መጋቢት 6 ፣ 2014

የእስራኤል መንግስት አግዶት የነበረውን የኢትዮጵያዊ ቤተ- እስራኤላውያንን ጉዞ ፈቀደ

ዜና

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ወስኖበት የነበረውን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚጓዙ ቤተ-እስራኤላዉያንን ጉዞ እንዲቀጥል ወሰነ።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የእስራኤል መንግስት አግዶት የነበረውን የኢትዮጵያዊ ቤተ- እስራኤላውያንን ጉዞ ፈቀደ
Camera Icon

Credit: TOMER NEUBERG/FLASH90

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ወስኖበት የነበረውን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚጓዙ ቤተ-እስራኤላዉያንን ጉዞ እንዲቀጥል ወሰነ።

የእስራኤል ካቢኔ ምክር ቤት በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. መጨረሻ 3 ሺህ ቤተ-እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል እንዲገቡ ወስኖ ነበር። በጊዜው፣ “ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የእስር በእርስ ግጭት ያላገናዘበ ነው” የሚሉ ወቀሳዎች መሰንዘራቸውን ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ጋዜጣ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤሎችን ወደ እስራኤል ለመውሰድ ከተወሰነ በኋላ ደግሞ በጥር ወር መጨረሻ ላይ የእስራኤል የስደት ፖሊሲ ማእከልን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ “ወደ እስራኤል መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎችን አይሁዳዊነትን ለማረጋገጥ ትክክለኛ መመዘኛ አለመቀመጡ እና ዜጎቹ የዘር ሀረጋቸው ከእስራኤል የሚመዘዝ መሆኑ ወደ አስራኤል ሳይገቡ መረጋገጥ ይኖርበታል” የሚል ቅሬታ አቅርበው ነበር።

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቹ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎም ኢትዮጵያዊ ቤተ-እስራኤላዉያኑን ወደ እስራኤል የመውሰድ ሂደት በጊዜያዊነት እንዲቆም ውሳኔ አስተላልፏል። 

ይሁን እንጂ ከአምስት ሳምንታት በኋላ ዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ካጣራ በኋላ ውሳኔውን ማንሳቱን የ’ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ዘገባ አስነብቧል።

የእስራኤል የአዲስ ስደተኞች እና ተመላሽ ነዋሪዎች ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ለውሳኔው አመስግኖ ተሰብስቦ የነበረው አቤቱታ የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የጣለ ነበር ማለቱ ተሰምቷል። 

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ኒና ታማኖሸታ “በዚህ ውሳኔ መቋረጥ ኢትዮጵያ የቆዩ ቤተ-እስራኤላውያን ከበቂ በላይ ተንገላተዋል፤ የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገቢውን ውሳኔ በማሳለፉ ለእነዚህ ሰዎች መታገሌን እቀጥላለሁ።” ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል። ሚንስትሯ በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ዩክሬናዉያን ቤተ-እስራኤሎች ወደ እስራኤል እንዲገቡ ጥረታችንን እንደሚያጠናክሩም ገልፀዋል።

አስተያየት