መስከረም 13 ፣ 2014

“ሀፍላታ ሻይ” የበርታዎች መረዳጃ መድረክ

City: Assosaባህል

ወደ በርታ ማኅበረሰብ የመኖርያ አካባቢዎች በእንግድነት የተገኘ ማንኛውም ሰው የእንግድነት ስሜት አይሰማውም። ነዋሪዎቹ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው ሲመለከቱ እንደ ቅርብ ዘመድ የሞቀ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ወደ “አልከልዋ” ይወስዱታል።

“ሀፍላታ ሻይ” የበርታዎች መረዳጃ መድረክ

የበርታ ማኅበረሰብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ አምስት ነባር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው። አብዛኛዎቹ የብሔረሰቡ ተወላጆች በአሶሳ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች እና በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳዎች ውስጥ በስፋት ይገኛሉ። የበርታ ብሔረሰብ አባላት በክልሉ ከሚገኙት ለሎች ብሔረሰቦች መካከል አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት በእርሻ እና በእንስሳት እርባታ ይተዳደራሉ። በክልሉ ከርሰ-ምድር በስፋት የሚገኘውን የወርቅ ሀብት በባህላዊ መንገድ አምርቶ ለገበያ ማቅረብም ሌላኛው የክልሉ ነዋሪዎች መተዳደሪያ ነው።

የበርታ ብሔረሰቦች ካሏቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች መካከል የእንግዳ አቀባበል እና የሰላምታ አሰጣጥ ሥርዓታቸው ጎልቶ ይታያል።  ወደ በርታ ማኅበረሰብ የመኖርያ አካባቢዎች በእንግድነት የተገኘ ማንኛውም ሰው የእንግድነት ስሜት አይሰማውም። ነዋሪዎቹ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው ሲመለከቱ እንደ ቅርብ ዘመድ የሞቀ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ወደ “አልከልዋ” ይወስዱታል። “አልከልዋ” በማኅበረሰቡ ልማድ መሰረት ከሩቅ ተጉዞ የመጣ እንግዳ እንዲያርፍበት የሚዘጋጅ ቤት ነው። አልከልዋ የገባው እንግዳ ቤት ያፈራው የሚበላውም ሆነ የሚጠጣው ያለ ስስት ቀርቦለት እንግድነቱን ያስረሱታል። ለእንግዳው የሚቀርበው መስተንግዶ እና እንክብካቤ እንግዳ ከሆነበት ቤት በተጨማሪ ከጎረቤቶችም ይመጣል።

“አልከለዋ” እንደ ስብሰባ አዳራሽነትም ያገለግላል። ማኅበረሰቡን ስለ አካባቢው ልማት ጉዳይ ለማወያየት፣ ለማስገንዘብና ለማነሳሳት ተመራጭ ነው። የስብሰባው ተሳታፊዎች በሙሉ መሬት ላይ ይቀመጣሉ። ማንም ከፍ ዝቅ ሳይል በእኩልበት መንፈስ ውይይታቸውን ያካሂዳሉ። ሃሳብ ይለዋወጣሉ፣ ያልገባቸውን ይጠይቃሉ፣ በጋራ ይወስናሉ።

የበርታ ማኅበረሰቦች በሚኖሩባቸው አከባቢዎች ማዕድ ቀርቦ ምግብ ሲበላ የደረሰ እንግዳ ጠገብኩ ማለት አይችልም። ማዕድ ላይ ከቀረበው ሰው ጋር ትውውቅ ባይኖር እንኳን አብሮ መመገብ ግዴታ ነው። አንድ ሰው ብቻውን ማዕድ መቅረብ አይፈቀድለትም። ነውር ነው። በሁለቱ ሰዎች ዘንድ ጸብ ቢኖርም ጸቡን ትተው ማዕድ መጋራት፣ አብረው መመገብ ለዘመናት የኖሩበት ልዩ መገለጫ ነው።

የበርታ ማኅበረሰብ ውብ ባህሎች ይዘታቸውንና ስረዓታቸውን እንዳልለወጡ ብዙዎች ይስማማሉ። ከመጤ ባህሎች ጋር የመቀየጥ አደጋ ሳይደርስባቸው አሁን ያለንበት ዘመን ድረስ ከዘለቁ የማኅበረሰቡ ባሕላዊ እሴቶች መካከል የእንግዳ አቀባበል ስርአት አንዱ ነው። የገንዘብም ሆነ ሌላ ዐይነት ችግር ያጋጠመው ወዳጅ ዘመድ ሲኖር የሚረዳዱበት መንገድም ሌላው ተጠቃሽ የባህላዊ አኗኗር ስርአታቸው ነው።

አንድ የማኅበረሰቡ ተወላጅ ወይም የአካባቢው ነዋሪ መፍትሔ ያጣለት ችግር ሲገጥመው “ሀፍላታ ሻይ” (ሻይ እንጠጣ) በሚሰኘው ባሕላዊ ስርአት አማካኝነት የግል ችግሩን በጋራ ይፈቱለታል።

ለማግባት አቅዶ ገንዘብ የቸገረው፣ መማር ፈልጎ አቅም ያጠረው፣ በእንግድነት መጥቶ ገንዘብ የጨረሰ፣ የጀመረውን ቤት ማጠናቀቅ ላቃተው፣… እነዚህ እና እነዚህን መሰል ሌሎች ችግሮች እንቅልፍ የነሱት ሰው ካለ “ሀፍላታ ሻይ” ጭንቀቱን የሚያቀልለት መፍትሔ ይሰጠዋል።

ሂደቱም እንደሚከተለው ነው። ወቅታዊ ችግር ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ ለአንድ የዕድሜ አቻው የሚገኝበትን ችግር ያካፍላል። የወዳጁን ችግር ያደመጠው ግለሰብም “ዛሬ እኛ ቤት ሀፍላታ ሻይ አለ” (እኛ ቤት የሻይ ግብዣ አለ) ይላል። ለትንሽ ትልቁ፣ ለወዳጅ ዘመዱ፣ ለሩቅ ለቅርቡ ይናገራል። የሰማው ላልሰማው እያስተጋባ በ“ሀፍላታ ሻይ” ፕሮግራሙ ላይ ይታደማሉ።

ፕሮግራሙም ሳይውል ሳያድር ይዘጋጃል። ትኩስ ሻይ ይቀርባል። ሻይ እና ዳቦ እየተበላ ችግር የማስረሻ ባህላዊ ጭፈራ ይካሄዳል። ይህ ፕሮግራም በወጣት ሴቶችና ወንዶች በጣም ተወዳጅ ነው፤ ምክንያቱም በፕሮግራሙ ላይ በሚካሄደው የ“ችግር ማስረሻ” ባህላዊ ጭፍራ ያላገቡ ወጣቶች የሚተጫጩበት መድረክም ነው። ከዝግጅቱ በኋላም ታዳሚው ወደቤቱ ከመበተኑ በፊት አቅሙ የፈቀደውን ይለግሳል። የተሰበሰበው ገንዘብም ፕሮግራሙ ለተዘጋጀለት ግለሰብ ይሰጠዋል። ፕሮግራሙ የሚከናወነው ችግር እንዳጋጠመው የታመነውና የዝግጅቱ መነሻ የሆነው ግለሰብ ወደ ውጭ እንዲቀጣ ተደርጎ ነው። ሻይ እየተጠጣ፣ በዘፈን እና በጭፈራ የተሰበሰበለትን ገንዘብ ችግረኛው የገጠመውን ችግር ይቀርፍበታል። በማኅበረሰቡ ታግዞ ከኪሳራ ይተርፋል።

በዚህ አጋጣሚ በተዘጋጀው መድረክ በሚኖረው ጭፈራ ሴቶችም ወንዶችም ታዳሚ እና ተሳታፊ ይሆናሉ። በጭፈራው ወቅት ሴቷ ዐይኗ ያረፈበትን መርጣ በምልክት ለጭፈራ ልትጋብዘው ትችላለች። ወንዱም ልጅቱን ከወደዳት ግብዣዋን ተቀብሎ አብሯት ይጨፍራል። ጨፋሪዎቹ ከተዋደዱና መፈላለግ ካላቸው ‹‹ሀፍላታ ሻይ›› ላይ የጀመሩትን ፍቅር ወደ መተጫጨት ከዚያም ወደ ጋብቻ ሊያሳድጉት ይችላሉ። ለጭፈራ የተጋበዘው ወጣት እምቢታውን ከገለጸ ጋባዧ ሴት ለትዳር ተመራጭ እንዳልሆነች ስለሚቆጠር መራጯ ከፍተኛ ጥንቃቄ ታደርጋለች። ጠይቃ ላለማፈር እምቢ ሊላት የማይችልን ሰው ለመምረጥ ትሞክራለች።

ይህ የሻይ እንጠጣ ፕሮግራም ለበርታ ተወላጆች ብቻ የሚከናወን አይደለም። ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች መጥቶ በርታ ለሚኖር ሰውም ይዘጋጅለታል። የሀፍላታ ሻይ ዝግጅት በእንግድነት መጥቶ ተቸገርኩ ላለ ሰው ብቻ ሳይሆን በአጋጣሚ አካባቢውን ለሚለቅና ወደ ትምህርት ቤት ለሚሄድ ሰው እንዲሁም በቅርብ ለማግባት ለሚዘጋጅ ወጣት ይዘጋጅልኝ ብሎ ባይናገርም የሚያውቁት ጓደኛቹ፤ ጎረበቶቹ ያዘጋጁለታል።

እንግዲህ በበርታ ማኅበረሰብ ባህል ውስጥ ሁለት ዓይነት የሀፍላታ ሻይ ዓይነቶች አሉ። የመጀመርያው ከላይ የተመለከትነው ለተቸገረ ሰው “የሻይ ፓርቲ” በማዘጋጀት ብቻ ገንዘብ የሚሰበሰብበት መድረክ ሲሆን፤ ሌላኛው አቅመ ደካሞች ያለ ምንም ክፍያ ስጋ በማዘጋጀት የሚጋበዙበት መድረክ ነው።

በዚህኛውም መድረክ ልክ እንደ አፍላታ ሻይ ሁሉ በወጣቱ ዘንድ የመተጫጫ እና ለጋብቻ መመራረጫ ቦታ ስለሆነ በወጣቱ ዘንድ በጣም ተወዳድ ነው። ልዩ የሚያደርጋቸው ሀፍላታ ሻይ ገንዘብ ተሰብስቦ ገንዘቡ ለተቸገሩት ሰዎች ይሰጣል። ሁለተኛው ዐይነት ግን የተዘጋጀውን ስጋ ነክ ምግብ አቅም ለሌላቸው እንዲከፋፈል ይደረጋል።

የማኅበረሰቡ ተወላጅ የሆኑት የአሶሳ ከተማ ነዋሪ አቶ አልከድር አህመድ “ሕብረተሰቡ መድረኩን ሲያዘጋጅ ሌላኛውን አካል በማይጐዳ መልኩ እንደሆነ እና በማኅበራዊ ህይወት ውስጥ የሚከሰቱት ችግሮችን ለብቻ ከመጋፈጥ በጋራ ሆኖ እንዲያቃልለው ያስችላል።” ብለዋል። “የበርታ ማኅበረሰብ መገለጫና ማኅበራዊ ባህሉም ስለሆነ መጠበቅ አለበት” የሚል ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

አስተያየት