መስከረም 14 ፣ 2014

የዴልታ ቫይረስ ስርጭትና የትምህርት ቤቶች መከፈት

City: Addis Ababaዜና

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመመከት እንዲቻል ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የቆዩ ቢሆንም በሽታው የሚገታበት መንገድ ባለመገኘቱ እና የዕለት ተዕለት ህይወትም መቀጠል እንዳለበት በመታመኑ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የዴልታ ቫይረስ ስርጭትና የትምህርት ቤቶች መከፈት
Camera Icon

Photo: news.cn

ዓለም አቀፉን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመመከት እንዲቻል በማለም መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከማወጅ ጀምሮ የተለያዩ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ ተጉዟል። ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከልም ቫይረሱ በተከሰተ በአጭር ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት አንዱ ነበር።

ይሁን እንጂ በሽታው ባህሪውና እና ሁኔታዎችን እየቀያየረ ከመጓዝ ባለፈ የሚገታበት መንገድ ባለመገኘቱ እና የዕለት ተዕለት ህይወትም መቀጠል እንዳለበት በመታመኑ ትምህርት ቤቶች መከፈት እንደሚኖርባቸው የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር በበኩላቸው ትምህርቱ ኮቪድ ወረርሽኝን ከግምት ባስገባ መልኩ የሚሰጥበትን መንገድ ዘረጉ።

በዚህም ረገድ በፈረቃ የትምህርት አሰጣጥ ሒደት እንዲከወን እና በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስ፣ ተማሪዎች በሳምንት ውስጥ ሲማሩበት የነበረውን የቀናት ቁጥር ወደ ሶስት ቀናት በማውረድ ማስተማር የሚያስችል መመርያን ተግባራዊ በማድረግ የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን እንዲጠናቀቅ ተደረገ።

አሁን ደግሞ የ2014ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሊጀምር ቀናት ቀርተውታል ከዚህ ጋር በተያያዘም የትምህርት ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመመካከር ባለፈው አመት ሲተገበር የቆየውን የፈረቃ ትምህርት ለማስቀረት እና ወደ መደበኛው ለመመለስ መወሰኑንና በአዲስ አበባ ከመስከረም 29  ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ ተነግሯል።

ምንም እንኳን ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛው የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ሲመለሱ የኮቪድ 19 ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል የሚወሰዱት ፕሮቶኮሎች አሁንም በጥብቅ እንደሚተገበሩ ቢገልፅም የተማሪዎች ደህንነት ጉዳይ እና የቫይረሱ መስፋፋት ሁኔታ ላይ የሚነሱ የተለያዩ ስጋት እና ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ይነሳሉ።

ዓለምን ላለፉት አንድ አመት ከ8 ወር ገደማ ክፉኛ ሲፈትናት የከረመው ኮቪድ-19 አሁንም ከዕለት ወደ ዕለት ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡ የተከሰተው ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ  በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ እየተስፋፋ የዜጎችን  ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል። በተዛማችነቱ እና በተለይም ሕጻናትን በማጥቃት የሚታወቀው ዴልታ ቫይረስ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ  ሲሉ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

አዲስ ዘይቤ “እንዲህ አይነት ውሳኔ ሲተላለፍ ልጆቹን ከቫይረሲ ለመጠበቅ ምን አይነት የመከላከል እርምጃዎች ተወስዷል?” ስትል ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አንስታለች።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች አሁንም ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ መሆኑን እና የትምህርት አሰጣጡ ሂደት ወደ መደበኛ መመለሱ ችግር እንዳይፈጥር ትምህርት ቤቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ በመግለፅ “የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ሃላፊነት እንዲወጡ አድርገናል፣ ለዚህም መምህራን የፀረ ኮቪድ ክትባት ሳይከተቡ ወደ ስራ ገበታ እንዳይገቡ መመርያ ሰጥተናል” ሲሉ ይገልፃሉ።

አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ከመጀመሪያው በሁለት እጥፍ ተላላፊ መሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት መገለፁን በማስታወስ አዲስ ዘይቤ ቫይረሱ ካለፈው ከመክፋቱ አኳያ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እንዴት ይታያል ስትል ላነሳችው ጥያቄ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ “ምንም እንኳን አዲስ ዝርያ መከሰቱ ቢታወቅም የመከላከያ ጭምብሎችን ጨምሮ የተለያዩ አንቲ ቫይረስ ኬሚካሎችን በመጠቀም እንደከዚህ ቀደሙ ስርጭቱን መግታት ስለሚቻል ከተማሪዎቹ እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀው ከዚህ ቀደም የነበሩትን መመርያዎችን መተግበር ነው” ሲሉ በማብራራት ፈረቃ ይቀራል ማለት ተማሪዎች በጣም ተቀራርበው እና አጋላጭ በሆነ መልኩ ይማራሉ ማለት እንዳልሆነ እና መማርያ ክፍሎችም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ልጆቻቸውን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ ወላጆች ትምህርት ሚንስቴር ያሳለፈውን ውሳኔ አሁን ካለው የቫይረሱ ስርጭት መጨመር አንጸር ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የፈረቃ ትምህርት አሰጣጡ ከተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ስነ ልቦና አንፃር አሉታዊ ጫና እንዳለው በመጥቀስ ትምህርት በመጀመሩ ውሳኔ የሚስማሙም አልጠፉ።

“ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በፈረቃ ለማስተማር ሲቸገሩ ነው የቆዩት” የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አበራ ጣሰው ናቸው። አያይዘውም በፈረቃ ማስተማር የሚለው ሀሳብ ተማሪዎች ላይ የትምህርት አቀባበል ክፍተት እንሚፈጥር ያስረዳሉ።

"የፈረቃ ትምህርትን አሰጣጥ በአብዘሀኛው ተማሪዎች ላይ የስነ ልቦና ጫና መፍጠሩን መገንዘብ ስለተቻለ ነው ወደዚህ ውሳኔ የተመለስነው” የሚሉት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዋና ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ሲሆኑ እሳቸውም የኮቪድ ፕሮቶኮልን ከመጠበቅ አኳያ ስጋት ሊኖር አይገባም ይላሉ።

ዶክተር መሰለ ተሬቻ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ የወረርሽኝ እና ተዛማች በሽታዎች ተመራማሪ ናቸው። "አሁን ባለው የኮቪድ 19 የስርጭት ደረጃ ሁኔታ ተማሪዎችን በታሰበው መልክ ማስተማር ይመከራል ወይ?" ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ 

"በተለያዩ ሀገራት ያለውን ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው ለምሳሌ በቅርቡ በእንግሊዝ አርካንሳስ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በዴልታ ቫይረስ ምክንያት በጥቂት ቀናት ከ1,200 በላይ ተማሪዎች እና ከ100 በላይ ሰራተኞች ተጠቅተዋል፣ ይሄ ማለት ቫይረሱ ከበፊቱ የባሰ እንጂ ያነሰ አለመሆኑን መገመት ቀላል ነው ማለት ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ዶክተር መሰለ አክለውም ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ቤቶች መከፍት ኖሮባቸው ወደዚህ ውሳኔ ቢታለፍም መንግስት ያለምንም ችግር ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አመቱን ማጠናቀቅ ይቻላል የሚለውን እርግጠኝነቱን ወደ ጎን በመተው በትኩረት ሊከታተል የበሽታውን ስርጭት በመከታተል አስጊ ምልክቶች ሲታዮ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል።

አስተያየት