መጋቢት 2 ፣ 2014

ለ3 ዓመት ታቅዶ 9 ዓመታት በግንባታ የዘለቀው የጎንደሩ “አይራ ዞናል አጠቃላይ ሆስፒታል” ፕሮጀክት

City: Gonderዜና

የጎንደር ከተማ ጤና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ በለጠ ፈንቴ “ሆስፒታሉ ሲገነባ ለጎንደር ከተማ ብቻ ሳይሆን በዙርያዋ ለሚገኙ አጎራባች ከተሞች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ነው” ሲሉ ጅማሬውን ያብራራሉ።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለ3 ዓመት ታቅዶ 9 ዓመታት በግንባታ የዘለቀው የጎንደሩ “አይራ ዞናል አጠቃላይ ሆስፒታል” ፕሮጀክት
Camera Icon

ፎቶ: ጌታሁን አስናቀ

የአይራ ዞናል አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታ የተጀመረው በ2005 ዓ.ም. ነበር። ለግንባታው ከ140 ሚልዮን ብር በላይ የተመደበ ሲሆን በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ቢታቀድም ከ9 ዓመታት በኋላም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም። 350 የህሙማን አልጋዎች የሚኖሩት ሆስፒታሉ ከ81 ሚልዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ቢመደብለትም እስካሁን ሥራ አለመጀመሩ አነጋጋሪ ሆኗል።

የጎንደር ከተማ ጤና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ በለጠ ፈንቴ “ሆስፒታሉ ሲገነባ ለጎንደር ከተማ ብቻ ሳይሆን በዙርያዋ ለሚገኙ አጎራባች ከተሞች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ነው” ሲሉ ጅማሬውን ያብራራሉ። አይራ ዞናል አጠቃላይ ሆስፒታል ሙሉ ለሙሉ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገለውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ጫና እንደሚያቃልል እምነት ተጥሎበት ነበር። በዓመት ከ190 ሺህ በላይ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድም ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።

“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እያስተናገደ የሚገኘው ታካሚ ከአቅሙ በላይ ነው” የሚሉት ኃላፊው በርካታ ታካሚዎች አልጋ በማጣት በመተላለፊያ ኮሪደሮች ላይ ሳይቀር የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሚገኝ አንስተዋል። የአዲሱ አይራ ዞናል አጠቃላይ ሆሰፒታል በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት በሆስፒታሉ ላይ ያለውን ጫና ከማቃለሉም በላይ ለታካሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ተብሎ ቢጠበቅም የግንባታ ጊዜው ከታቀደው ጊዜ በላይ መውሰዱ ችግሩ በነበረበት እንዲቀጥል ማስገደዱን ኃላፊው አቶ በለጠ አስታውቀዋል።

በሦስት ዓመታት ውስጥ የብቸኛውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል መጨናነቅ እንደሚያስቀር የታመነበት ፕሮጀክት ከታቀደለት ጊዜ ከሁለት እጥፍ በላይ የዘገየበትን ምክንያት በተመለከተ የፕሮጀክቱ የተጠሪ መሃንዲስ ቴዎድሮስ ካሳ የግንባታውን ኃላፊነት የወሰደው “ሲና ኮንስትራክሽን” ሥራውን በጊዜ አጠናቆ አለመመለሱ የመጀመርያው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። በ140 ሚልዮን ብር በጀት ሥራውን የተረከበው ተቋራጩ ሥራውን ለማቋረጡ የሲሚንቶ እና ሌሎች የግንባታ ግብአቶች እጥረትን በምክንያትነት አስቀምጧል። እንደ ተጠሪ መሃንዲሱ ገለጻ የመጀመርያው የንግባታ ተቋራጭ ሲና ኮንስትራክሽን ከነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የሥራ ውሉ ተቋርጦ የግንባታ ፕሮጀክቱ ለሌላ ተቋራጭ ተሰጥቷል። ሲና ኮንስትራክሽን በፈረመው የግዴታ ውል መሰረት የሆስፒታሉን ግንባታ አጠናቅቆ ባለማስረከቡ ክስ እንደተመሰረተበትና ጉዳዩ በፍርድቤት ክርክር ላይ እንደሚገኝም ተጠሪ መሃንዲሱ ይናገራሉ።

ሲና ኮንስትራክሽን 87 በመቶ ያደረሰውን ግንባታ ከህዳር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተረከበው አያሌው አዲሱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ግንባታውን 94.28 በመቶ ቢያደርሰውም አሁንም በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም። የተቋረጠውን የግንባታ ሂደት በ81,393,592.84 ብር በጀት ሀምሌ 7 ቀን 2013 ለማስረከብ ግዴታ ቢገባም አላሳካውም። የሆስፒታሉ ተጠሪ መሃንዲስ የግንባታውን ደረጃ ሲያብራሩ “አሁን የሚቀሩት የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ብቻ ናቸው” ብለዋል። የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሙላት ዘለቀ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ አፈጻጸም ከ94 በመቶ በላይ መድረሱን አረጋግጠዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠሪዎች የሥራ ተቋራጩን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይልን እና አማካሪ ድርጅቱን የእሳት ማጥፊያ እና የትራንስፎርመር ድጋፍ ቢጠይቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን ነግረውናል። ለኤሌትሪክ ስራው መጓተትም ሀገሪቱ ከምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ እና የተቋማት ተባባሪ አለመሆን በምክንያትነት ተቀምጠዋል።

የሲቪል ስራውን በ10 ቀን ውስጥ አጠናቅቀው እንደሚጨርሱ ሥራ አስኪያጁ ኢንጅነር ሙላት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ለኤሌክትሮመካኒካል ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያግዙ ግብአቶችን ከውጭ ለማስመጣት የገበያ ጥናት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መዘግየት ዋነኛ ምክንያት የሲሚንቶ እጥረት፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። “ሁሉንም ስራ እስከ መጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ውስጥ አጠናቀን እናስረክባለን” ብለዋል።

አስተያየት