መጋቢት 5 ፣ 2014

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ

ዜና

በዩኒቨርሲቲው ትላንት መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቁጥራቸው በወል ያልታወቁ ተማሪዎች ተጎድተዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ
Camera Icon

credit: Ethio Sports

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ። በዩኒቨርሲቲው ትላንት መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቁጥራቸው በወል ያልታወቁ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በተጨማሪም በግቢው የነበረውን ሁኔታ ለማረጋጋት የገቡ የፀጥታ ኃይሎች በተኮሱት የአስለቃሽ ጭስም የታመሙ ተማሪዎች መኖራቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚማር ተማሪ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀው፣ “ትላንት (መጋቢት 4) ምሽት ከ4 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ቤተ መፅሐፍት ውስጥ ነበርኩ። ረብሻው ሲነሳ ቤተ መፅሐፍቱ ተዘግቶ ለምንም ጉዳይ መውጣጥ ተክልክሎ ዛሬ መጋቢት 5 ከንጋቱ 12 ሰዓት ተኩል ነው የተከፈተው” ብሏል።

በዛሬው እለት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳስታወቀው “ተማሪዎች ላይ የፀጥታ ችግር ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ዩኒቨርሲቲው ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን” ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።

በተጨማሪም ዩኒቨርስቲው መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባሩን ቀጥሏል ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወ/ሃና የፀጥታ ሁኔታውን ለማረጋገጥ ከከተማው የፀጥታ ሀይል ጋር በመሆንም አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲዉ የሚገኙ ተማሪዎች እንደገለፁት አሁን ያለው ሁኔታ ከትላንትናው አንፃር የተረጋጋ የሚባል ነው። “ነገር ግን ተማሪዎች ላይ ስጋት በመፍጠሩ አዲስ አበባ ውስጥ የቅርብ ዘመዶች ያሏቸው ተማሪዎች ከግቢ እየወጡ ወደቤተሰብ እየተጠጉ ይገኛሉ” ሲሉም ተማሪዎች ላይ የተፈጠረውን ድንጋጤ ገልፀዋል።

እንደዚህ አይነት ችግር ሲፈጠር በዩኒቨርሲቲዉ የመጀመሪያ ባለመሆኑ አሁንም እስከመጨረሻው ሰላም ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም የሚሉት ተማሪዎች፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተማሪዎችን ለመጠበቅ ምንም አላደረጉም ብለዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በኮሚቴም ጭምር አስተዳደሮችን ስለ ደህንነታቸው ቢጠይቁም “እናንተ ራሳችሁን ጠብቁ” ከሚል ቃል ውጪ ምንም የሰጡት ምላሽ አለመኖሩን አዲስ ዘይቤ ሰምታለች።

አስተያየት