በአማራ ክልል በመተማ በኩል በሕገ-ወጥ መንገድ ከሐገር ለመውጣት የሚሞክሩ ወጣቶች ቁጥር ማሻቀቡ ተሰምቷል። በያዝነው ዓመት ከየካቲት 15 ቀን ጀምሮ ባሉ 21 ቀናት ብቻ 398 ተዘዋዋሪ ስደተኞች፣ ተጠርጣሪ ደላሎች እና የሆቴል ባለቤቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጾአል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር በስራ እና ስልጠና መምሪያ የስራ ስምሪት ማስፋፊያ ቡድን መሪ ወ/ሮ ጠይባ አብዱልቃድር በተጠቀሱት ቀናት በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 230 ሕገ-ወጥ ስደተኞች መካከል 222ቱ ከደቡብ ኢትዮጵያ “ቡሎሶሶሪ” ወረዳ፣ 8ቱ ከኦሮሚያ ክልል እንደመጡ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህጻናት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር አልማዝ ላቀው ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የመጡት ተጓዦች መነሻቸውን አዲስ አበባ በማድረግ፣ በጎንደር አቋርጠው ወደ ሱዳን የመሻገር እቅድ ያላቸው ናቸው። ሕገ-ወጥ ተሰዳጆቹ ከ14 እስከ 38 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ወ/ሮ ጦይባ አልቃድር በበኩላቸው “ከየካቲት 15 እስከ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከተያዙት 230 በሕገ-ወጥ መንገድ ከሐገር ለመውጣት የሞክሩ ግለሰቦች መካከል 227 ያህሉ ሴቶች ናቸው” ብለዋል።
“ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በጎንደር ከተማ በስፋት እየተበራከተ ያለ ድርጊት ነው” ያሉት ኮማንደር አልማዝ ተጓዦቹ የመሚመጡባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ሲናገሩ “ከደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ከሱማሌና እና ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡት አብላጫ ቁጥር አላቸው” ብለዋል።
እስከ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከተያዙት 398 ሰዎች መካከል የጸጥታ አካላት ባደረጉት ርብርብ፣ በማኅበረሰቡ ጥቆማ በየካቲት ወር መጨረሻ አካባቢ በአንድ ቀን ብቻ 40 ሕገ-ወጥ ተዘዋዋሪዎችን ከተጠርጣሪ ደላላ እና ባለሆቴሎች ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ለጉዞ በመሰናዳት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
“የተጓዦችን ህይወት ማዳን የመጀመርያ ሥራ ነው” ያሉት ኮማንደር አልማዝ ሕገ-ወጥ ተጓዦችን በቁጥጥር ስር በማዋል 385 ሰዎችን ወደመጡበት አካባቢ መመለሳቸውን ተናግረዋል። 115 ያህሉ ከቤተሰቦቻቸው ለመገናኘት የመመለሻ ወጫቸውን በራሳቸው የሸፈኑ ሲሆን የ270 ተጓዦችን ወጪ የሸፈነው የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ነው። ቀሪዎቹ 9 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
የሆቴል ባለቤቶችን ጨምሮ በድለላ እና በተባባሪነት ሥራ ላይ እጃቸው ያለበት 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል። ስደተኞቹ መንገድ የጀመሩት ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ዱባይ፣ ኬኒያ እንደሚጓዙ በደላላ ተታለው መሆኑን ወ/ሮ ጦይባ ተናግራለች።
በዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) አማካኝነት መስራት የፈለጉትን የስራ ዘርፍ እንዲያሳውቁና የፍልሰተኞች ድርጅቱ የቁሳቁስ፣ የከተማ አስተዳደራቸው የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እንዲያገኙ እና ወደመጡበት ተመልሰው መስራት እንዲችሉ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ታውቋል።
እንደ ወ/ሮ ጠይባ ገለጻ “አብዛኛዎቹ ተዘዋዋሪዎች ለሚዲያ ቅርብ አይደሉም። የሚኖሩበት አካባቢ ከሚዲያ ግንኙነት ውጭ ካለ ገጠራማ ክልል የመጡ ናቸው። የደላላውን የማታለያ ቃላት እንጂ የሚገጥማቸውን መጥፎ ችግር አያስቡም። ቀጥታ ዱባይ የሚገቡ የሚመስላቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው” ብለዋል።
በወ/ሮ ጠይባ ሐሳብ የሚስማሙት ኮማንደር አልማዝም በተለይ በደቡብ ክልል በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ስለ ሕገ-ወጥ ስደት ግንዛቤ መፈጠር እንደሚገባው አንስተዋል። በሕገ-ወጡ ድርጊት ላይ እጃቸው ያለበት ተሳታፊዎችም ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።