የካቲት 3 ፣ 2014

የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በየጊዜው የሚያሻቅብባት ድሬዳዋ

City: Dire Dawaጤና

ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር ከሌሎች ክልሎች አንፃር ሲታይ በተወሰነ ደረጃ ከፍ ይላል፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በየጊዜው የሚያሻቅብባት ድሬዳዋ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

በኢትዮጵያ የዕምሮ ጤና ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚገኝ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በያዝነው ዓመት መጀመሪያ የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን በተከበረበት ወቅት በጤና ሚኒስቴር የፕሮግራም ሚኒስትር ዴኤታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና አማካሪው አቶ ፍቃዱ ያደታ አጽንኦት ሰጥተውበታል። በዓሉ በድሬዳዋ ከተማ “የአዕምሮ ጤናን ለሁሉም እውን እናድርግ” በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ30ኛ በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ ሲከበር በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ከሚገኙት ከፍ እንደሚል ተጠቅሷል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የሀሮማያ ዩንቨርሲቲ በሰራው ጥናት 33 በመቶ የሚሆነው የድሬደዋ ነዋሪ በአዕምሮ ጤና ህመም እንደሚሰቃይ ያትታል። የከተማዋ አስተዳደር ቁጥሩ የተጋነነ ነው ቢልም የጤና ባለሙያዎቹ በሐሳቡ አይስማሙም።

“በድሬደዋ አስተዳደር ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የአዕምሮ ስፔሻሊስት ዶ/ር ጽዮን አንድ ሰው የማገናዘብ አቅሙን ተጠቅሞ ለራሱና ለሌላ ሰው አስተዋጽፆ ማድረግ ካልቻለ እና የተዛባ አመለካከት ከኖረው በአዕምሮ ህመም ተጠቅቷል እነላለን” ስትል ገልፃለች። እንደ ዶ/ር ጽዮን ገለፃ ሁለት መቶ የሚሆኑ የአዕምሮ ህመም ዓይነቶች ሲኖሩ እነዚህ ህመሞች የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያሉ ለምሳሌ የስሜት መዋዥቅ፣ ድብርት፣ የእንቅልፍ ጊዜ ማጠር፣ በር ዘግቶ መቀመጥ፣ ከሰዉ በላይ ወይም በታች እንደሆኑ ማሰብ፣ ራስን መጥላት የመሳሰሉት ምልክቶች ካሳዩ ግለሰቦቹ ወይ ወደ ህመሙ እየተጠጉ ነው አልያም የአዕምሮ ህመም ገጥሟቸዋል” ስትል አስረድታለች። እነዚህ ሰዎች በስሜት ህዋሶቶቻቸው አማካኝነት በገሀዱ ዓለም የሌሉ ስሜቶችን ሊቀበሉ ይችላሉ።  

“ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር ከሌሎች ክልሎች አንፃር ሲታይ በተወሰነ ደረጃ ከፍ ይላል፡፡ ነገር ግን ያን ያህል የተጋነነ ነው የሚል እምነት የለኝም። ድሬደዋ ከተማ ነች፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ከተሞች እንደ አዲስ አበባ ካሉ ከተሞች ጋር ተነፃፅሮ የተሰራ የቅርብ ጊዜ ጥናት ስለሌለ ሙሉ ለሙሉ ከሌሎች ክልሎች ከፍተኛ ቁጥር ነው ያለው ለማለት አያስደፍርም። በአጠቃላይ ያለውን ሁኔታ ስናየው ግን በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያልደረሱ የአዕምሮ ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ እንደ አስተዳደር “MH gap" (የአዕምሮ ህመምተኞች በሁሉም ጤና ጣቢያዎች ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር) ተጀምሯል። በሁሉም ጤና ጣቢያ በድልጮራ ሆስፒታል የሚሰጠውን ተመሳሳይ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው” የምትለው ዶ/ር ጽዮን “በአሁን ሰዓት ደጅ ወጥቶ የምናየው በጣም ትንሹን ቁጥር ነው፡፡ በአብዛኛው የአዕምሮ ጤና ህመም ይፋ ከመውጣቱ በፊት ህመምተኛው ለረጅም ጊዜ ሊያሰቃየው ይችላል። ለዚህም ነው በአዕምሮ ጤና ህመም የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር መለየት የማይቻለው” ብላናለች።

በድሬዳዋ አስተዳደር ቃልቻ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ጠቅላላ ሀኪም የሆነው ዶ/ር ፍሰሀ ሰለሞን “በድሬዳዋ ከተማ በአሁን ጊዜ የአዕምሮ ህመምተኞች በሁሉም ጤና ጣቢያዎች ቢሄዱ ተመሳሳይ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን “MH gap” በእኛ ጤና ጣቢያም ይሰጣል። ይህ የሆነበት ምክንያትም በአሁን ሰዓት የአዕምሮ ህመምተኛ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው። በተለይ ድሬደዋ ላይ በተለያየ ምክንያቶች ቁጥሩ ከፍ ይላል” እንደ ዶ/ር ፍስሀ ገለፃ እንደ ከተማ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ይህ ነው ማለት ባይቻልም ሊያባብሱ የሚችሉ ምክንያቶችን ለመጥቀስ ግን ጫት በከፍተኛ መጠን መጠቀም እና የተለያዩ አደንዛዥ እፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች መብዛት ለቁጥሩ ከፍ ማለት እንደምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ። “እንደ ማኅበረሰብ የተለያዩ ዓይነት የአዕምሮ ህመም በሚያጋጥም ወቅት ህመሙን ከሀይማኖታዊ ነገር ጋር ማያያዝ የተለመደ በመሆኑ የበሽታውን መጠን ምን ያህል በድሬደዋ እየጨመረ መጥቷል የሚለውን መለየት ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት ነው። ይህንን ችግር ለማቃለል የህክምና ባለሞያውና የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ማሰተማርና የህክምና መንገዶቹን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊን አለባቸው” ብሏል።

በድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት አቶ አቤል ሽፈራው ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች አንፃር የአዕምሮ ህመምተኞች ቁጥር ድሬደዋ ከተማ ላይ ከፍ አንደሚል ተናግሯል። እንደሌሎች ህመሞች በቁጥር ለመግለፅ አመቺ ባይሆንም ከአምስት ዓመት በፊት የወጣ ጥናት እንደሚያመለክተው እንደ ኢትዮጵያ ከ10-25 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአዕምሮ ህመም እንዳለባቸው ያመለክታል። እንደ አስተዳደር የአዕምሮ በሽተኞችን ለመርዳትና የቁጥር መጠኑን ለመቀነስ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ከነሱም መካከል ከዚህ በፊት በድልጮራ ብቻ ተገድቦ የነበረውን የአዕምሮ ህክምና በጤና ተቋማትም አንዲነኖር የጤና መኮንኖችን በማሰልጠን ወደስራ አስገብተናል፣ በድሬደዋ ሳቢያን ጤና ጣቢያ ከሱስ ማገገሚያ መዓከል በመገንባት ላይ ይገኛል ከሶስት ወር በኋላ ስራ ይጀምራል፣ በድልጮራ ሆስፒታል የአንድ ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የአዕምሮ ህመምተኞች ተኝተው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል፣ የስነ-አዕምሮ ሀኪም ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ አስመጥተናል፣ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲመቻች ተደርጓል እንዲሁም በያዝነው ዓመት ድሬደዋ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የስነ-አዕምሮ ቀን ተከብሯል” ሲል አቶ አቤል በአስተዳደሩ ጤና ጣቢያ የተከናወኑትን ነገሮች ተናግሯል።

አስተያየት