መጋቢት 7 ፣ 2014

‘ኦብነግ’ ከ25 ዓመታት በኋላ 2ኛውን ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ አሳወቀ

City: Somaliዜና

ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው በፓርቲው ሕገ-ደንብ፣ በሚከተለው የፖለቲካ ፕሮግራም እና በሌሎች የግንባሩ ውስጣዊ አሰራሮች ላይ በሰፊው እንደሚመክር ይጠበቃል።

Avatar: Abdi Ismail
አብዲ ኢስማኤል

Abdi Ismail is Addis Zeybe's correspondent in Somali regional state

‘ኦብነግ’ ከ25 ዓመታት በኋላ 2ኛውን ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ አሳወቀ
Camera Icon

ፎቶ፡ አብዲ ኢስማኤል

በአሸባሪነት ተፈርጆ ለ25 ዓመታት ከሐገር ውጭ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ የነበረው፣ በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክርቤት 2 መቀመጫ ያለው፣ እኤአ በ1984 ዓ.ም. የተመሰረተው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ ድርጅታዊ ጉባኤውን በጅግጅጋ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል። አዘጋጅ ኮሚቴው ጉባኤው ከመጋቢት 7 እስከ መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚያካሂድ አስታውቋል።  

የኦብነግ የፓርቲ ጉዳዮች ኃላፊና የግንባሩ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሁሴን መሀመድ ኑር ለሁሉም የፓርቲው አባላት ክፍት እንደሚሆን በሚጠበቀው ጉባኤ ላይ “የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ይገኛሉ” ብለዋል። ከአጀንዳዎቹ መካከልም የግንባሩ ውስጣዊ ችግሮች ላይ መወያየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ማስቀመጥ እንዲሁም በወቅታዊ እና ሐገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንደሚገኙበት አቶ ሁሴን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው በፓርቲው ሕገ-ደንብ፣ በሚከተለው የፖለቲካ ፕሮግራም እና በሌሎች የግንባሩ ውስጣዊ አሰራሮች ላይ በሰፊው እንደሚመክር ይጠበቃል።

“ጊዜው የሶማሌ ክልልን ህዝብ የማይጠቅሙ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት አይደለም” ያሉት የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሐሳብ ልዩነቶች ቢኖር ቢችልም ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል። በተጨማሪም “የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር በጉባኤው ላይ በአካል ተገኝቶ በአጀንዳዎቹ ላይ በመወያየት የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ደምጠዋል።

ኦብነግ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁሉም ፓርቲዎች ጉባኤ እንዲያካሂዱ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ነው።

ቦርዱ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የአባላት ጠቅላላ ጉባኤዎች እንዲያካሂዱና ውጤቱን ለቦርዱ እንዲያቀርቡ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23 ቀን 2014 ከፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ምክክር ከ6ተኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ በጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ይሁን እንጂ. አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ባለማድረጋቸው በትግራዩ ጦርነት ምክንያት ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተነሳ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ሰነዳቸውን ለቦርዱ እንዲያስገቡ መወሰኑ ይታወሳል። በዚህም መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳ ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ ጨምሮ 13 የፌደራልና 13 የክልል ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ አከናውነው አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል።

አስተያየት