8ኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የድሬዳዋ ከተማ የጽዳት ዘመቻ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውኅዳር 14 ፣ 2014
City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች
8ኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የድሬዳዋ ከተማ የጽዳት ዘመቻ

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የሚካሄደው የጽዳት ዘመቻ የያዝነው ሳምንት ሲጠናቀቅ 9ኛሳምንቱን ያስቆጥራል። በድሬዳዋ ከተማ ዘወትር ቅዳሜ በሚካሔደው የጽዳት ዘመቻ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። ባለፉት ስምንት ሳምንታት 06፣ 07፣ 08 በመባል የሚታወቁት የከተማዋ መኖርያዎች የዘመቻ ጽዳቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ፣ በድሬዳዋ አስተዳደር ም/ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ አጽጂዎችን በማንቃትና በጋራ በመስራት ተሳትፎ ከነበራቸው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

9ኛ ሳምንቱን ሊያስቆጥር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የቅዳሜ ማለዳ ሳምንታዊ የጽዳት ዘመቻ በተከታታይ ሲካሄድ በከተማዋ ታሪክ እጅግም ያልተለመደ ነው። በተራራቁ ቀናት ለአንድ ጊዜ ብቻ መካሄዱ ቀርቶ ለተራዘመ ጊዜ የተካሄደበትን ምክንያት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር ሲያብራሩ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በነፍሳት ምክንያት የሚዛመቱ በሽታዎች የነዋሪዎች ስጋት ሆነዋል። ተመሳሳይ ችግሮችን የመከላከያ ዋነኛው መሳሪያ ጽዳት ነው” ብለዋል። ከፍተኛ አመራሩ በየሳምንቱ ቅዳሜ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የጽዳት ዘመቻውን መቀላቀሉ አርአያነቱን እንደሚያጠናክር የተናገሩት ከንቲባው “ዘመቻው ለአንድ ዓመት ይቀጥላል” ማለታቸውን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከድሬዳዋ ዘግባለች። የተከታታይ ዘመቻው ዋና ዓላማም ሕብረተሰቡ ጽዳትን ባህል እንዲያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። የንግድ ድርጅቶችም ሕግ በሚያስገድዳቸው መሰረት የተቋማቸውን ዙርያ እንዲያጸዱ ያሳሰቡ ሲሆን አዋጁን በማይተገብሩ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቀዋል።

ወ/ሮ ሙላቷ ግዛው የለገሀሬ አካባቢ ነዋሪ መሆኗን ነግራናለች። “ዘመቻው ለተከታታይ ሳምንታት በመዝለቁ ቀጣይነት ያለው ይመስላል። ማሕበረሰቡ ማንም ሳይቀሰቅሰው እንዲያጸዳ እና የጸዳውንም መልሶ እንዳያቆሽሽ ማስተማር ግን ያስፈልጋል። መጽዳት ከልብስ እና ከቤት ውጭ ያለውን አካባቢም ማጽዳት እንደሆነ የተገነዘበ ማሕበረሰብ መፍጠር ዋነኛ ግቡ ሊሆን ይገባል” የሚል ሐሳቧን ሰንዝራለች።  

አቶ ድቡሽ ተገኝ በበኩሉ ዘመቻው ነዋሪውን ከአመራሮች ጋር ማቀራረቡን በበጎ ተመልክቶታል። ጽዳቱ ሁሉንም የከተማዋን አካባቢዎች ያካተተ አለመሆኑ እንዲስተካከልም ጠይቋል። “በግልጽ ቆሻሻ የሚጣልባቸው እንደ አሸዋ (ደርዘን ተራ፣ ሰልባጅ ተራ፣ ጫት ተራ)፣ ከሺኒሌ (ክርስቲያን መቃብር) ወደ ገንደ ገራዳ የሚወስደው መንገድ የመሳሰሉ አካባቢዎች አሉ። በ8 ሳምንቱ ጽዳት ግን አልተካተቱም” የሚለው አቶ ድቡሽ በከተማዋ የተሟላ የቆሻሻ መጣያ አለመኖሩ የሚቀረፍበት መንገድ እንዲኖር ጠይቋል። “የመንገድ ላይ ደረቅ ቆሻሻ መጣያዎች በቅርብ ርቀት ትልልቅ ጎዳናዎች ላይ ቢቀመጡ የተሻለ ይሆናል። መስተዳድሩ ቢያስብበት ጥሩ ይመስለኛል” ብሏል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪአችን ወ/ት ሙና ሁሴን “የነዋሪው የቆሻሻ አወጋገድ ችግር አለበት። የፍሳሽ ማስወገጃዎች ላይ ደረቅ ቆሻሻ ይጥላል። ቱቦዎቹም አሁን ያለውን የሕዝብ ቁጥር እና የፍሳሽ መጠን የሚያስተናግዱ አይደሉም። መሻሻል ይገባቸዋል” ብላለች።

በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ በወረርሽኝ መልክ እየተከሰቱ ጉዳት የሚያደርሱት ችኩንጉንያ፣ ወባ እና ደንጊ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር አካባቢን ማጽዳት እና ውሃ የቋጠሩ ጉድጓዶችን ማፋሰስ ቀዳሚ መከላከያዎቹ ስለመሆናቸው የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።  

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊ ናቸው። “እንደ ድሬዳዋ ባሉ ሞቃታማ አካባቢዎች የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ማኅበረሰቡን ለተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ እድሉን ይጨምረዋል። በተለይም አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የድሬደዋ አስተዳደር ነዋሪዎችን እያጠቁ ያሉትን የችኩንጉኒያ፣ የወባና ደንጊ በሽታ ወረርሺኝ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ሕብረተሰቡ አካባቢውን በባለቤትነት እንዲያጸዳ ማበረታቱ ጥሩ ጅምር ነው” ብለዋል።

አዋጅ ቁጥር 513/ 1999 ስለ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ይደነግጋል። የመኖርያ ቤት አያያዝ ቁጥር 11 ላይ የእያንዳንዱ መኖርያ ቤት ኃላፊ ቆሻሻን ሲያስወግድ በአግባቡ መሆን እንደሚገባው ያስገነዝባል። ለዳግም አገልግሎት የሚውለውን እና ከነጭራሹ የሚጣለውን ቆሻሻ ለይቶ ለቆሻሻ ማስወገጃ ወደተወሰነው ቦታ እንዲደርስ የማድረግ ግዴታ ይጥልበታል። ይሁን እንጂ፤ ቆሻሻን ከመኖርያ መንደሮች ለመሰብሰብ የተዘጋጀ ሥፍራ በአቅራቢያው እያለ ያልተፈቀደ ቦታ መጣልን ይከለክላል። ጉድፍን በመንገድ፣ በጎርፍ መሄጃ ቦይ፣ በፓርክ፣ በአውቶቢስ ወይም በባቡር ጣቢያ በስፖርት ሜዳ በከተማ ውስጥ በሚገኝ የውሃ አካል ወይም በሌላ የህዝብ መጠቀሚያ ቦታ መጣል የተከለከለ ነው። የከተማ አስተዳደሮች በዚህ አዋጅ መሰረት በተወሰኑ የመኖርያ አካባቢዎች የመኖርያ ቤት ደረቅ ቆሻሻ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ በቂ የአገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። የመኖርያ አካባቢን እስከ 12 ራዲየስ የግል ድርጅቶችና የተለያዩ ተቋማት ደግሞ እስከ 40 ራድየስ ድረስ የተቋማቸውን አካባቢ የማፅዳት ግዴታም በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል።

ከፍተኛ ፍሳሽ ቆሻሻ ከሚገኝባቸው የከተማዋ መኖርያዎች መካከል አንዱ የሆነው ቀበሌ 06 ከጽዳት ባሻገር አጥፊዎችን የመቅጣት ሥራ መከናወኑን ሰምተናል። አስተማሪ ነው የተባለለት ቅጣት በጥፋቱ ውስጥ የነበሩትን እንደሚያርም እና ሌሎችም ወደ ጥፋቱ እንዳይገቡ ያስጠነቅቃል ተብሏል ከመጠን በላይ ፍሳሽ በመልቀቅ፣ የተበላሹ የውሃ ቧንቧዎችን በፍጥነት ባለማስጠገን፣ የተሰበሩ እና የተሰነጠቁ የውሃ መስመሮችን ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባለማሳወቅ፣ የቤት ውስጥ ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በሕዝብ መተላለፊያ መንገዶች በቋሚነት በማስወገድ እና በመሰል ጥፋቶች ቅጣት የተጣለባቸው ግለሰቦች ብዛት 60 እንደሚደርስ የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፋህሚ ሙሜ በዘመቻው ወቅት ባስተላለፉት መረጃ ተጋግረዋል ቅጣቶቹ የውሃ ቆጣሪ ማሸግን የመሳሰሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ የገንዘብ ቅጣት የሚገኝበት ሲሆን በወረዳ 06 ውስጥ የሚገኙትን ቀፊራ፣ 5ኛ፣ መልካ ጀብዱ፣ የለገሀሬ አዋሳኝ መንገድን፣ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ያጠቃልላል።

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

Zinash is Addis Zeybe's correspondent in Dire Dawa.