መጋቢት 4 ፣ 2014

የ4ኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ህይወት እና እረፍት

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ስነ ስርዓት መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የ4ኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ህይወት እና እረፍት
Camera Icon

ፎቶ: ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት

አቡነ መርቆሬዎስ በልዩ ስሟ “ስሙማ ምድር” በምትባል አካባቢ በ1930 ዓ.ም. ተወለዱ። ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ በቀድሞ አጠራር በደብረታቦር አውራጃ፣ በአለታ ወረዳ፣ በአዳጊት ኪዳነምህረት ገዳም ሰበካ ተወለዱ። 

የዓለም ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ ነው። ከተወለዱበት ገዳም አንስተው በመላ ሐገሪቱ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት እየተዘዋወሩ መንፈሳዊ ትምህርት ቀስመዋል። አጨታ ኪዳነ ምህረት፣ ጎንጅ ቴዎድሮስ ገዳም፣ ዋሽራ፣ አጋጥ ደብረጽዮን፣ መነጎዛር፣ አቡነ አረጋዊ ደብር ተዘዋውረው ከተማሩባቸው አድባራትና ገዳማት መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው።

ንባብ፣ ዳዊት፣ ምዕራፍ፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ቅኔ፣ አቋቋም፣ ዝማሬ፣ መዋስእት ከተማሯቸው ትምህርቶች መካከል ይገኙባቸዋል። እያንዳንዱን ትምህርት ለማጠናቀቅ ከ2 እስከ 4ዓመት ፈጅቶባቸዋል።

በጋይንት ወረዳ በምትገኘው ስመ-ጥሩዋ ቤተልሄም ለ4ዓመታት ቆይተው ድጓ ካስመሰከሩ (ዕውቀታቸውን ካረጋገጡ) በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል። ከዚያም በአዳጊት ኪዳነምህረት ገዳም ለ7 ዓመታት ድጓ አስተምረዋል። 

በ1961 ዓ.ም. ስርአተ ምንኩስናን ከጣና ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ተቀብለዋል። ማዕረገ ቅስናንም በዚያው ዓመት ከወቅቱ የጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብጹእ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል።

በገዳም ቆይታቸው በልማት ሥራዎች፣ በጸሎት ማኅበር ተሳትፎ፣ አቅመ ደካሞችን በመርዳት የሚታወቁት አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት ዓታት የስሙጋ ሻላ ገዳም ቆይታቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ አመሩ። (ስሙጋ በባህርዳር አውራጃ የሚገኝ ገዳም ነው) አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴ እና በማኅሌት እንዲሁም በመምህርነት እያገለገሉ ትርጓሜና አቡሻኸር ተምረዋል።

ዘመናዊ ትምህርታቸውንም እስከ ሁለተኛ ደረጃ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደተማሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያንን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ያስተዳደሩት ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር። ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. የፓትርያርክነት መንበረ ስልጣኑን ቢረከቡም ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ከሐገር ወጥተዋል።

ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ጥሎ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ተራውን የተረከበው ኢህአዴግ ባበረታባቸው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከሦስት ወራት በኋላ መንበራቸውን ለቀው ወደ አሜሪካን ሐገር ተሰደዋል። ቅዱስ ሲኖዶስን ለሁለት ከፍሎ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው አለመግባባት የተፈታው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር።

“የቅዱስ ሲኖዶስን ክፍፍል ያስከተለው የ4ኛው ፓትርያርክ ከሐገር መውጣት ነው” የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ “4ኛው በህይወት እያሉ 5ኛው መሾማቸው ስህተት ነበር” የሚሉትን በአንድ ወገን ሲያከራክር የቆየው ክስተት ሲኖዶስን ለሁለት ከፍሏል።

አቡነ መርቆሬዎስ በአሜሪካን ሐገር ቆይታቸው “ስደተኛው ሲኖዶስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን “ ቅዱስ ሲኖዶስ” ለ26 ዓመታት ሲመሩ ቆይተው በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥረት ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል። በእርስ በእርስ ውግዘትና በፖለቲካ መገፋፋት እንደዋዛ በነጎደው የአንድ ወጣት እድሜ በርካታ ሁኔታዎች ‘ነበር’ ሆነዋል። በሕይወት ያሉትን 4ኛውን ፓትርያርክ የተኩት 5ኛው ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አልፈው በ6ኛው ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተክተዋቸዋል። በትጥቅ ትግል ወታደራዊውን መንግሥት የተካው ኢህአዴግ ከተማ ባፈራው ብልጽግና በተራው ተተክቷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የጠቅላይ ሚንስትር መለስን መንበር ተረክበዋል።

አቡኑ በአገልግሎት ዘመናቸው በበርካታ ገዳማትና አድባራት በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብኤል ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ የኦጋዴን አውራጃ ሊቀ ጳጳስ፣ የጎንደር ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በመሆን ያገለገሉባቸው ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት፣ የሐገር እና የቤተክርስቲያን ቅርሶች እንዲጠበቁ በማድረግ፣ የሰበካ ጉባኤዎችን በማቋቋም፣ መንፈሳዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስከፈት፣ መተዳደሪያ ያልነበራቸው የአብነት ትምህርት መምህራን ደሞዝ እንዲያገኙ በማስወሰን፣ የቤተ-ክርስቲያን መመሪያ የሆነውን ቃለ-አዋዲ በማስተግበር፤ በጭልጋ፣ በሊቦ፣ በደብረታቦር፣ በጋይንት አውራጃዎችና በእስቴ ወረዳ የችግኝ ጣቢያዎች በማቋቋም ችግኞች እንዲከፋፈሉ፣ ጥንታዊውና ታሪካዊው የጣና ቂርቆስ ገዳም እንዲታደስ፣ የደረሞ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን እንዲታደስ፣ የገርቢ ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን እንዲታደስ፣ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ፣… ባደረጉት አስተዋጽኦ ሲታወሱ ይኖራሉ።

ብጹእነታቸው ባደረባቸው ህመም የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. 6ኛው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ጨምሮ በርካታ ብጹአን አባቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል። አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የሌሎች ሐይማኖቶች መሪዎች እና አምባሳደሮችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ለአገራቸው በየደረጃው ከልጅነት እስከ እውቀት የሚገባቸውን ሁሉ አግልግሎት ማበርከታቸውን አውስተዋል። ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብሎም ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ሲሰጡ መቆየታቸውን እና ቤተክርስቲያን የሰጠቻቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣታቸውን ተናግረዋል።

የህይወት ዘመናቸውን መጨረሻ በአርምሞ እና በጸሎት ያሳለፉት አቡነ መርቆሬዎስ ከጠፊው ዓለም ወደ ዘልአለማዊው ዓለም በክብር ተሻግረዋል ነው ያሉት።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ስነ ስርዓት መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

አስተያየት