መጋቢት 6 ፣ 2014

እስራኤል ኢትዮጵያዉያን የሀይማኖት ተጓዦች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አገደች

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

የእስራኤል የህዝብ እና ስደት ጉዳዮች ባለስልጣን በእስራኤል ለሚገኙ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚዎች ከኢትዮጵያ የሚጓዙ የመንፈሳዊ ተጓዦችን እንዳይቀበሉ ደብዳቤ መላኩ  ተሰምቷል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

እስራኤል ኢትዮጵያዉያን የሀይማኖት ተጓዦች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አገደች
Camera Icon

ፎቶ፡ አሶሼትድ ፕረስ

የእስራኤል የህዝብ እና የስደት ጉዳዮች ባለስልጣን ኢትዮጵያዉያን በመንፈሳዊ ጉዞም ቢሆን ወደ እስራኤል እንዳይገቡ መወሰኑን የመገናኛ ብዙኀን በትላንትናዉ እለት ዘግበዋል።

የእስራኤል የህዝብ እና ስደት ጉዳዮች ባለስልጣን በእስራኤል ለሚገኙ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚዎች ከኢትዮጵያ የሚጓዙ የመንፈሳዊ ተጓዦችን እንዳይቀበሉ ደብዳቤ መላኩ  ተሰምቷል። 

እገዳዉ ኢትዮጵያዉያዉያን ተጓዦችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን  የእገዳው ዋነኛ መንሳኤ በኢትዮጵያ ያለው “የእርስ በእርስ ጦርነት” ነው መባሉን መቀመጫዉን እየሩሳሌም ያደረገው ‘ታይምስ ኦፍ እስራኤል’ ዲጂታል ጋዜጣ አስነብቧል።

የእስራኤል የህዝብ እና ስደት ጉዳዮች ባለስልጣን በደብዳቤው እንዳስታወቀው “በኢትዮጵያ ያለውን የእስር በእርስ ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያዉያን ወደ እስራኤል ከመጡ አይመለሱም የሚል ስጋት በመኖሩ” ለሀይማኖታዊ ጉዞዎች እንዳይገቡ ብሏል። ባለስልጣኑ ለጉዞ ወኪሎች እንደገለፀው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እስራኤልን መጎብኘት ወይም ለመንፈሳዊ ጉዞ መጓዝ ከፈለጉ ጥያቄያቸዉን በቀጥታ ለእስራኤል የህዝብና ስደት ጉዳዮች ባለስልጣንን በበይነ መረብ ላይ ማቀረብ አለባቸው መባሉን ዘገባዉ ያሳያል።

በሳኡዲ አረቢያ ዋና መስሪያ ቤቱን ያደረገው እና በመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ጥምረት የተመሰረተው ‘ትሪቡናል ኮሚዩኒቲ’ ጋዜጣ በበኩሉ ወደ እስራኤል የሚገቡ ተጓዦችን የሚቀበሉ የአስጎብኚዎች ማህበር ለሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በፃፈው ይፋዊ ደብዳቤ “እስራኤል የምትከተለዉ የጉዞ ፖሊሲ በርካታ መገለሎችን እያደረሰ መሆኑን” ተችቷል። የአስጎብኚዎች ማህበሩ አክሎም ውሳኔውን የተቃወሙ በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የመንግስት ባለስልጣናትን እየተቹ ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ የእስራኤል የህዝብ እና ስደት ጉዳዮች ባለስልጣን “ባለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የገቡ ጎብኚዎች ከሚመለከተው የመንግስት እውቅና እና ፈቃድ ውጪ በህገ ወጥነት እየኖሩ በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ማለቱን ‘ትሪቡናል ኮሚዩኒቲ’ አስነብቧል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት የእስራኤል ካቢኔ 3 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ወደ እስራኤል እንዲገቡ መወሰኑን አስታውሰው ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸው ኢትዮጵያዉያን ብቻ የሚፈቀድላቸው በመሆኑ በፍጥነት ወደ እስራኤል እንዲገቡ አሳስበዋል።

የዐብይ ፆም ፍቺን ተከትሎ በሚከበረው የፋሲካ በዓል ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ እና የእስራኤል የጉዞ ወኪሎች ወደ እየሩሳሌም የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን የኦርቶክስ እምነት ተከታዮች ወደ እስራኤል ይጓዛሉ።