በ28 ታህሳስ 2013 ዓ.ም Tigray Defence Force በሚል ስያሜ የተከፈተውና ከ16,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ገጽ በሱዳን ወታደሮች ላይ ወታደራዊ ጥቃት ሲያካሂዱ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሱዳን ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል በሚል በርካታ ወታደሮችን እና ታንኮችን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል። በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ የተፃፈው ጽሑፍ “በሁለት ግንባሮች ጥቃት ከፍቶ የሱዳንን ድንበር አቋርጦ የወጣውን ወራሪውን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የሱዳን ጦር በቁጥጥር ስር አውሏል” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ ከዚህ በታች ያለው ምስል በሱዳን ጦር በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተያዙትን የኢትዮጵያ ወታደሮችን የሚያሳይ ባለመሆኑ እና ልጥፉ ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ በሁለቱ ሃገራት መካከል ግጭቶች መኖሩ እውነት ነው። የሱዳን ጦር በአል ገዳሪፍ፣ በሰላም ቢር እና ማሃጅ አካባቢዎችን ከኢትዮጵያ ጦር እና ከታጠቁ ሚሊሻዎች ማስመለስ መቻላቸውን መግለፁ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም በ28 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የተወሰዱትን በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉ ሁሉንም ግዛቶች መቆጣጠሩን አክለው መግለፃቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራቱ ጉዳዩን ለመፍታት እና ድንበሩ ለማካለል ድርድር እያደረጉ እንደቆዩም የሚታወቅ ነው፡፡
ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው በፌስቡክ ልጥፉ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው 9 ታህሳስ 2013 ዓ.ም በሐዋር ዜና አገልግሎት ሲሆን የሱዳን ጦር በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ያሉትን የአቡ ቶዮር ተራራን ጨምሮ ሁሉንም ግዛቶች ተቆጣጥሯል ከሚል ጽሑፍ ጋር ተያይዞ ነበር በወቅቱ የወጣው። ዋናው ጽሑፍ ግን ስለ ምስሉ ምንም ዓይነት መግለጫ የለውም ወይም በምስሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች እነማን እንደሆኑ አይናገርም።
በድንበር አካባቢዎች በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ የፌስቡክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ በድንበር አካባቢ ባለው ግጭት ወቅት በሱዳን ጦር የተያዙ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደማያሳይ እና ትክክለኛ ያልሆነ ምስል በመጠቀሙ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ
ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው
አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።