መስከረም 14 ፣ 2014

በድምጽ ብክለት የምትታመሰው አዳማ ከተማ

City: Adamaመልካም አስተዳደርማህበራዊ ጉዳዮች

የአካባቢ ብክለት በማስከተል የሰዎችን መኖርያ ከሚያውኩ ነገሮች መካከል ድምጽ አንዱ ነው። ከእምነት ተቋማት፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎችና ሌሎች ሰዎች የተረጋጋ ኑሮ መኖር እንዳይችሉ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሕግ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በድምጽ ብክለት የምትታመሰው አዳማ ከተማ

የአካባቢ ብክለት በማስከተል የሰዎችን መኖርያ ከሚያውኩ ነገሮች መካከል ድምጽ አንዱ ነው። በካይ ጋዞችን፣ የቆሻሻ ሽታን ጨምሮ ሰዎች የተረጋጋ ኑሮ መኖር እንዳይችሉ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሕግ ገደብ ተጥሎባቸዋል። በዋናነት የድምጽ ብክለት ምንጮች ተብለው የተዘረዘሩት ከእምነት ተቋማት፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ከትራፊክ እንቅስቃሴ፣ ከግንባታ ሥፍራ የሚወጣው ከፍ ያለ መጠን ያለው ድምጽ ነው። ማሽኖች በሥራ ሂደት የሚያወጡት ራቅ ካለ ሥፍራ የሚደመጥ ድምጽም እነዚህ ውስጥ ያካተታል።

ከአዲስ አበባ በ100 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው አዳማ የድምጽ ብክለት ከተባባሰባቸው መካከል የምትመደብ ከተማ ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም። በከተማዋ አውራ ጎዳናዎች የተዘዋወረ ማንኛውም ሰው ከንግድ ማዕከላት፣ ከካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ ከፍ ባለ ድምጽ በመኪና በመዘዋወር ከሚነገሩ ማስታወቂያዎች፣ አላግባብ ከሚለቀቁ የመኪና ጥሩምባዎች፣ ከእምነት ተቋማት፣ ከመዝሙር እና ሙዚቃ መሸጫ ቤቶች፣ ከብየዳና ብረት ቤቶች፣ ከፊልም ማከራያ ሱቆች፣ ከኢንተርኔት ቤቶች፣ ከቋንቋና መሰል ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ከፑል እና ከረምቡላ ማጫወቻዎች፣ በየመንገዱ እየተዘዋወሩ ከሚሰብኩ የሐይማኖት ሰዎች፣… የሚወጣ ድብልቅ ድምጽ ይረብሸዋል።

በአዳማ ከተማ ተዘዋውሮ ድምጽ በካይ አካባቢዎችን የቃኘው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ሶሬቲ ሲቲ ሞል ላይ ከፍ ያለ ሙዚቃ የሚያጫውተውን የፑል ማጫወቻ ባለቤት አነጋግሯል። የሱቁ ባለቤት ወጣት ወንደሰን ሞላ “4ኛ ፎቅ ላይ ስላለን እዚህ መኖራችንን ለተጠቃሚ ለማሳወቅ እና  ትኩረት ለመሳብ ግዴታ ሙዚቃ እና ማስታወቂያ መልቀቅ አለብን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ከሥራ ቦታው የሚወጣው ከፍ ያለ ድምጽ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችን ረብሾ እንደሆነ ለጠየቅነው ሲመልስ “አሁን ተሻሻሽሏል” ብሎናል። ሥራ በጀመረ ሰሞን በርካታ ሰዎች ቅሬታ ስላሰሙ ድምጹን መጠነኛ በማድረግ ደንበኞቹን ለመሳብ በመጣር ላይ እንደሚገኝ ነግሮናል።

ጀርመን ሞል የልጆች አልባሳት መሸጫ ሱቅ ውስጥ የምትሰራው ሀውለት ከድር በበኩሏ “እኔ ካለሁበት ሕንጻ አጠገብ ከሚገኝ ህንጻ  የሚመጣው ድምጽ በጣም ይረብሻል። ጩኸቱ ከደንበኞቼ ጋር አላደማምጥ ስለሚለኝ በር ዘግቼ ለመስራት ተገድጃለሁ” ስትል ምሬቷን አሰቀምጣለች። “በረብሻው የተነሳ ለከፍተኛ ራስ ምታት እና ለእንቅልፍ ማጣት ተዳርጌአለሁ” ብላለች።

በከተማዋ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸው የድምጽ ብክለት ምንጮች ማስታወቂያዎች እና ስብከቶች ናቸው። “መኪና ላይ በጫኑት ከፍተኛ መጠን ያለው ድምጽ የሚያወጣ ድምጽ ማጉያ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ተቋማት ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። በቀን ውስጥ ከ10 በላይ መቁጠር ይቻላል። የጸረ-ተባይ፣ የኮስሞቲክስ፣ ቁሳቁሶች የብዙ ነገሮች ማስታወቂያ በየመንገዱ ይነገራል።” የሚለው ፈቃደ ተማም “ለመቁጥር የሚያታክቱ የሐይማኖት ሰባኪዎች አነስተኛ ድምጽ ማጉያ በመያዝ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ላይ በርከት ብለው ይገኛሉ። ይሄም በጣም የሚረብሽ ነገር ነው” ሲል ምሬቱን ነግሮናል።

መሰለ ማሞ በከተማው ውስጥ በመኪና የድምጽ ማስታወቂያዎችን በመስራት ይታወቃል። ከድምጽ ብክለቱ ጋር ተያይዞ ስለሚነሳው የህዝብ ቅሬታ ጉዳይ አንስተን ለጠየቅነው ጥያቄ “የድምጽ መጠናችንን በአካባቢ ጥበቃ ቢሮ የተወሰነ ነው። ሆኖም ክፍት ቦታ በመስራታችን መስተጋባቱ፣ ከምንጠቀማቸው መሳሪያዎች አሰራር የድምጽ መብዛት ሊኖር ይችላል” ብሎናል።

የህክምና ባለሞያው ዶ/ር ታሪኩ ገለሼ የድምጽ ብክለት “ከእርጅና በፊት የመስማት ችሎታ ከመቀነሱ ሌላ ለጭንቀት፣ ለልብ ህመም እና ከልብ ህመም ጋር ተያያዥ ለሆኑ አፋጣኝ ሞቶች ያጋልጣል።” ብለዋል። አክለውም የድምጽ ብክለት እረፍት /እንቅልፍ/ በማዛባት የመንፈስ መረበሽ እና ያለመጠን መሸበር በማስከተል ለአዕምሮ ጤና መዛባት እና ለአዕምሮ ህመም መጋለጥ አስተዋፅዖ ያደርጋል። የተረጋጋ ሰብዕና በማሳጣት በስራ እና በእለት ተእለት ኑሮ ላይ ጫና ያሳድራል። ከፍ እያለ ሲሄድም የኅብረተሰብ ጤና ስጋት የመሆን አቅም እንዳለውም ነግረውናል።

በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ምኒልክ ሰርጹ በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 44 ላይ የአካባቢ ደህንነት መብት በሚለው ዝርዝር ውስጥ “ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው።” ብሎ በግልጽ ያስቀምጣል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርን ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 177/2005 ዓ.ም.ን አውጥቷል። አዋጁ ማንኛውም ሰው ከተቀመጠለት የድምጽ መጠን በላይ የሚያወጣ መሳሪያ በመጠቀም በሰው እና አካባቢ ላይ ተጽዕኖ ወይም ጉዳት ማስከተል እንደሌለበት አስቀምጧል። በዚህም መሰረት የድምጽ ክልሎችን የጸጥታ፣ የመኖርያ፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ በሚል ከፋፍሎ አስቀምጧቸዋል። ቦታዎቹ በደምጽ መጠን መለኪያ ዴሲ ቤል መሰረት በቀን እና በምሽት ሊኖራቸው የሚገባውን የድምጽ መጠን ገድቧል። በዚህም መሰረት ለጸጥታ ቦታዎች ለቀን ከ55 ዴሲቤል በታል ለምሽት ከ45 ዴሲ ቤል በታች መሆን እንደሚገባው አስቀምጧል። ለመኖርያ በቀን 65 በምሽት 55 ሲሆን ለንግድና ኢንዱስትሪ አካባቢዎች ደግሞ ለቀን 75 ለምሽት 70 እንዲሆን አስቀምጧል።

ከተማዋን ከፍ ባለ ድምጽ በማወክ ላይ የሚገኘው ድምጽ ሁለት ክፍል ሊመደብ የሚችል ስለመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰርጓለም አብቧል ይናገራሉ። “የመጀመሪያዎቹ የቁጥጥር ደንብ በማውጣትና ጥብቅ ክትትል በማካሄድ የሚቀንሱ ወይም የሚጠፉ ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከመኖርያ አካባቢዎች የራቀ የራሳቸው ሥፍራ እንዲኖራቸው በማድረግ ሰዎችን እንዳይረብሹ ማድረግ ይቻላል።” የሚሉት ባለሙያው ከሙዚቃ ቤቶች እና ከሌሎችም ተቋማት የሚወጣው ድምጽ እንዲገደብና በማይረብሽ መልኩ እንዲከፈት ማድረግ ይቻላል። ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡት ሱቆች በተጠና መንገድ ራቅ ራቅ ብለው ሳይጠጋጉ እንዲገኙ ማስቻል ሌላኛው መንገድ ስለመሆኑ አብራርተዋል። እንደ እንጨት ቤት፣ ብረት ቤት፣ ጋራዥ ያሉ የሥራ ቦታዎች የሚወጣውን በካይ ድምጽ ለመከላከልም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡት ቦታዎች ሰዎች ከሚበዙባቸው የመኖርያ አካባቢዎች እንዲርቁና በቻሉት ሁሉ አነስተኛ ድምጽ የሚያወጣ አሰራር እንዲከተሉ ማድረግ ይቻላል።

በጨፌ ኦሮሚያ አዋጅ 177/2005 ዓ.ም. መሰረት ለሚፈጸም ብክለቶች ግለሰብ የድምጽ ብክለት ገደቡን ተላልፎ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ በገንዘብ ከብር ከ1,000 ባላነሰ እና ከ5,000 በማይበልጥ በመቀጮ ወይም በእስራት ከ1 ዓመት ባላነሰ ከ10 ዓመት ባልበለጠ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል። ጥፋተኛው የሕግ ሰውነት የተሰጠው (ተቋም) ከሆነ ደግሞ ከብር 5,000 እስከ 25,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይጣልበታል። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ከ5 እስከ 10 ዓመት እስራት ወይም ከብር 5,000 እስከ 10,000 በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ደንግጓል።

ሪፖርተራችን ያገናነራቸው የከተማው የተፈጥሮ፣ የደን እና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ የአገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ጫላ ሴያ ለመኪና ማስታወቂያ በስታንዳርዱ መሰረት ለንግድ ቦታዎች ቀን ላይ በተፈቀደው ጣራ መጠን 65 ዴሲ ቤል ነው የምንሰጠው ነገር ግን ከተፈቀደው የድምጽ መጠን፣ ጊዜ እና ቦታ ውጪ የሚሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት አሉ” ያሉ ሲሆን ህንን ለማስተካከል እየተሰራ ቢሆንም ቢሮው የባለሙያ እና የመዋቅር ውስንነት እንዳለበት ይናገራሉ።

በከተማዋ ከሚስተዋለው የድምጽ ብክለት የተወሰደ እርምጃ ስለመኖሩ የጠየቅናቸው ኃላፊው “በዋናነት ቅሬታዎች እና ጥቆማዎች  ሲኖሩ በክትትል እየፈታን ነው። በራሳችን የቁጥጥር ስራ ብንሰራም ቢሮው የሰው ኃይል እና የመዋቅር ችግር አለብን” ብለውናል። ቢሮው በክፍለ ከተማ እና በቀበሌ ደረጃ መዋቅር እንደሌለውና ለስራው ፈተና እነደሆነበትም ይናገራሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ሁሉም የድምጽ አካባቢዎች (ከጸጥታ እስከ ኢንዱስትሪ) በቀን እና በማታ ከሚጠበቀውን የድምጽ መጠን በለይ ነው። እንደ ጥናቱ መደምደሚያ የድምጽ ብክለት በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ የሆነ የሕብረተሰብ ጤና እና የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑ አይቀርም።

አስተያየት