የካቲት 3 ፣ 2014

ታካሚዎችን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን በጎንደር

City: Gonderማህበራዊ ጉዳዮች

የጤና አገልግሎት ሽፋን በኢትዮጵያ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲኖረው ምክንያት ከሆኑ መካከል በአገልግሎት ወቅት ታማሚው ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ አንዱ ነው።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ታካሚዎችን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን በጎንደር
Camera Icon

ፎቶ፡ማህበራዊ ሚዲያ

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ መሰረት በማድረግ በ1991 ዓ.ም. ለጤና እንክብካቤ የሚሆን  ገንዘብ  ማግኛ  ስልት  ነድፎ  በሚኒስትሮች  ምክር ቤት አስጸደቀ። የስልቱ ዋና ዋና ዓላማዎችም ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ ሃብት ማሰባሰብ፣ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም፣ የጤና አገልግሎት ጥራትን እና ሽፋንን ማሳደግ፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ እና ቀጣይነት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ ናቸው። ስትራቴጂው ከሀገር  ውስጥ  እና  ከአጋር  ድርጅቶች  ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ ሀብት በማሰባሰብ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የጤና ሁኔታ እንዲሻሻል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዳደረገ ከጤና ሚንስትር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በአዲሱ መንገድ የተመዘገበ ውጤት ቢኖርም የጤና አገልግሎት ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመናሩ፣ አዳዲስ የህክምና ፍላጎቶች መበራከት እና ሌሎችም ሰበቦች  አሁንም በዘርፉ ብዙ መሰራት እንዳለበት ማሳያነት የሚጠቅሱ ባለሙያዎች አሉ።

የጤና አገልግሎት ሽፋን በኢትዮጵያ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲኖረው ምክንያት ከሆኑ መካከል በአገልግሎት ወቅት ታማሚው ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ አንዱ ነው። ይህ እውነታ የጤና አገልግሎቶችን በአብዛኛው እየተጠቀመ ያለው የተሻለ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል።

አቶ ቢሆነኝ ምናለ የወንዶች አልባሳት በመሸጥ የሚተዳደር የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው። የታዘዘለትን መድኃኒት ጤና ጠቢያ በማጣቱ ውጭ ከሚገኝ የግል መድኃኒት መደብር በ600 ብር ገዝቶ ቢታከምም የጤና መድኅን ዋስትናው መድኃኒቱ ጤና ጣቢያ ይሸጥ በነበረበት ሂሳብ አስቦ 200 ብር ብቻ እንደተመለሰለት ነግሮናል። "ይህ ለምን ይሆናል?" ሲልም ይጠይቃል። “መድኃኒት ከውጪ ግዙ ብለው ካዘዙን በኋላ የገዛንበትን አይሰጡንም” ሲል አቤቱታውን አቅርቧል።

ሌላዋ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ወ/ሮ የሽወርቅ ተካ ትባላለች። ራሷን ጨምሮ ሦስት ልጆቿን የምታስተዳድረው እንጀራ በመሸጥ ነው።  የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን መጀመር እሷን እና ቤተሰቧን ስለመጥቀሙ ምስክርነት ሰጥታለች። ቅሬታም አላት። “ለህክምና ስንሄድ አንዳንድ ቦታዎች መስተንግዶው ላይ ችላ የማለት አዝማሚያ ዐያለሁ። ይህ ተገቢ አይደለም” ትላለች። እንዲስተካከልም ታሳስባለች።

በጤና ሚኒስቴር እ.አ.አ. በ2016/17 በተሰራው ብሔራዊ  የጤና  አካውንት  ጥናት  መሰረት  የነፍስ  ወከፍ  የጤና  አገልግሎት  ወጪ  በዓመት  32 ዶላር  ብቻ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት ካስቀመጠው 86  ዶላር  ጋር  ሲነጻጸር  እጅግ  ዝቅተኛ ነው።  ለጤና  አገልግሎት ተቋማት  የኢንሹራንስ ክፍያ ተቋማቱ የአገልግሎት ጥራትን እና መሰረተ ልማትን  የሚያሻሽሉበትን አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ስለመሆኑ ተነስቷል።

በሌላ በኩል በዚሁ ጥናት እንደተመለከተው ለጤና ከወጣው አጠቃላይ ወጪ 31  በመቶ  የሚሆነው  ተጠቃሚዎች  በአገልግሎት  ወቅት  በቀጥታ  ከኪሳቸው  የከፍሉት ነው። ይህም ግለሰቦች ለጤና አገልግሎት ከኪሳቸው የሚከፍሉት ከፍተኛ በመሆኑ በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ድህነት አረንቋ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።

ስለሆነም ሕብረተሰቡን ካልተጠበቀ ከፍተኛ የጤና ወጪ ከለላ በመስጠት ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር አንዲቻል የጤና መድኅን ሥርዓትን መዘርጋት አስፈላጊ ነው።

የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ቡድን አስተባባሪ አቶ አለበል ዓለሙ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ የጤና አገልግሎት ወጪ የሚሸፈንበት ሥርዓት ነው” ብለዋል። “የጤና ወጪ ስጋትን በመቅረፍና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ሁሉም እንደህመሙ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ነው። ሕብረተሰቡ የሚያዋጣውን አነስተኛ መዋጮ በአንድ ቋት በማሰባሰብ የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት ጤነኛው ታማሚውን፣ የታሻለ ገቢ ያለው አነስተኛ ገቢ ያለውን ተቀናጅቶ ዘላቂ የሆነ ጤናችንን መላበስ የምንችልበት መንገድ ነው” ይላሉ።

ጤና መድኅህን ያስፈለገበት ምክንያት አንድ ሰው በኪሱ ገንዘብ ሳይኖር የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል፣ የህክምና ወጪ ለመቀነስ እንዲያግዝ፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ መደጋገፍን እንዲያጎለብት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚነትን ስለሚያሳድግ ከእርዳታ ነፃ ለመውጣት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ማኅበረሰብ አቀፍ፣ ማኅበራዊ  እና  የግል  ጤና  መድህን  የሚባሉ  እንዳሉ  ገልጸው  በከተማችን  ከ2013  መጋቢት  ወር  ጀምሮ  ተግባራዊ  እየሆነ  ያለው  ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ነው። ለህዝቡ ተደራሽ የሆነውን፣ በመደበኛው  ክፍለ  ኢኮኖሚ  ያልተሰማሩትን  የማኅበረሰብ  ክፍሎች  ወይም  ያልተማሩትን  የቤተሰብ ክፍሎች ሊያቅፍ የሚችለውን ማህበረሰባዊ ጤና መድህንን ተግባራዊ እያደርጉ እንደሚገኙ ገልጸው በ2013 ዓ.ም. 35,125 ሰዎች፣ በ 2014  ከ  ጥር16-ይካቲት 1 ባለው ጊዜ ውስጥ በጤና መድህን 16,000 ሰው መመዝገባቸውንና ምዝገባው እስከ ይካቲት 15 ድረስ እንደሚቀጥል ገልጸው 24% አካባቢ  መመዝገባቸውንና በዘንድሮው እለት በ 15 ቀን ውስጥ  4.8 ሚልዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ከግለሰቦች ለቀረበባቸው ቅሬታ "በጎንደር ከተማ ውስጥ 8 ጤና ጣቢያዎች አሉ። በእነዚህ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንሰጣለን። ሪፈራል ለሚያስፈልጋቸውም አዲስ አበባ 8 ሆስፒታሎች ውል አለን። እዚያም ይታከማሉ። የመድኃኒት እጥረት ማንኛውም ሆስፒታል፣ ጤና ጣቢያ  እንደሚያጋጥመው  ሁሉ እነሱም  እያጋጠማቸው እንደሆነ ገልጸው ከጤና ጣቢያ ውጪ መድኃኒት ለመግዛት የሚሄዱ ካሉም ቀይ መስቀል እንዲገዙ የሚያደርጉ መሆናቸውንና ከግል ክሊኒክ ወይም መድኃኒት መደብር ለሚገዙ ደግሞ በመንግስት ተመን አማካኝነት የመድኃኒቱን ዋጋ እንደሚከፍሏቸው ተናግረዋል። ለምሳሌ አንድ መድሃኒት ከግል ድርጅት 600 ብር ቢገዙና በመንግስት ደረጃ 200 ብር ተመን ቢቀመጥለት እኛ በመንግስት ተመን መሰረት ትክ ክፍያ 200  ብር  ለገዢታው  እንመልሳለን"  የሚል  ምላሽ ሰጥተዋል።

መቼ እንደምንታመምና አደጋ እንደሚደርስብን ተገንዝበን ያልታሰበ ጤና ቀውስ እንደሚያስከትልና የኢኮኖሚ ቀውስንም እንደሚያመጣ አውቀን 1-5 ቤተሰብ 400 ብር፣ ከ6-7 ቤተሰብ 480 ብር፣ ከ8 እና ከዚያ በላይ 550  ብር  ለዓመት  ከፍሎ  መታከም  እንዲችል  ሁሉም  ሰው  የተቻለውን  አድርጎ  ዘላቂነት  እንዲመጣ ማድረግ መቻልና ማኅበረሰባችን  ጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አስተያየት