የካቲት 4 ፣ 2014

የድሬደዋ ባለውለታ አቶ መርሻ ናሁሰናይ

City: Dire Dawaታሪክ

ከሠላሳ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረው በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬደዋ ባለውለታ አቶ መርሻ ናሁሰናይ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

በድሬደዋ ከተማ “ደቻቱ” የሚል መጠሪያ ያለው የመኖርያ ሰፈር “ገንደ መርሻ” (መርሻ ሰፈር) እየተባለ ይጠራ እንደነበር ታሪክ አዋቂዎች ይመሰክራሉ። አቶ መርሻ ናሁሰናይ ለድሬዳዋ ከተማ መመስረት ባበረከቱት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ለውለታቸው የተበረከተ ነበር። አሁን  በጊዜ ሂደት እየተዳከመ መጥቶ ጠፍቷል። አቶ መርሻ ዘመናዊ የአስተዳደር ዘዬዎችን፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የምድር ባቡርና የመሳሰሉት መጓጓዣዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ረገድ ከፍ ያለ ሚና ስለመጫወታቸው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ከሠላሳ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረው በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

የአስተዳደር ኃላፊነት ተረክበው መስራት የጀመሩት ከተወለዱበት ሸዋ ወደ ሀረር አቅንተው ኑሯቸውን ከመሰረቱ በኋላ ነው። ሀረር ከተማ ኑሮን ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት በኋላ በከተማዋ የፀጥታ ፖሊስ ኃይል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ከዚያም “ጀልዴሳ” የምትባለው ታሪካዊ ከተማና አካባቢዋ አስተዳዳሪ ሆነዋል። በአሁን ሰዓት ሱማሌ ክልል የምትገኘው”ጀልዴሳ” በወቅቱ ሸዋን ጨምሮ የተቀሩትን የኢትዮጵያ ክፍሎች ከቀይ ባህርና ከገልፍ ኦፍ ኤደን ጋር የሚያገናኘው የካራቫን ንግድ መተላለፊያ ነበረች። ከኢትዮጵያ የድንበር ክልል እስከ አዋሽ ያለውን አካባቢ በሙሉ ያስተዳድሩ እንደነበር ይነገራል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይ እና ከጣልያን ሶማሌ ላንድ ጋር ትዋሰን ነበር። ከአፀፄ ሚኒልክ ቀዳሚ ዓላማዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያን ወሰን መከለልና ማስከበር ስለነበር አቶ መርሻ በተደረገው ጥረት ተሳትፈዋል እንዲሁም በድንበርና እና አካባቢ ጥበቃ ሚና እንደነበራቸው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

አቶ መርሻ የጄልደሳ ጉምሩክ ኃላፊ ስለነበሩ ወደ ሀገሪቱ የሚወጣውና የሚገባውን ሁሉ በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር። ሸቀጦች ዘይላ በተባለው የእንግሊዝ ሶማሌ ላንድ ወደብና በጅቡቲ ፈረንሳይ ሶማሌላንድ በኩል እንደልብ ይገቡና ይወጡ ስለነበር ከተማዋ በንግዱ ዓለም ታዋቂ ሆና ነበር። ለምሳሌ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ብሪታንያ በ1897 እ.ኤ.አ በፈረሙት ዲፕሎማሲያዊ ውል አንቀፅ ሦስት መሰረት ጀልዴሳ ለሁለቱም ሀገሮች ንግድ ክፍት እንድትሆን ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ትሪፕል ትሪቲ የታሪክ ማስረጃ ነው። የካራቫን ነጋዴዎች እና መንገደኞች ጀልዴሳ ሲደርሱ ከሀገር ውጪ ያመጧቸውን ግመሎችና በቅሎዎች ወደመጡበት ልከው ለቀጣዩ ሀገር ውስጥ ጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን እንሰሳት ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዲከራዩ ይደረግ ነበር። የጅቡቲ ወደብ መከፈት ለጀልዴሳ ጉምሩክ መጠናከርና የንግድ መስፋፋት ከፍተኛ እርዳታ አድርጓል። አቶ መርሻም ለስራ ወደ ጅቡቲ ይመላለሱ ነበር።

በ1902 እኤአ ድሬደዋ ስትቆረቆር የከተማውና አካባቢዋ አስተዳዳሪና የድሬደዋ ጉምሩክ የመጀመሪያው ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። በ1894 አፄ ሚኒልክ የምደር ባቡርን ወደኢትዮጵያ እንዲገባ ከተስማሙ በኋላ የቅርብ አማካሪዎቻቸው የሆኑት አልፍሬድ ኢልግ እና ፈረንሳዊው ሌዎን ሸፍነ ለሀዲዱ የሚያስፈልገውን ስራ ጀመሩ። የምድር ባቡር ኩባንያም በአስቸኳይ ተቋቋመ። የባቡር ሃዲዱ ስራ በ1897 እ.ኤ.አ ሲጀመር አቶ መርሻ ከኢትዮጵያ በኩል በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት ተቀበሉ። ፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገራቸው ኃላፊነቱ እንዲጣልባቸው እንዳደረገ ይነገራል። በ1900 ሀዲዱ ከጅቡቲ ተነስቶ ደወሌ ሲደርስ በተደረገው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ አፄ ሚኒልክን ወክለው ተገኝተዋል። የሀዲድ ግንባታው ለሰባት ዓመት ተቋርጦ እንደገና ሲጀመር በድጋሚ በበላይነት ኃላፊ ሆነው እንዲያስተዳድሩ ስልጣኑ ለአቶ መርሻ ተሰጣቸው።

ከጅቡቲ የተነሳው ሀዲድ በአሁን ሰዓት ድሬደዋ ከተማ “ሼማንደፈር” እየተባለ በሚጠራው የመጀመሪያው ሕንፃ አካባቢ ሲደርስ አንድ ጣቢያ እንደሰራ ተደረገ። የጣቢያው መገንባት ለድሬደዋ መቆርቆር ምክንያት ሆነ። አቶ መርሻም የድሬደዋ የመጀመሪያ መሪ ሆኑ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ ከተማ ተቋቋመ። አቶ መርሻ እስከ 1906 በአስተዳዳሪነት አገለገሉ። ከዚያም ለሀያ ዓመታት የኢሳ ግዛቶችና የባቡር ሀዲዱ የበላይ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።    

ከዓድዋ ድል በኋላ በርካታ የውጪ መልዕክተኞችና እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ በጀልዴሳና በድሬደዋ አስተዳደሪነታቸው የማስተናገድ ዕድል ያገኙና ኢትዮጵያ በቀና መልክ ዕንድትታይ ልዩ ጥረት ያደረጉ ናቸው።  

አቶ መርሻ ወ/ሮ ትደነቂያለሽ መክብብን አግብተው አስራ አንድ ልጆችን ወልደዋል። የአቶ መርሻ የበኩር ልጅ ባላንበራስ በየነ የእቴጌ መነን የሴቶች ት/ቤት ሲከፈት የመጀመሪያው ዳሬክተር ነበር። ከደሴ ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ ሲሰራ በኃላፊነት መርቷል። የሶማሌ ክልል ድርድር ሲጀመር ሀገራቸውን ወክለው በኮሚቴ ጸሐፊነት ተሳትፈዋል። በአሁኑ ጊዜ በህይወት ካሉት የልጅ ልጆቹ መካከል አቶ አብነት በአዲስ አበባ የታወቁ የንግድ ሰውና በጎ አድራጊ ነው።

የድሬደዋ መስራችና ባለውለታ አቶ መርሻ ናሁሰናይ በሰማንያ አምስት ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም በ1937 እ.ኤ.አ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ስነስረዓታቸውም በሀረር ከተማ ተፈጽሟል።

አስተያየት