ወ/ሮ ማእረግ ሙጨዬ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ጠመንጃ ያዥ በሚባል አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ከሰሞኑ የ10 ዓመት ልጃቸው መንደር ውስጥ በሚገኝ ባለቤት አልባ ውሻ መነከሱን ተከትሎ ያጋጠማቸውን ሲናገሩ "የተነከሰው እግሩ አካባቢ ነው። ብዙ ጊዜ ሳናጠፋ ወደ ክሊኒክ ወስደነው። ሐኪሞቹ 7 መርፌ አዘውለት አሁን አገግሟል” ይላሉ። “ውሻው ታማሚ መሆኑን ያወቅነው በኋላ ነው። ባለቤት የለውም። የመንገድ ላይ ውሻ ነው። “እብድ ውሻ” መሆኑ ሲያረጋግጡ አስወግደውታል” ብለውናል። በተጠቀሰው አካባቢ ለጥቂት ደቂቃ የተዘዋወረ ማንኛውም ሰው በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ባለቤት አልባ ውሾች እንደሚገኙ ያስተውላል። ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን አረጋግጠዋል። በውሾቹ በድንገት የሚነከሱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ስለመሆኑም ሰምተናል።
ወ/ሮ ማዕረግ በልጃቸው ላይ ከደረሰው በውሻ የመነከስ አደጋ በኋላ የጉዳዩን አሳሳቢነት እንደተረዱ ነግረውናል። “እንኳን ባለቤት አልባዎቹ ራሳችን የምናሳድጋቸውም ቢሆኑ በምን ሰዓት ለበሽታ እንደሚጋለጡ አናውቅም። ስለዚህ ንጽህናቸውን መጠበቅ፣ ማስከተብና ክትትል ማድረግ ይገባል” ሲሉ ይመክራሉ።
በመኖርያ ቤቷ አቅራቢያ በባለቤት አልባ ውሻ እንደተነከሰች የነገረችን ደግሞ አዜብ የማነህ ትባላለች። “አጎንብሼ ሥራ በመስራት ላይ እያለሁ ነው ድንገት የነከሰኝ። ዐላየሁትም ነበር። ፊቴ እና ቅንድቤ አካባቢ ነው ጉዳት ያደረሰኝ” ብላለች።
በፍጥነት ህክምና መከታተል እንደጀመረችና 16 መርፌ ታዞላት እንደዳነች ትናገራለች። የውሻውን ጤንነት ለማረጋገጥ ተገድሎ ሲመረመር በሽታው እንደተገኘበትም ነግራናለች።
ገላን አካባቢ የሚኖረው አቶ አብርሃም ፈቃደ በበኩሉ፡፡ “በድንገት ውሻ የተነከሰ ሰው የውሻውን ጤንነት ለማረጋገጥ ይቸግረዋል” ይላል፡፡ “ሐኪሞቹ የተነከሰው ሰው የውሻውን አንገት ቆርጦ እንዲያመጣ ያዛሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው” ብሎናል ፡፡ የአብርሃምን ቅሬታ እውነተኛነት ለማረጋገጥ ያነጋገርናት ሲ/ር ዘቢደር ኃይሉ ይህ ትእዛዝ የሚሰጠው በሁለት ምክንያት ነው ብላናለች “የመጀመርያው ውሻው ባለቤት አልባ ከሆነ ሌላሰው ላይ አደጋ እንዳያደርስ በሚል ነው፡፡ ዝም ብሎ መናከስ ከጀመረ የሚበክላቸው ሰዎች ስለሚበዙ መሞቱ ለማኅበረሰቡ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የበሽታው ምልክት ሰዎች ላይ በፍጥነት አይታይም፡፡ የምልክቱ ዘግይቶ መታየት ደግሞ የተነከሰውን ግለሰብ ሊጎዳው ይችላል፡፡ ስለዚህ ውሻው በአካል ወይም ሞቶ ሐኪም ቤት ከሄደ ምልክቶቹን ተመልክቶ አለበለዚያም በምርመራ አረጋግጦ ተነካሹን መድኃኒት ለማስጀመር ነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥታናለች፡፡
ከዚህ የውሻ በሽታ ጋር ተያይዞ ያነጋገርናቸው የጎተራ ማሳለጫ ጤና ጣቢያ የሰው ኃብት ኃላፊ እና የድንገተኛ ክፍል ሃኪም የሆኑት አቶ ገብሬ ባደንጋ የበሽታውን መነሻ እና የህክምናው ሂደት በተመለከተ ሲያስረዱ፡-
“በውሾች ላይ የሚታየው የበሽታ ዓይነት ሬቢስ ቫይረስ ከሚባለው የቫይረስ አይነት የሚነሳ ነው። ቫይረሱ የያዘው ውሻ ከውስጡ የሚወጣው ፈሳሽ ላይ ቫይረሱ ይገኛል። ውሻው በሽታው እንዳለበት የሚታወቀው ያለወትሮው ብዙ ሰዎችን ሲናከስ እና በውሻው የተነከሱት ሰዎች ተመርምረው ቫይረሱ ሲገኝባቸው ነው።” ያሉ ሲሆን ትኩሳት፣ በተነከሱበት ቦታ ማሳከክ እና ማቃጠል፣ የለሃጭ መዝረክረክ፣ ራስን መሳት፣ እንደ ውሻ መጮህ፣ ብርሃን መፍራት፣ ለመናከስ መሞከር፣ የውሃ ፍራቻ፣ የሰውነት ክፍሎችን ማንቀሳቀስ አለመቻል እና የመሳሰሉት ሰዎች እብድ ውሻ በሽታ የተነከሱ ሰዎች የሚያሳዩአቸው ምልክቶች ስለመሆናቸው ነግረውናል። በታማሚው ውሻ የተነከሰው ሰው አብዛኛውን ጊዜ ከተነከሰበት ቀን ጀምሮ ከአንድ እስከ ሦስት ወራት ባለው ጊዜ በበሽታው የመያዝ ምልክቶች ያሳያል። ይሁን እንጂ በጥቂት ሰዎች ላይ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ የሚታይበት ጊዜ አለ። የበሽታው አምጪ ህዋስ ወደ ማዕከላዊው የነርቭ ስርአት ለመድረስ እንደሚፈጅበት ርቀት የበሽታው ምልክት ሳይታይባቸው ከአንድ ዓመት በላይ የሚቆዩ ሰዎችም ይኖራሉ። ንክሻው አንገት ጆሮና ትከሻ ላይ ከተደረገ ምልክት የመታየት ሂደቱን እንደሚያፋጥነው ባለሙያው ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሁን ላይ ባለው አሀዛዊ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በዓመት 2 ሺህ 700 ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ ህይወታውን እንደሚያጡ ቢገለጽም ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይገመታል።
የእብድ ውሻ በሽታ በበሽታው በተለከፉ እንስሳት ንክሻ ከውሻ፣ ድመት፣ ቀበሮ፣ ተኩላና ሌሎች ወደ ጤናማ ሰው ሊተላለፍ የሚችል አደገኛ በሽታ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችልበት መንገድ ሰፊ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያ ያስረዳሉ።
በእብድ ውሻ የተነከሰ ሰው ወድያው ወደ ሃኪም ቤት ሄዶ ካልታከመ ከባድ የህክምና ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እና ከዛም ካለፈ ለሞት እንደሚያደርሰው ገልጾልናል።
ህክምናው በውሻ በሽታ የተጎዳውን ሰው “አንቲ ሬቪስ” እና “አይጂ ኤም” የሚባሉ ክትባቶችን በመስጠት እና ሕክምናን በአግባቡ በመከታተል ይፈወሳል።” የሚሉት ባለሙያው ጉዳቱን ያስከተለው ውሻ በአፋጣኝ መወገድ እንዳለበት ገልጸው ውሻው ጤነኛ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚመረመረው ተገድሎ መሆኑን ነግረውናል። የዚህ ምክንያት የተጎጂ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንደሆነ ነግረውናል።
60 በመቶ የሚሆኑት ሰውን የሚጎዱ በሽታዎች የሚተላለፉት ከእንስሳት እንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ከዚህም ውስጥ የእብድ ውሻ በሽታ ዋነኛው ነው። የበሽታውን ስርጭት ከ70 እስከ 80 በመቶ ለመግታት እንደሚያስችል የታመነበት ሕክምና ውሾችን ማስከተብ እንደሆነ የባለሙያዎች አስተያየት እና የጥናቶች ድምዳሜ ያሳያል።