የህዝብ ብዛቷ ከ3መቶ ሺህ በላይ የሚገመተው ባህርዳር ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ)ን ጨምሮ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ (ሚኒባስ)፣ ለመንግሥት ተቋማት የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶች፣ ለመንግሥት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ 12 አውቶብሶች፣ አልፎ አልፎ ብስክሌት የከተማዋ የትራንስፖርት አማራጮች ናቸው። በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ 6ሺህ ባለ ሦስት እግር ተሽርካሪዎች (ባጃጅ) ሲኖሩ ያለ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱትን ሲጨምር ቁጥሩ ከ6ሺህ ይልቃል። ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው በከተማዋ ከ12 በላይ በሚሆኑ የባጃጅ ማኅበራት የተደራጁ ከ6ሺህ በላይ ሕጋዊ ባጃጆች አሉ። ባጃጆቹ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲያቋርጡ ውሳኔ ተላልፏል። የባጃጆቹ አሽከርካሪዎች በበጎ ያልተቀበሉት ይህ ውሳኔ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጾች እያስተናገደ ይገኛል።
ተስፋዓለም ታደሰ የባጃጅ አሽከርካሪ ነው። ለስድስት ዓመታት የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ራሱን አስተዳድሯል። የከተማ አስተዳደሩን ውሳኔ በተመለከተ "ድንገተኛና ያልታሰበ ነው" ይለዋል። ውሳኔው ድሀውን የሕብረተሰብ ክፍል ያለማከለ ስለመሆኑ ደጋግሞ አንስቷል። ውሳኔውን ሰርቶ የመብላት መብትን መነፈግ እንደሆነ በመቁጠር ይኮንነዋል።
ሌላው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪ ታደሰ ሙላት የሚያሽከረክረውን ባጃጅ በቀን ገቢ ተከራይቶ እንደሚሰራ ይናገራል። “ለባለቤቱ በቀን 2መቶ ብር ማስገባት ይጠበቅብኛል” የሚለው ታደሰ የራሱን የቀን ገቢ እና የዕለት ወጪ ሳይጨምር ይህንን ያህል ብር ለማግኘት በርትቶ መስራት ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም አዲሱ ውሳኔ ሥራውን እንዲያቆም ሊያስገድደው እንደሚችል ስጋቱን ገልጾአል።
ለእለት ለእለት የትራንስፖርት አማራጫቸውን ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ካደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው ዘሪሁን ይልማ “የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ተገቢ ነው” ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ በከተማው ዋና ጎዳና ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ይቀንሳል ብሎ ማመኑ ነው። ይሁን እንጂ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ላይ የሚኖረውን የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት መንግሥት ከወዲሁ ሊያስብበት እንደሚገባ አሳስቧል።
የባህር ዳር ከተማ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ በቀለ ባጃጆችን ከዋና ዋና ጎዳና የማስወጣት ወሳኔ ከሁለት ዓመት በፊት በከንቲባ ከሚቴ የተወሰነ ስለመሆኑ ተናግረዋል። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጥናት ሲደረግ ቆይቶ አሁን ውሳኔውን የማስፈፀም ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ውሳኔው የተላለፈው የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ነው። በተመሳሳይ የደንብ ጥሰት እና ለትራፊክ ሕግ ተገዢ አለመሆን ጉዳይ ተበራክቷል። ውሳኔው ይህንን እና ይህንን መሰል ቅሬታዎች መልክ ለማስያዝ ተላልፏል። “ውሳኔው ድንገተኛ ሳይሆን ከባጃጅ ማኅበራት ጋር ውይይት የተደረገበት ነው" በማለት ሂደቱን አስረድተዋል።
ከውሳኔው ጋር በተያያዘ በባጃጅ አሽከርካሪዎች ዘንድ መንገድ ማቋረጥን የተመለከተ ጥያቄና በተገልጋዩ ዘንድ ደግሞ የትራንስፖርት እጥረት ስጋት ይነሳል። ኃላፊው አቶ ስንታየው ጉዳዩን አሰመልክተው ሲናገሩ “ከዋናው መንገድ በመውጣታቸው የሚፈጠረውን የትራንስፖርት እጥረት ለማሻሻል እየሰራን ነው። የባጃጅ አሽከርካሪዎቹ ማቋረጫ መንገድን የተመለከተው ጥያቄም በሂደት መፍትሄ ያገኛል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“የከተማዋ ባጃጆች ከሰሞነኛው ወሳኔ በፊት ነዋሪውን በፈለገው ሰዓት ከፈለገው ቦታ በማድረሳቸው የሚወደሱትን ያህል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚኮነኑበት ነገር አለ” የሚሉ በርካታ ናቸው። ባጃጆቹ የጉዞ ክፍያ የታሪፍን አለማክበራቸው፣ ተጠቃሚው ተገዶ ወይም አማራጭ አጥቶ ከፍ ባለ ብር በኮንትራት እንዲጓዝ መደረጉ የከተማውን ነዋሪ እንዳማረረ ከነዋሪዎች መረዳት ይቻላል።
ቅሬታውን በተመለከተ ተስፋዓለም ሲያስረዳ "በኮንትራት መስራት የተሻለ ትርፍ ስለሚያስገኝ፤ የኮንትራት ተሳፋሪን እመርጣለሁ” ይላል። “ቀኑን መሉ ሲሽከረከሩ ከመዋል አመቺ በሆነ ቦታ ኮንትራት የሚጠቀም ሰው መጠበቅ” እንደ ቢዝነስ አዋጭ እንደሆነ ያክላል። "የነዳጅ እጥረት በከተማ አለ። በጥቁር ገበያ ስለምገዛ ትርፍ ለማግኘት የኮንትራት እሰራለሁ" ይላል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ይገረም በበኩሉ ”የከተማዋ ታክሲዎች በሀሉም የከተማዋ መኖሪያ መንደሮች ተደራሽ አይደሉም” ይላል። እንደ ይገረም ሐሳብ ባጃጆች በየመንደሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በመግባት ከምሽት እስከ ንጋት አገልግሎት ይሰጣሉ። “ታሪፉን የመቆጣጠር እና ሕግ የማስከበሩ ሥራ ግን የመንግሥት ነው። ክልከላ መፍትሔ አይሆንም” ሲል ሐሳቡን ይደመድማል።
ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት በከተማዋ የሚስተዋለውን ከታሪፍ ጋር የተያያዘ እና ሌሎች የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ የሕብረተሰቡ ተባባሪ አመሆን እንዳለበት አመላክቷል። ችግሮችን ለመቅረፍ ከማኅበራቱ ጋር ምክክር እንደሚደረግ ለማወቅ ችለናል። ባጃጆች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ብቻ መወሰናቸው የነዳጅ ብክነት ነው የሚሉት ወገኖች ደግሞ ባጃጆች ከሌሎቹ ተሽከርካሪዎች አንጻር ባነሰ የነዳጅ መጠን የበዛ ኪሎሜትር መጓዛቸውን በማንሳት ሥርአት ተበጅቶ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።