አንድ የፌስቡክ ገፅ የካቲት 30 ፤ 2014 ዓ.ም በሰበር ዜና መልክ “ሩስያ በኢትዮጵያ ትልቁን የኒውክለር ማብላያ ልትከፍት ነው” በሚል ፅሁፍ የከባድ ሚሳኤሎች ምስል አጋርቶ ነበር።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ግጭት ተከስቷል። ይህ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በኔቶ እና በሩስያ መካከል የኒውክለር ጦርነት ሊከሰት ይችላል የሚሉ ስጋቶች ባሉበት ሁኔታ ይህ መረጃ ተጋርቷል።
በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ሩስያ በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር አመታት ውስጥ የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከስምምነት ላይ ደርሳለች።
በታህሳስ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኒውክለር ኃይልን ለሰላማዊ አላማ በማዋል ዙርያ ከሩስያ ጋር የተደረገውን ስምምነት አፅድቋል። በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ሩስያ የኒውክለር ኃይልን ለሰላማዊ መንገድ በመጠቀም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ይህ የፌስቡክ ፖስት አሳሳች ከሆነበት ምክንያት አንዱ በፅሁፉ ካቀረበው ኃሳብ ጋር በጣም ትልልቅ እና ዘመናዊ ሚሳኤሎችን የሚያሳይ ምስልን ማያያዙ ነው። አብዛኛው ሰው የኒውክለር ማብላያ መገንባት የሚለውን ሀሳብ እንደ ኒኩሌር መሳሪያ ቢቆጥረውም ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችው ስምምነት ግን የኒውክለር መሳርያ ማምረቻን ለመገንባት ሳይሆን የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ጣብያ ለመገንባት ነው።
በአዲስ አበባ የሩስያ ኤምባሲ ለሀቅቼክ በኢሜል እንደገለፀው የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያን በተለያዩ የኒውክለር ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችላት ገልጸዋል።
ይህ የፌስቡክ ፖስትም ትልልቅ የሚሳኤል ምስሎችን በማያያዝ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ካለው ስምምነት በራቀ መልኩ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ማምረቻ ጣቢያ ሊቋቋም እንደሆነ አስነብቧል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀቅቼክ ምስሉን በማጣራት ምስሉ የተወሰደው በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በChina Central Television (CCTV) ላይ ከተላለፈ ቪድዮ እንደሆነ አረጋግጧል። ቪድዮው በመስከረም 19 ፤ 2012 ዓ.ም የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ከፈረንጆቹ ጥቅምት 1 ፤ 1949 ጀምሮ ስልጣን የያዘበትን 70ኛ አመት ክብረ በዓል በሚያከብርበት ቀን የተደረጉ ወታደራዊ ትርኢቶችን ያሳያል።
በፌስቡክ ፖስቱ ላይ የተመለከቱት ከባድ ሚሳኤሎችም የተወሰዱት ከዚሁ ወታደራዊ ትርኢት ላይ ነው። ሚሳኤሉ DF (Dongfeng) ሲባል ትርጉሙ በመንደሪን ቋንቋ 'ሚሳኤል' ማለት ነው።
ይህ 5B ሞዴል የሆነው የሚሳኤል አይነት እጅግ ውስብስብና አህጉር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳኤል ነው።
የተለያዩ መረጃዎች የሚገኙበት እና Britannica የሚባለው ድረ-ገጽ ይህ ባልስቲክ ሚሳኤል ትልልቅ ፈንጂዎችን በተጨማሪም የኬሚካል ፣ የባዮሎጂካል ወይም የኒኩሌር መሳርያዎችን ሊሸከም እንደሚችል ያስነብባል።
ይህን ቪድዮ ካስተላለፉት የዜና አውታሮች መካከል አንዱ የሆነው CGTN በወታደራዊ ትርኢቱ ላይ የታዩት Dongfeng-5B የተባሉት ባልስቲክ ሚሳኤሎች የኒኩሌር ሚሳኤል እንደሆኑ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የፌስቡክ ፖስቱ ካቀረበው ሩስያ በኢትዮጵያ የኒውክለር ማብላያ ጣቢያ ልትገነባ ነው ከሚለው መረጃ አንፃር፣ የባልስቲክ ሚሳኤሉን የሚያሳየው ምስል የፌስቡክ ፖስቱን አሳሳች የሚያደርገው ሲሆን መረጃውን ለመደገፍ የታዩት ባልስቲክ ሚሳኤሎችም የሩስያ ሳይሆኑ የቻይና እንደሆኑ ተረጋግጧል።
ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ፖስቱን አጣርቶ አሳሳች ብሎታል።