ከ100 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ አየር ሃይል በግዳጅ ላይ!!” በማለት ሁለት ተመሳሳይ ምስሎችን በመስከረም 2 ፣ 2014 ዓ.ም አጋርቷል። ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖችን ጨምሮ ልጥፉ ከ160 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይሁን እንጂ ሃቅቼክ ምስሎቹን አጣርቶ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
ከህዳር 2012 ዓ.ም አንስቶ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ልጥፎች መካከል ይህ አንዱ ነው። ጦርነቱ የተጀመረው የሕውሃት ሃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ራሱን የመከላከል እርምጃ በማለት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመወሰዱ ነው። ግጭቱ መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድሮኖችን መጠቀም መጀመሩን እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቱ አየር ሃይል ዘመናዊ የጦር ድሮኖችን እየተጠቀመ መሆኑን አስታውቋል። ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎችም የወታደራዊ እርምጃዎች እንደቀጠሉ ይገኛሉ።
ሆኖም የጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ምስሉ ሰኔ 8 ፣ 2009 ዓ.ም በተለቀቀ የዩቲዩብ ቪዲዮ ላይ ይገኛል። ቪዲዮው “የኔቶ ሃይሎች በምን ያህል ፍጥነት ግዳጃቸውን ይፈጽማሉ? የኔቶ ሃይሎች በሮማኒያ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ” የሚል አርዕስት ያለው ሲሆን ከ15 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተቀረጸው በሮማኒያ ውስጥ “Exercise noble jump 17” በተባለ የወታደራዊ ልምምድ ወቅት ነው።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አየር ሃይል በሕውሃት ሃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ቢያሳዩም ይህ ምስል የኢትዮጵያ አየር ሃይል እርምጃ ሲወስድ አያሳይም። ስለሆነም በፌስቡክ ገጹ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል ሀሰት ነው።