የካቲት 4 ፣ 2014

ሀሰት፡ ምስሉ በራያ ግንባር የተማረኩ መሳሪያዎችን አያሳይም

HAQCHECK

ፅሁፉን ለመደገፍ የቀረቡትን ምስሎች ትክክለኛነት መርምሮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል።

Avatar: Kirubel Tesfaye
ኪሩቤል ተስፋዬ

Kirubel works as a fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is interested in learning and expanding his writing and journalistic skills.

ሀሰት፡ ምስሉ በራያ ግንባር የተማረኩ መሳሪያዎችን አያሳይም

ከአንድ ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የቴሌግራም ቻናል “በዛሬው ዕለት በራያ ግንባር በጀግኖቻችን ከትግሬ ወራሪ ሃይል የተማረከ መሳርያ” የሚል ጽሁፍን በማያያዝ ጥር 27 ቀን ፤ 2014 ዓ.ም ላይ ምስሎችን አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የቴሌግራም ፖስቱ ከ6700 በላይ ዕይታን አግኝቷል።   

ከ17ሺህ በላይ ተከታይ ያለው ሌላ የፌስቡክ ገጽ ተመሳሳይ ይዘት ካለው ፅሁፍ ጋር አንዱን ምስል አጋርቶት ነበር። ይህ የፌስቡክ ፖስት ከ800 በላይ ግብረ መልስ ሲያገኝ ከ100 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል። 

ይሁን እንጂ ፅሁፉን ለመደገፍ የቀረቡትን ምስሎች ትክክለኛነት መርምሮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል። 

  

በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል በማስወጣት በአፋር እና አማራ ድንበር አካባቢዎች ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።

የፌዴራል እና የክልል ልዩ ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በኋላም የህወሓት ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል አፈግፍገዋል። ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ እንደሚቆዩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ህወሓት የአማራ እና አፋር ሚሊሽያዎች በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረጉብኝ ነው ሲል ወቀሳውን አቅርቦ ነበር።

ሀቅቼክ ምስሎቹን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምስሎቹን በአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን የዩቲዩብ ቻናል ላይ ጥር 25 ፤ 2014 ዓ.ም በቀረበ የዜና ቪድዮ ላይ አግኝቷቸዋል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የዩቲዩብ ቪድዮው ከ150ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል። 

የመጀመርያው ምስል በዜና ቪድዮው በ23ተኛ ደቂቃ ከ05 ሴኮንድ ላይ ይገኛል   

 

 

ሁለተኛው ምስል በዜና ቪድዮው በ22ተኛ ደቂቃ ከ57ተኛ ሴኮንድ ላይ ይገኛል 

 የዜና ቪድዮው፣ “በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ጥምር ሃይል አማካኝነት በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደው ርምጃ ከ100 በላይ የሚሆኑ አባላቱ ተደምስሰዋል” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በቪድዮው ተማረኩ ያላቸውን የሽብር ቡድኑን አባሎች ያሳያል። 

በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፖስቱ ጋር የተያያዙትን ምስሎች ሀቅቼክ ሀሰት ብሏቸዋል። 

አስተያየት