መጋቢት 3 ፣ 2014

በትግራይ ዩንቨርሲቲዎች የተማሩ የዚህ ዓመት ተመራቂዎች ውጤታቸው ባለመላኩ መቸገራቸውን ተናገሩ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡት ተማሪዎቹ በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እድሉ ተመቻችቶላቸዋል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በትግራይ ዩንቨርሲቲዎች የተማሩ የዚህ ዓመት ተመራቂዎች ውጤታቸው ባለመላኩ መቸገራቸውን ተናገሩ

በትግራይ ክልል በሚገኙት አዲግራት፣ መቐለ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ትምህርታቸውን መቀጠል አለመቻላቸው ይታወቃል። በወቅቱ የተማሪዎቹን ጉዳይ በተመለከተ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ከጦርነቱ ቀጣና ለማውጣት ባቋቋምኩት የቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት ከ10ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አገናኝቻለሁ ብሏል። ኮሚቴው ወደ አንድ ወር ገደማ ፈጀብኝ ባለው ሂደት ከመቐለ ከ3ሺህ 6መቶ በላይ፣ ከአክሱም ከ2ሺህ 9መቶ በላይ፣ ከአዲግራት ከ2ሺህ 3መቶ በላይ ተማሪዎችን ወደቀደመ ቀያቸው መልሷል።

ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡት ተማሪዎቹ በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እድሉ ተመቻችቶላቸዋል። ተማሪዎቹ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ናቸው። ለመመረቅ ወራቶች ከሚቀራቸው ጀምሮ ለጥቂት ወራት ብቻ ትምህርታቸውን እስከተከታተሉት ድረስ ይገኙበታል።

በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው፣ ዳግም ምዝገባቸውን በስሊፕ እና በመታወቂያ አከናውነው ትምህርታቸውን የቀጠሉት ተማሪዎች “ዛሬም ቅሬታችን አልተፈታም። በትምህርት ያሳለፍናቸው ዓመታት ባክነውብናል” የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ያሰማሉ።

ተማሪ እዮብ ዘነበ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ተማሪ እንደነበር ይናገራል። በጦርነቱ ምክንያት ከነበረበት መቐለ ዩኒቨርሲቲ በአፋር በኩል ከቤተሰቦቹ ጋር በሰላም ተቀላቅሏል። ከነበረበት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ያለፉትን ዓመታት የትምህርት ውጤቱን የሚያሳይ ማስረጃ አለማምጣቱ ስጋት ፈጥሮበታል። የተመደበበት ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ማስረጃ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ሲማር የነበረውን የሚያጠቃልል አለመሆኑ “ትምህርቴን ባጠናቅቅም የተሟላ ማስረጃ አይኖረኝም። የጥቂት ወራት ኮርሶችን ውጤት ብቻ ዐይቶ የሚቀጥረኝም አይኖርም” የሚል ስጋቱን አጠናክሮታል።

በተመሳሳይ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ተማሪው ጌዲዮን ደርቤ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ትምህርቱን እየቀጠለ ነው። የያዝነው ዓመት ትምህርቱን አጠናቆ ቢመረቅም ብዙም የጓጓ አይመስልም። “የምመረቀው ባለፈው ዓመት ነበር። በግጭቱ ምክንያት በያዝነው ዓመት ሰኔ ላይ እመረቃለሁ። አሁን እያሰብኩ ያለሁት ስላለፈው ውጤቴ እንጂ ስለ አሁኑ አይደለም” ይላል። ያልተሟላውን የትምህርት ዶክመንት እንዳሟላ የሐገሪቱ ወቅታዊ ሁሄታ ስላልፈቀደለት “ችግራችን መፍትሔ ያለው አይመስልም” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። “ከትግራይ ስንወጣ ውጤታችንን አልያዝንም፣ አሁን ማምጣት የምንችልበት እድልም የለም፣ ጉዳዩ ከትምህርት ሚኒስቴርም አቅም በላይ ነው። ሁላችንም ግራ ተጋብተናል” ሲል ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ አስረድቷል።

ከጦርነቱ በፊት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከጦርነቱ በኋላ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆነው አላዛር መኮንን የተማሪዎቹ ስጋት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለው።

“አንድ ተማሪ ሲመረቅ የተሟላ መረጃ ይዞ መሆን ይኖርበታል። የወሰዳቸው ኮርሶች ዝርዝር፣ በየዓመቱ ያገኘው ውጤት ተሰብስበው በአንድነት መኖር አለባቸው። ይህ በሌለበት ሁኔታ ቀርቷቸዋል የተባለውን ኮርስ ብቻ ወሰወደው ለምርቃት መሰናዳታቸው አብዛኛዎቹን ተማሪዎች ሲረብሽ ተመልክቻለሁ። ቅሬታቸው ተገቢ አይደለም ማለትም አይቻልም። ተገቢ ስጋት ነው” ብሎናል።

አዲስ ዘይቤ በተጨማሪም ከአክሱም ዲላ፣ ቦንጋ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን አነጋግራ ተመሳሳይ ምላሽ አግኝታለች። ተማሪዎቹ የሚማሩበት ከተማ የጦርነት ቀጣና ሲሆን የቅድሚያ ሐሳባቸው ራሳቸውን ማዳን ነበር። ነገሮች ሲረጋጉ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን ሲመሩ ግን በቅጡ ያልተሰነደው የዓመታት የትምህርት ውጤታቸው ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። ከምርቃት በኋላ በሚኖራቸው ህይወት እንደ ሌሎች ተማሪዎች ሙሉ የትምህርት ማስረጃቸውን ተቀብለው በሥራው ዓለም ተወዳዳሪ የሚሆኑበት እድል እንደጠበበ ተሰምቷቸዋል። ከተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ይመለከታቸዋል ላሏቸው አካላት ጥያቄአቸውን ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መረጃን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስተር የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ የሆኑት አመለወርቅ ህዝቅኤል ሁሉም ተማሪዎች ሲመዘገቡ በዶክመንታቸው እና በዲፓርትመንታቸው መሆኑን ይናገራሉ። “ሲመረቁም ሙሉ መረጃቸው ይዘው ነው የሚመረቁት  ከዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ውጤት ማስረጃ አልደረሰንም የሚለው ጉዳይ የሚመለከተው እኛን ሳይሆን የትምህርት ሚኒስተር አካዳሚክ ዳይሬክተርን ነው” ብለውናል።

"መመረቅ የነበረብን ባለፈው ዓመት ነበር። አሁን ግን መጋቢት መጨረሻ ላይ ዲፌንስ አቅርበን ብቻ ወደ ቤት ትሄዳላችሁ መባላችን አሳዝኖናል። "የምትለው ደግሞ በአክሱም ዮኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት አፕላይድ ኬሚስትሪ ተማሪ የነበረችው እና አሁን ላይ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ ትምህርቷን እየተከታተለች የምትገኘው ተማሪ ሜላት መኮንን ናት። ለፍተን ተምረን ያለ ውጤት ወደ ቤት እንድንመለስ መደረጋችን አዕምሯችንን ጎድቶታል" ትላለች። ጋዋን ለብሰው የምረቃ ስነ-ስርአቱን የሚካፈሉት ሁሉንም ዓመት በግቢው ውስጥ ያሳለፉ ተማሪዎች ናቸው መባሉ ዩኒቨርሰቲው እንደ መደበኛ ተማሪው እንዳልቆጠራቸው ዕንደሚያሳይ እንደምታምን ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ ሚጄና የተማሪዎች ቅሬታ አግባብነት የለውም ይላሉ "ሁሉም በትግራይ ክልል ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመመደባቸው በፊት የነበራቸውን ውጤት እንዲሞሉ ፎርም ሞልተዋል። በዚያ መሰረት ምደባ አከናውነናል" የሚሉት አካዳሚክ ዳይሬክተሩ "ማንኛውም ተማሪ ውጤቱን ከዩኒቨርሲቲ የኦላይን የመረጃ ቋት ላይ ገብቶ መመልከት ይችላል። አስፈላጊ ከመሰለውም ዳውንሎድ አድርጎ ሊያስቀምጠው ይችላል” ብለዋል።

በየሴሚስተሩ ውጤታቸውን በኦላይን ይመለከቱ የነበሩት ተማሪዎች በበኩላቸው፤ ከዩኒቨርሲቲው ከወጡበት ጊዜ አንስቶ የዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ አገልግሎት እየሰጠ እንደማይገኝ አሳውቀዋል። በትምህርት ሚኒስትር በኩል እንዲሞሉት የተላከላቸውን ፎርም አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሞሉት በግምት እንደነበረም አንስተዋል። “ውጤቱን የተመለከትንበት ጊዜ ስለቆየ ሁሉንም ኮርሶች በትክክል ማስታወስ ይከብዳል” ያሉት ተማሪዎቹ “ያላስታወስናቸውን የሞላነው በግምት ነው” ይላሉ።

በተማሪዎች ጥያቄ ዙሪያ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዶ/ር ኤባ ሚጄና “ከዩኒቨርሲቲ የበላይ አካላት ጋር ተነጋግረን በቅርቡ ምላሽ እንሰጣለን” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

አስተያየት