በጅማ ከተማ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ባጃጆች እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለው እገዳ ብዙዎችን እያጉላላ ይገኛል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ትጃኒ ናስር አልፎ አልፎ የከተማይቷን ሰላምና ፀጥታ ለማድፈረስ የሚደረጉ ሙከራዎች እንደነበሩ ከሶስት ወራት በፊት ለአዲስ ዘይቤ መግለፁ ይታወሳል፡፡
ከአራት ወራት በፊት ማንነቱ በዉል ያልታወቀ ግለሰብ በባጃጅ ውስጥ ሆኖ በቾቦሬ ቀበሌ አከባቢ በከተማዋ ሚሊሻዎች ላይ በወረወረው የእጅ ቦምብ የአንድ ሚሊሻ ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡ ከክስተቱ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ በጅማ ዞን ማረሚያ ቤት ላይም ሌላ የእጅ ቦምብ ማንነቱ ባልታወቀ ግላሰብ ተወርውሮ እንደ ነበር የሚታወስ ነው፡፡
ይህንን የሰላም መድፍረስ ተከትሎ የከተማዋ ፀጥታ፣ ፖሊስ፣ ትራንስፖርትና የባጃጅ ማህበራት በመስማማት ነው የሰዓት እላፊ እገዳው የተጣለው ።
በመሆኑም የትራንስፖርት እጥረት በመፈጠሩ የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለከተማ መስተዳደሩ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር አዲስ ዘይቤ አጣርታለች፡፡
ባጃጅ ለከተማዋ ከፍተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በተጣለው እገዳ መማረራቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሰኚ ዱጋሳ “የተወሰኑ ባጃጆች እንዲሰሩ ከተፈቀዳ በኋላ ራሱ በከተማዋ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር አለ፡፡ የከተማዋ ታሪፉ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም የሆነው የመናፈሻ-ቆጪ መንገድ ላይ ታክሲዎች አምስት ብር አስከፍለው ይጭናሉ፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ ግዜ እስከ ስድስት ሰዎች ትርፍ ይጭናሉ፡፡ ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ስለሌለ በዚሁ ሁኔታ ትገለገላለህ፡፡” ሲል እያጋጠመው ያለውን ችግር ለአዲስ ዘይቤ አሰረድቷል።
“በጅማ ከተማ እንደሚታወቀው ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ታክሲዎች ብዙም የመሰራት ልምድ ያለቸውም፡፡ በተቃራኒው ባጃጆች ለከተማዋ ከፍተኛ የመጓጓዣ አገልግሎት በመስጠት ያገለግሉ ነበር፡፡ ላለፉት ሶስት ወራት ከሌሊቱ አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይሰሩ ተከልክሎ ስለነበረ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ነበረ፡፡” ይላል ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ፍሮምሳ ጎዳና
ይሁን እንጂ አሁን በአንዳንድ ቅድመ ሆኔታዎች ውስን ባጃጆች እስከ ከሌሊቱ ሶስት ሰዓት እንዲሰሩ በከተማዋ ፖሊስ መምሪያ፣ ትራንስፖርት ባልስልጣንና የባጃጅ ማህበራት ወስነዋል፡፡
የባጃጅ አሽከርካሪ የሆነው ጥላሁን ገመቹ በበኩሉ “የተደረገው ማሻሻያ የከተማውን ባጃጅ ማህበራት፣ ፖሊስና መምሪያና ትራስፖርት ባለስልጣን አወያይቶ የተደረገ ነው፡፡ ውሳኔውም ባጃጆች ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መስራት የሚችሉት በሶስቱም አካላት ስምምነት በተዘጋጀው ቅጽ ላይ የባጃጅ ባለቤትና ሹፌሩ ከፈረሙ ብቻ ነው፡፡ ቅፁ ስለ ባጃጁ፣ ባለቤቱ፣ ሹፌሩና የተሰማራበት መስመር ሙሉ መረጃ የያዘ ነው፡፡ ከፈረሙ በኋላ የይለፍ ወረቀት ለባጃጅ ሹፌሮች ይሰጣል፡፡ ይህ ወረቀት የሌላቸው ሹፌሮች ግን ከአንድ ሰዓት በኋላ መስራት አይችሉም፡፡ በዚሁ ውሳኔ መሰረት ከህዳር 29፣ 2013 ዓ.ም ጀምረን በየተራችን እየሰራን ቢሆንም መፈረሙን ፈርቶ ወደ ሥራቸው ያልገቡ ሹፌሮችም አሉ” ሲል አቶ ጥላሁን ለአዲስ ዘይቤ አስረድቷል፡፡”
በጅማ ከተማ ስድስት የባጃጅ ማህበራት ያሉ ሲሆን ተራ በተራ ለአንድ ሌሊት ሁለት ማህበራት ብቻ እንዲሰሩ ነው የተፈቀደው፡፡
ወረቀቱን ካልፈረሙት መሀል አንዱ የሆነው እና ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ የባጃጅ ሹፌር “ወረቀቱን ይዘህ እንኳን ራስህን ትጠራጠራለህ፤ የሆነ ችግር ቢከሰት እጠየቃለው ብለ ታስባለህ፡፡ በመሆኑም ነጻ ሆነን እንዳንሰራ የስነልቦና ጫና አሳድሮብናል፡፡አንዳንድ ባጃጆች ህግወጥ ሥራዎች ላይ ስለተሰማሩ ሁሉም ባጃጅ ይጠረጠራል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ተፈጠረ የተበለው ችግር በአንድ ባጃጅ ነው፤ ሥራችንን እንዳንሰራ የተቀጣነው ግን ሁላችንም ነን፡፡ ላለፉት አራት ወራት ከፍተኛ የኦኮኖሚ ጫና ደርሶብናል፡፡ አሁንም ቢሆን በፍራቻ ውስጥ ሆነን ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ እኛ ሥራ ላይ እያለን የሆነ የጽጥታ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂ እንሆናለን የሚል ፍራቻ አለብን።”ይላል
አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን ሰፊ ሽፋን ለመስጥት እና ለማጣራት ለጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ፡ ኢንስፔክተር አንተነህና የከተማው የትራንስፖርት ባለስልጣን ሀላፊ አቶ ረሻድ አባምልኪ ጋር ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች አልተሳኩም፡፡ (ወርቅነህ ድሪብሳ)