኑ ቆሻሻ እንዳይደፋ መከላከል እንዳልቻሉም አሚና ነግራናለች።
መንግሥት የከተማዋን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በማስያዝ የማኅበረሰቡን ጤንነት እና የአካባቢን ብክለት የመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ነዋሪዎቹ ይጠይቃሉ። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 92 (1) ‹‹መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት›› በማለት ይደነግጋል በእርግጥ ይህ ማለት ዜጎች እያቆሸሹ መንግሥት ያጽዳ ማለት ሳይሆን ሥርዓት ማስያዝ የመንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
የሶማሊ ክልል ከተማ አስተዳደር ቤቶች እና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አረንጓዴ ልማት ጽዳት እና ውበት አፈፃፀም ቡድን መሪ አቶ መሀመድ አሊ አብዲ የከተማው የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በችግር የተከበበ እንደሆነ ይገልፃል። “በመንግሥት የተከለለው የቆሻሻ መድፊያ ቦታ ከሰው እና እንስሳት ንክኪ በፀዳ መልኩ ታጥሮ አገልግሎት እንዲሰጥ አለመደረጉ የመጀመሪው ችግር ነው። ከተዘጋጀው ቦታ ውጭ ቆሻሻ የሚደፉ ሕገ ወጦች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም በምሽት ስለሚደፋ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ደግሞ ሌላው ችግር ነው” ብሏል።
የከተማ አሰተዳደር ምክትል ሀላፍ ሻፊ አብዲ በበኩሉ በከተማው 60 የደረቅ ቆሻሻ የጎዳና ጽዳት ሠራተኞች እና 42 አባላት ያሏቸው አራት ማኅበራት ቢኖሩም የጽዳት ሥራውን ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት አባል የሆኑበት የንቅናቄ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ሥራ መጀመሩን በመግለፅ በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ የጅግጅጋ ከተማ ፋፋን ዞን 12 ቀበሌ ወጣቶችን በማደራጀት አካባቢያቸዉን እንዲጠብቁ መደረጉን ገልፅዋል። “በከተማዉ የደረቅም ይሁን እርጥብ ቆሻሻ ማሰወገጃ ቦታ አለመኖሩ ሽታው አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ ለበሽታ እንዳይዳረግ በአጭር ጊዜ ባይፈታም እንደተቋም ችግሩን ለመፍታትና ቦታ ለመቀየር እተነጋገርን ነው” ያለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም አላግባብ ወደ መስመር የወጡ ቆሻሻዎችን የመጥረግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልፅዋል፡፡
አቶ ሻፊ አያይዞም በከተማው ያሉ የቆዳ ነጋዴዎች አገልግሎት የማይሰጡ ቆዳዎችን ጉድጓድ ቆፍረው መቅበር ሲገባቸው በዚሁ ቦታ እያመጡ በመጣላቸው ከፍተኛ የሆነ ማንንም የማያስቀርብ ሽታ መፈጠሩን ጠቁመዋል። “እነዚህን ሰዎች በቀጣይ መመሪያን በመከተል አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስድባሽኋለን። በቅርቡም ለቆሻሻ መጣያ ቦታ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል” ሲል ለአዲሰ ዘይቤ ተናግሯል።