በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ገፆች ከማክሰኞ ሕዳር ፤ 14 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላሊበላ እና አካባቢው በመንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር ገብተዋል የሚሉ ልጥፎች ሲዘዋወሩ አስተውለናል። ሲዘዋወሩ ከነበሩት ልጥፎች መካከል አንዳንዶቹ አንድ የአማራ ልዩ ሃይልን የደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ከታዋቂው “የቤተ-ጊዮርጊስ” ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አጠገብ ተቀምጦ የሚያሳይ ምስል አያይዘው ለጥፈዋል።
ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።
ከህዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፌደራሉ መንግስት እና የህወኃት ሃይሎች በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል አስወጥቷል።
ከዚያ በኋላ የህወኃት ሃይሎች ወደ ደቡባዊ የክልሉ አቅጣጫ በመጓዝ የአማራ እና አፋር አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እየገፉ በመምጣት ሐምሌ ፤ 29 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘውን የላሊበላ ከተማን ተቆጣጥረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የማጥቃት እና የመልሶ ማጥቃት እርመጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል። በሕዳር 13 ፤ 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ።” በማለት ጦርነቱን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ጦር ሜዳ መዝመታቸውን ተከትሎ አዳዲስ የመልሶ ማጥቃት ወሬዎች እየተሰሙ ይገኛሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግምባር በመዝመት እና አቅጣጫ ለመስጠት በጦር ሜዳ ግምባር መገኘታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ የድል ዜናዎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። ይህም የፌስቡክ ልጥፍ በዚህ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው።
ሀቅቼክም ጉዳዩን በመከታተል የልጥፉን እውነታነት ለማጥራት ባደረገው ጥረት መሰረት የተጋራው ምስል የቆየ እንደሆነ አረጋግጧል። ምስሉ ከዚህ ቀደም በሚያዚያ 21 ፤ 2013 ዓ.ም ዉበቱ ይግዛው በተባለ የፌስቡክ አካውንት “የቅዱስ ላሊበላ መቅደሶች በአማራ ልዩ ሃይል በተጠናከረ ሁኔታ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።” በማለት ምስሉን አጋርቶት ነበር።
ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከፌደራል መንግስቱም ሆነ ከህወኃት ሃይሎች ከተማዋ ስለመያዟ የወጣ ምንም አይነት መግለጫ የለም። ከሚመለከታቸው አካላት የተረጋገጠ መረጃን ለማግኘት ጥረት እያደረግን ሲሆን አዲስ መረጃ እንዳገኘን የምናሳውቅ ይሆናል።
ምንም እንኳን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመንግስት ሃይሎች የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን የሚገልፁ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ሀቅቼክ ምስሉ የመንግስት ሃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ስለማያሳይ ሀሰት ብሎታል።