መጋቢት 2 ቀን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች የደንበኞች ሰልፍ እና ግርግር ተስተውሎባቸዋል። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን እንደ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ አፋር ክልል ሎጊያ ከተማ፣ ሐዋሳ እና ሌሎች ከተሞችም በተለይ ከምሳ ሰዓት በፊት ባለው ጊዜ የረዘመ ሰልፍ ስለመኖሩ በየአካባቢው የሚገኙ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢዎች ሪፖርት ያሳያል። በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ የነበረው የባንክ ደንበኞች ሰልፍ የጸጥታ ኃይል እስከማሰማራት ያደረሰ ሲሆን ግርግሩን ተጠቅመው ለዘረፋ የተሰማሩ መኖራቸውንም አዲስ ዘይቤ ከዓይን እማኞች ማረጋገጥ ችሏል።
ባንኩ በልዩ ልዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የተከሰተውን መጨናነቅ ተከትሎ ከቀኑ 6፡30 ላይ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች መረጃ ያላሟሉ ደንበኞች የተወሰኑ የባንኩ አገልግሎቶች እንደሚቋረጡባቸው አሳውቋል። ይህም በዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ውስጥ የሚካቱት የሞባይል ባንኪንግ እና የኤቲኤም አገልግሎቶች ብቻ እንደሚቋረጡ እና በቅርንጫፍ ባንኮች በአካል በመቅረብ የሚሰጠው መደበኛ አገልግሎት ባለበት ይቀጥላል ብሏል። ይሁን እንጂ በድጋሚ ባወጣው ሌላ ማሳሰቢያ የደንበኞችን መረጃ የማሰባሰብ ስራው ለተጨማሪ 2 ወራት ተራዝሟል የሚል መረጃ አሰራጭቷል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በደንበኞቹ የእጅ ስልክ በላከው የጽሁፍ መልዕክት ማንኛውም የባንኩ ደንበኛ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ቅርንጫፍ ባንኮች በአካል በመሄድ አስፈላጊውን መረጃ ካልሰጠ ከመጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በኋላ ማንኛውንም የባንክ አገልግሎትን ማግኘት እንደማይችል አሳስቦ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት በመረጃ ቋታቸው ማካተት የሚገባቸውን የደንበኞቻቸውን መረጃ በተመለከተ ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተግባራዊነቱ የተራዘመው መመሪያ የአዋጁን መነሳት ተከትሎ ሲተገበር በቅድሚያ ያወዛገበው የታደሰ መታወቂያ ጉዳይ ነበር። የቀበሌን ጨምሮ ማንኛውም መታወቂያ አዲስ መስጠትም ሆነ ማደስ በተቋረጠባቸው ወራት የታደሰ መታወቂያ ባንኩ መጠየቁ ያላሳመናቸው ደንበኞች ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያሰሙም ባንኩ በቀደመ አሰራሩ ቀጥሎበታል።
ብሔራዊ ባንክ በመመሪያው ለዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ የመስጠት ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የፋይናንስ ተቋማቱ ለደንበኞቻቸው የተለየ የመለያ ቁጥር እንዲሰጡ አስገድዷል። የልዩ መለያ ቁጥሩ ዓላማ አንድ ደንበኛ በአንድ ባንክ ከአንድ በላይ አካውንት እንዳይኖረው ማስቻል ነው። በአንድ ባንክ የተለያዩ ቅርንጫፎች በርከት ያለ ሂሳብ ያላቸው ሰዎች ሂሳባቸውን ወደ አንድ አካውንት እንዲያጠቃልሉ የሚያስገድደው አሰራር ዋና አላማም አንድ ደንበኛ እንደ አንድ ሰው ብቻ የሚያሳውቀው ማንነት እንዲኖረው ማስቻል መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ባወጣው መመሪያ መሰረት ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት እስከ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የደንበኞችን መረጃ እንዲያደራጁ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር። በመመሪያው መሰረት በቀነ ገደቡ መሰረት ደንበኞች ሂሳብ በከፈቱባቸው ባንኮች በአካል በመገኘት ቀሪ ተፈላጊ መረጃዎችን እስከሚሰጡ ሂሳባቸው ሊታገድ እና የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ሊደረግ ይችላል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የጊዜ ገደብ ማስቀመጡን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የታዩ መጨናነቆች ቢከሰቱም፤ ሌሎች የግል ፋይናንስ ተቋማት ግን ይህን ገደብ ባለማስቀመጣቸው ሂሳብ የተዘጋባቸው ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ እንዲያስተካክሉ ፈቅደዋል። እንዲሁም የተወሰኑ የግል ባንኮች በደንበኞች የእጅ ስልክ በመደወል በአካል እንዲመጡ የማስታወስ እና የጎደሉ መረጃዎችን በመጠየቅ ሲሰሩ እንደነበረ መታዘብ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ዛሬ ከተከሰተው መጨናነቅ በኋላ አሰራሩን ከሌሎቹ ባንኮች ጋር አመሳስሏል። በዚሁ መመሪያ የተደነገገው ሌላኛው ጉዳይ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት አዲስ ሂሳብ ሲያስከፍቱ፣ ገንዘብ ገቢ ወይም ወጪ ሲደረግ እና ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ገንዘብ ማስተላለፍ ሲያስፈልጋቸው የሚጠየቁ መረጃዎችን ለመመዝገብ በተመሳሳይ ቅፅ እንዲጠቀሙ ያስገድዳል።
በተጨማሪም ሕጎችን ያላከበረ እና አጠራጣሪ ሁኔታ የታየበት ግለሰብ ወይም ድርጅት አገልግሎት እንዳያገኝ የማድረግ ስልጣን ለፋይናንስ ተቋማት የተሰጠ ሲሆን የአጠራጣሪው ግለሰብን ወይም ድርጅትን መረጃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የፋይናንስ መረጃ ደህንነት ማዕከል እንዲያስተላልፉ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
በመጨረሻም የፋይናንስ ተቋማት የደንበኞቻቸውን ሁኔታ እና ታሪክ የሚከታተል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ አደረጃጀት እንዲዘረጉ ግዴታ መጣሉን የብሔራዊ ባንክ አዲስ መመሪያ አስቀምጧል።