የካቲት 2 ፣ 2014

ነባሩ ጋቢ የማልበስ ባህል እና አዳዲስ ልማዶች

City: Adamaባህል

በኦሮሞ ፈረስ፣ ጋቢ፣ ጦር ክብርን ውዴታን ለመግለጽ ይሰጣሉ።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ነባሩ ጋቢ የማልበስ ባህል እና አዳዲስ ልማዶች

በተለይ በእድሜ ተለቅ ያለን እና በጋብቻ የተዛመዱትን ሰው ጋቢ ማልበስ በተለያዩ የኢትዮጵያ ባህሎች የተለመደ ነው። የኦሮሞ ህዝብም ፍቅሩን እና ክብሩን ሊገልጽለት ለፈለገው ሰው ጋቢ ያለብሳል። ጋቢ ማልበስ ትልቅ የክብር እና የፍቅር መገለጫ፤ ለለባሹ ያለን ትልቅ ቦታ የመግለጫ መንገድ ነው። እንደባህሉ አንድ ሰው ዘመዱን ጋቢ ቢያለብስ ውዴታውን፣ ባዳ ቢያብስ አክብሮቱን ለመግለጽ፣ ወዳጅነቱን መፈለጉን፣ ዝምድና መሻቱን ለማሳያ ይገለገልበታል። ፈረስ እና ጦር መስጠትም የክብር እና የውዴታ መግለጫ ሆኖ አገልግሏል።

ይህ ነባር ባህል እንደ ጊዜው ሁኔታ በተለያየ መንገድ ቀጥሏል። በአንድ ወገን የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በማመቻቸት በሌላ ወገን የመረዳዳት ባህልን እያዳበረ ይገኛል የሚሉ ሀሳቦች ይነሳሉ። በሌላ ወገን ከመሠረታዊ ባህሉ አፈንግጦ ባህሉን እየቆረቆዘ ነው የሚል ሌላ ጽንፍ ደግሞ ይሰማል።

ባሌ ሮቤ ከተማ ተወልዶ ያደገው ቡርሃን አህመድ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ነው። በተወለደበት አካባቢ ስለሚታየው የጋቢ ማልበስ ስርዓት አጫውቶናል። 

“በሰርግ ላይ ብርድ ልብስ ማልበስ የተለመደ ሆኗል” የሚለው ቡርሀን አህመድ የብርድ ልብስ ዋጋው ከጋቢ ከፍ ቢልም ጋቢ መስጠት ግን የትልቅ ክብር ማሳያ ነው ይላል።

“በባሌ አካባቢ ክብርን ለመግለጽ ለአያት፣ ለአማች፣ ለሀገር ሽማግሌ የሚሰጠው ጋቢ ነው” የሚለው ቡርሃን “በኦሮሞ ባህል አማች ወደ ልጁ ቤት አደጋ ካላጋጠመና ትልቅ ዝግጅት ካልኖረ በቀር ቅርብ እንኳን ቢሆን አይሄድም። እንዲህ ለብዙ ጊዜ ቆይቶ የሚመጣን አማች ለማክበር አባወራው ጋቢ ያለብሳል::" ይላል። "አማች የመጣበት ቀን ማታ ላይ የቤቱ አባ ወራ ከመንደር ሽማግሌ ፈልጎ ያዘጋጀውን ጋቢ አማቹን እንዲያለብስልት ይደርጋል” ሲል ባደገበት አካባቢ የተመለከተውን ነግሮናል። “ይህ ሲደረግ አማች መከበሩን እና መመስገኑን ያሳያል” ሲል ነግሮናል።

በአዳማ በግል ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ኢብሳ ጉተማ ተወልዶ ያደገው ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ነው። ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ጋቢ ትልቅ ክብር እንዳለው ይናገራል። "ጋቢ ገዝተህ መልበስ ትችላለህ፡፡ ስጦታ ሲሰጥህ ግን ትርጉሙ ትልቅ ነው" ይላል።

"አባቴ 8 ጋቢ አለው። ሁለት ታላላቆቼ ሲያገቡ እንዲሁም ሌሎች ዘመዶቻችን ሲያገቡ ያለበሱት ነው። ጋቢ መልበስ የሀብት መለኪያ ሳይሆን የፍቅር እና የክብር መገለጫ ነው” ሲል ባደገበት አካባቢ የተመለከተውን ነግሮናል። "ጋቢ ማልበስ ላለፈ መልካምነትም ማመስገኛ ነው" የሚለው ኢብሳ አሁን ላይ የሚታየው ነገር ግን ለገንዘብ አልያም ሌላ ጥቅም ፍለጋ ጋቢ ማልበስ እየተለመደ መምጣቱን ነግሮናል።

“በኦሮሞ ፈረስ፣ ጋቢ፣ ጦር ክብርን ውዴታን ለመግለጽ ይሰጣሉ። በተለይ ወደ ጅማ አካባቢ ደግሞ በርጩማም ከሌሎቹ ስጦታዎች ጋር ይሰጣል” ሲል ያጫወተን ሙባረክ ሱልጣን ነው። ወደ ጅማ እና ኢሉ አባ ቦራ አካባቢዎች ይህ በስፋት እንደሚስተዋል ነግሮናል።

ደጀኔ ጋዲሳ የቋንቋ እና የሶሺዮሎጂ ባለሞያ ነው። "ጋቢ ነጭ ነው። ነጭ ደግሞ የስኬት፣ ደስታ፣ የፍቅር ምልክት ነው። ጋቢ ደግሞ ድርብ ነው። ድርብ ነህ፤ ጠንካራ ነህ፣ ብርቱ ነህ የሚል ተምሳሌት አለው።" ብሎናል።

"ጋቢ የሚያለብስ ሰው ጉዞው ዘመድ፣ ወገን ፍለጋ ነው።"  የሚለው ደጀኔ ጋዲሳ በዚህ ውስጥ ሰውየው ችግር ቢገጥመው ደስታ ቢኖር ከጀርባው ማን አለ? እነማን የእርሱ ወገን ናቸው የሚለውን የሚያሳይ ስለመሆኑ ይናገራል። 

 በአዳማ ከተማ በአሁን ወቅት የተለያዩ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎች ሲመረቁ ይህ ዓይነት ባህል እየተለመደ መጥቷል። የንግድ ቤቱን የሚከፍተው ሰው በተለያየ መመዘኛ ሰዎችን መርጦ ጋቢ ያለብሳል። ከእነኚህም መሀከል ሀብት፣ ታዋቂነት፣ መሰል መስፈርቶች ይኖራሉ። እነኚህ ጋቢ የለበሱ ሰዎችም በእለቱ ጓደኞቻየውን፣ ወዳጆቻቸውን እና ቤተሰባቸውን ሰብስበው ወደ ጥሪው ቦታ ይሄዳሉ።

አዳማ ላይ ይህ ስርዓት ሲጀመር ከጀማሪዎቹ አንዱ እንደሆነ የሚናገረው ደረጀ ጉቱ የቄሮ ባር እና ሬስቶራንት ባለቤት ነው። ቅድሚያ መነሻው እንዴት እንደነበር አውግቶናል።

በ2011 ዓ.ም. ሱሉልታ ከተማ ለጓደኛው ሆቴል ምርቃት ሄዶ ይህንን ባህል እንደተመለከተ ያስታውሳል። ከዚያም ሌላ አዳማ ከሚኖር ባለሆቴል ጓደኛው ጋር ተማክረው እንደጀመሩት ይናገራል።

“በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. ሬስቶራንቴን ለማስመረቅ ለ25 ሰዎች ከወዳጆቼ ጋር ሆኜ ጋቢ አልብሻለሁ። አንድ ጋቢ የለበሰ ሰው በስሩ ቢያንስ 20 ቢበዛ 50 ሰው ይዞ ይመጣል” ይላል።

"መጀመሪያ ላይ ጋቢ እና ውስኪ ይዘን ሰዎች ጋር ስንሄድ ልጅ ለትዳር ጥየቃ መስሏቸው የሚደነግጡ ነበሩ" የሚለው ደረጀ ጉቱ ጋቢን ለሆቴል ምርቃት ማልበስ ብዙዎችን አስገርሟቸው እንደነበር ያስታውሳል።

"ጋቢ ማልበስ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለህን ደረጃ ፍንትው አድርጎ ያሳያል" የሚለው ደረጀ አንድ ሰው ምን ያህል ወዳጆች፣ ለምን ያክል ሰዎች ውለታ እንደዋለ፣ ተወዳጅነቱን ይገልጽበታል። የወዳጁ ሆቴል ምርቃት ላይ የተፈጠረውን የሚያስታውሰው ደረጀ አንድ ስዕል በ550 ሺህ ብር ከጓደኞቹ ጋር በጋራ መግዛታቸውን አስታውሶ ይህንን ያደረጉት ጓደኛቸውን ለማገዝ እንደሆነ ይገልጻል።

"አሁን ያለው ጋቢ ማልበስ ቀድሞ ከነበረው ባህል የራቀ ነው። ኑ መርቁልኝ፣ አግዙኝ ወጪ አድክሞኛል ብለህ ነው ሰው ደጅ ምትጠናው" ያለን ደረጀ አሁን ፈሩን እንደለቀቀ ይሰማዋል። እስከ 120 ሰው ያለበሱ ሰዎች እንደገጠሙት እና ተመርቀው ወር ሳይሰሩ የተዘጉ ቤቶች ማየቱን በትዝብቱ ነግሮናል።

ይህ ደግሞ ባህሉ በብዙ ሰዎች በጥርጣሬ እንዲታይ፣ እንዲጠላ በማድረግ ሰዎች ሲመረሩበት መመልከቱን ነግሮናል። “ሁሉም ወደፈለገበት እየወሰደው ነው” የሚለው ደረጀ በጥበብ ስራዎችም ላይ እያስተዋለው እንደሆነም ነግሮናል።

የዙሩባቤል አበበ የኬቲ ፋሽን ባለቤት ነው። ስለጋቢ ማልበስ ሲናገር "ጋቢ ምታለብሰው አለኝ የምትለውን ሰው ነው። ይህ ባህል የቆየ መሠረት አለው። በገጠሩ ክፍል ቤት የሰራ ሰው ይጠቀምበት ነበር። አሁን ወደ ከተሞች መጥቷል። አንድ ሰው አንድ ቤት ሲሰራ፣ ከፍ ያለ ወጪ ሲያወጣ ለወዳጅ ዘመዱ የኔ ለሚለው ሰው አግዙኝ ይላል። ሰውም የተለያዩ ቤት መስሪያ እንጨት፣ የጣሪያ ክዳን ሳር ይዞ ሄዶ ያግዛል ይላል።

"አሁን ደግሞ በከተሞች ለወዳጆቹ ቀጠሮ እየሰጠ ጋቢ ያለብሳል። ይህ ጋቢ የለበሰ ሰው ደግሞ ጋቢ ለብሻለሁ ብሎ ወዳጆቹን ነግሮ የአቅማቸውን አዋጥተው እንዲያጅቡት ይጠይቃቸዋል” የሚለው ዘሩባቤል ከዚህ ቀደም አንድ ጋቢ የለበሰ ወዳጁን አጅቦ መሄዱን አስታውሶ ለስጦታ ትልቅ ሙክት እና ለተመረቀው ቤት የሚሆን የግድግዳ ስዕል መውሰዳቸውን ይናገራል።

"ይህ ባህል ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የኢኮኖሚያዊ መደጋገፍን ለማምጣቱ ትሩፋቱ ብዙ ነው። ይህንን የመሰለ መደጋገፍ ተደርጎ ቤቶችን ካስመረቁ በኋላ ሳይሰነብቱ መዘጋት እና መጥፋት ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው” ብሏል።

ባህሉ ጋቢ ማልበስ ከሬስቶራንት ምርቃቶች እና አዲስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምርቃት በዘለለ ወደ ጥበብ ስራም እየገባ እንደሆነ ይናገራል። “የሙዚቃ ቪዲዮ እና አልበም የሚያስመርቁ ሰዎች ጋቢ ማልበስ ጀምረዋል” የሚለው ዮሚዩ ሳምሶን የሙዚቃ ባለሞያ ነው። ይህ ባህል ወደ ሌላ የተለየ አቅጣጫ እየሄደ ነው ከሚሉት መካከል ነው።  ሙዚቃ እያስመረቁ ያሉ ድምጻዊያን ይህንን መንገድ ሲከተሉ ይታያል። ከዚህ በፊት አንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ በአዳማ የሙዚቃ ቪዲዮውን ሲያስመርቅ የተለያዩ ሰዎችን ጋቢ አልብሶ እንደነበር አስታውሶ ነባሩን ባህል አዲሱ ትውልድ በራሱ መንገድ እያስኬደው እንደሚገኝ መታዘቡን ነግሮናል።

አስተያየት