በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ አያሌ ቅርሶች በተለያዩ የኦንላይን መገበያያ አዉታሮች ላይ እየቀረቡ መሆኑ የቅርስ ዝርፊያ እና ህገ ወጥ ንግድ እንዳይባባስ ስጋት መፍጠሩን ኢንዲፔንደንት የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ዘገበ።
ጥንታዊ የብራና እና የተለያዩ የእጅ ፅሁፎች፣ ቅዱሳን መፃህፍት እንዲሁም በርካታ የእደ ጥበብ ውጤቶች ‘ኢቤይ’ን በመሳሰሉ የኦንላይን መገበያያ አውታሮች ለሽያጭ እየቀረቡ መሆኑን መረጃው አመላክቷል።
የመገበያያ አውታሮቹ ከእዚህ ቀደምም ከግለሰቦች እጅ የተገዙ ቅርሶች የሚገበያዩበት ቢሆንም፤ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ ቅርሶች በገበያው ላይ ተስፋፍተዋል። “አብዛኛዎቹ ቅርሶች በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል ከሚገኙ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች የተዘረፉ ናቸው” ብሏል የኢንዲፔንደንት ዘገባ።
ከ13ተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያየ እድሜ ያስቆጠሩት ቅርሶች እየተሸጡ የሚገኙትም ከአንድ መቶ ፓውንድ (6 ሺህ 900 ብር ገደማ) ባልበለጠ ገንዘብ ነው ተብሏል።
በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ማይክል ገርቬርስ እንደሚገልፁት፣ “ከትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ ከሚገኘው አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ብቻ 800 የሚደርሱ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ መዛግብት ተዘርፈዋል፤ እንዲሁም ጥንታዊው የነጃሺ መስጊድ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሶበታል”
የቋንቋ ተመራማሪ የሆኑት ሃጎስ አብርሃ ዘ ታይምስ ለተባለው የመረጃ ምንጭ እንደገለፁት፣ “በኦንላይን ግብይት ላይ እየቀረቡ የሚገኙት ቅርሶች በጦርነቱ ጊዜ የተዘረፉ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ላለፉት 6 ወራት በየቀኑ በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያ የሆኑ ቅርሶች በገበያው ላይ ተበራክተዋል”
ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው ‘ኢቤይ’ የተባለው የኦንላይን መገበያያ ምላሽ እንዲሰጥ ከተጠየቀ በኋላ ለሽያጭ አቅርቧቸው የነበሩ በርካታ ቅርሶችን ከገበያው አንስቷል። ኢቤይ በሰጠው ምላሽም “በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ ቅርሶችን ለገበያ ማቅረብ ዓለም አቀፍ ህጉም አይፈቅድም፤ እኛም አናደርገውም” ማለቱ ተገልጿል።