ትኩረት የሚሻው ቆማ ፋሲለደስ

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀኅዳር 15 ፣ 2014
City: Gonderባህል ታሪክ
ትኩረት የሚሻው ቆማ ፋሲለደስ

ቆማ ፋሲለደስ ክበቡ ክበቡ

እንኳን ሳር ቅጠሉ ያስደምማል ካቡ (ፋሲል ደሞዝ)

“ቆማ” ስያሜዋን ያገኘችው በአጼ ፋሲል እናት በንግሥት ወልደሳህላ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ያለችው “ቆማ የፋሲለደስ” ቤተ ክርስቲያን መገኛ ነች። ቤተ መቅደሱ የተገነባው በ1957 ዓ.ም. በንጉሥ ሱስንዮስ ሚስት በአጼ ፋሲል እናት በንግሥት ወልደ ሳህላ ነው። “ቆማ” ቅዱስ ፋሲለደስ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ተጠናቆ ለክብረ በዓሉ በታረደው ሰንጋ በሬ ምክንያት የተሰጠ አዲስ ስያሜ ስለመሆኑ ይነገራል። አፈ-ታሪኩ እንዲህ ይላል። ለቤተመቅደሱ ምርቃት ሊታረድ የተሰናዳው ነጭ በሬ የእርድ ሂደቱን አቋርጦ አመለጠ። ህዝቡም በሬውን ለመያዝ ሲሮጥ ንግሥቲቱ “በሬውን አትያዙት” አሉ። “ዝምብላችሁ ተከተሉት” ህዝቡም የታዘዘውን ፈጸመ። ለንግሥቲቱ “በሬው የት ደረሰ?” ለሚለው ጥያቄ ሕዝቡ “ቆመ” ሲል የሰጠው ምላሽ እስካሁን የአካባቢው መጠሪያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። “ቆማ ፋሲለደስ”

ንግስቲቱ በሬው የቆመበት ሥፍራ አጋጣሚ ሳይሆን ፈቃደ እግዚአብሄር እንደሆነ ተቀበሉ። በመጀመርያ እድሞ (አጥር) እና እቃቤት በድንጋይ እና በኖራ አሰሩ። በመቀጠልም ቤተ-መቅደሱን አሳነጹ። አባቶች ስለ አሰራሩ የሚያስረዱት የገዳሙ አባት “ግማሹ በኖራና በድንጋይ የታነጸው ቤተ-መቅደስ የተጠናቀቀው በጭቃ ነው። የበቁ አባቶች እድሜሽ አጭር ነው ስላሏት ሞትን ለመቅደም በጭቃ ተጠናቀቀ” ይላሉ።

“ቤተ ክርስቲያኑን በ1624 ዓ.ም. አፄ ፋሲል የደብርና የገዳም ሥርዓት እንዲፈፀምበት ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ቆማ ቅዱስ ፋሲለደስ ብለው ሰይሙታል” የሚሉት አባ ዓለሙ ናቸው፡፡ በገዳሙ ዙርያ ያሉ 44 አድባራት የሚገኙ ምእመናን ለገዳሙ ግብር እንዲያስገቡ በ318 አገልጋዮች እንዲገለገል፤ በደናግል መነኮሳት እና አስራ ስምንት ዓመት ባልሞላቸው ዲያቆናት አገልገሎት እንዲሰጥ እንዳደረጉ ያብራራሉ።

በንግሥቲቱ የተሰጠ ሰፊ የእርሻ መሬትም ነበረው። የድመት መሬት (ለእቃ  ቤት ጠባቂዋ ድመት የእርሻ መሬት ተዘጋጅቶ ኑግ እየተዘራ ትመገብ ነበር)፣ ለአጽጂዎች፣ ለብረት ባለሙያዎች፣ ለሸማኔዎች መሬት ነበራቸው።

አጼ ፋሲለደስ በነገሡ በ8ኛ ዓመቱ በ1632 ዓ.ም. ቆማ ፋሲለደስ ለርዕስ አድባራት ወገዳማትነት በቃ፤ ይህ ይሆን ዘንድ ለስፍራው የተለየ ትርጉም የነበራቸው እናቱ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

የጥንቱ ሕንጻ ኪነ-ቅርጽ ከፋሲል ግቢ ሕንጻዎች ጋር ይመሳሰላል። በክብ ቅርፅ የተሰራ ነው። ሦስት ክፍል አለው። በእንክብካቤ እጥረት ቢጎዳም ውበቱን ጨርሶ አልጠፋም። ከመሬት ወደ ላይ 6 ሜትር ከፍታ የካብ ዕድሞ /አጥር/፣ የትምህርት መስጫ ባለ ሰገነት ጉባኤ ቤት አለው።

ቤተ ክርስቲያኑ በሰማዕቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ስም የተደበረ ነው። ታቦቱ ከትውልድ ሀገሩ አንፆኪያ የመጣ እንደሆነም ይነገራል። ክብረ በዓሉ መስከረም 11 እና ታህሳስ 11 ሲሆን ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ክብረ በዓሉን የእስልምና ተከታዮችም ያከብሩት እንደነበር የደብሩ አባቶች ያስረዳሉ።

በ2005 ዓ.ም. ቤተ ክርስቲያኑ እድሳት ተደርጎለታል። በተደረገለት እድሳት የቤተ ክርስቲያኑ የውጭ ገፅታ በሲሚንቶ የተሰራ በመሆኑ ታሪካዊነቱን አጥፍቶታል። የቤተመቅደሱ እና የቅድስቱ ግድግዳ ግን ጥንት እንደነበረ ስለመሆኑ ከአስጎብኚዎች ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በቅድስቱ ውስጥ 12 የእንጨት ምሰሶዎች አሉ። ምሶሶዎቹ ወይራ እና ጥድ ከእንቧጮ ዛፍ ጋር በማጣበቅ ይዘጋጃል። እንጨቶቹ የተያያዙትም ካለምንም ማጣበቂያ እርስ በርስ በማያያዝ ነው። ምሰሶዎች ሲተከሉ ቤተክርስቲያኑን የሚገነቡት ሰዎች ምሶሶዎቹን መትከል ከብዷቸው ትተውት ሲሄዱ አንድ ባህታዊ ብቻቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደተከሉት ይነገራል።

ቅርሱ በቤተ ክርስቲያኑ ጥንታዊ የሆኑ ከአፄ ፋሲል፣ ከንግሥት ወልደሳህላ እና ከሌሎች ነገሥታት የተበረከቱ የብራና መጻሕፍት፣ የብረት ደውል፣ የብር ከበሮ፣ ነጋሪት፣ የወርቅ መስቀል እና ልዩልዩ ጥንታዊ ቅርሶች ይገኛሉ።

በተጨማሪም በዚህ ቤተክርስቲያን ከሚገኙ ጥንታዊና የማይቀሳቀሱ ቅርሶች መካከል የግድግዳ ላይ ሥዕሎች፣ በጎንደር ዘመነ መንግሥት የግንባታ ጥበብ የተሰሩት የቤተክርስቲያኑ አጥር፣ እቃ ቤት እና ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ናቸው።

ይህን ቤተክርስቲያን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ እቃ ቤቱ እና የቤተክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ያሉ መስቀሎች ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰሩ መሆናቸው ነው። ሌሎችም ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ቅርሶች ከብር፣ ከወርቅ፣ ከእምነ በረድ ከሌሎች ማዕድናት የተሰሩ ንዋየ ቅድሳት ይገኛሉ።

ቆየት በ1928 ዓ.ም. በጣሊያን ወረራ ዘመን ፈረንጆች ጫማቸውን ሳያወልቁ ቤተክርስቲያን ሊገቡ ሲሉ እባብ እግራቸውን ላይ ተጠምጥሞባቸው ሳይገቡ መቅረታቸው ከሚነገሩ የአካባቢው ተአምራት መካከል አንዱ ነው።

የቆሜ ዜና ርክርኩ(ጉሮሮ) ረዥም በመሆኑ  አንድ  አንድ ቦታ ላይ ዘሩ (ቁጥሩ) የሚለይ መሆኑ እና ዜማውን ለመማር ክብደት ያለው በመሆኑ ከሌሎች ዜማዎች ይለያል። የቆሜ ዜማ ድጓ መጻሕፍት በታላላቅ ገዳማትና አድባራት የሚገኝ ሲሆን በአክሱም፣ ላሊበላ እና በመካነ  ኢየሱስ እንደሚገኝ ይገመታል። የቆሜ ዜማ ምስክርነት የሚሰጠው በቆማ ፋሲለደስ ቤተክርስቲያን ነው።

በቤተ ክርስቲያኑ በርካታ ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በአያያዝ ችግርና ባለመጠገናቸው እየተበላሹ መሆኑን ታዝበናል። እነዚህም ችግሮች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የግድግዳ ሥዕሎች መበላሸት እና በእቃ ቤቱ የሚገኙ ቅርሶች በቦታ ጥበት ምክንያት ተደራርበው በመቀመጣቸው እየተጎዱ ይገኛሉ። በቤተክርስቲያኑ ያለው ዋና ችግር የቅርስ ማስቀመጫ ቦታ አለመኖርና ጎብኚዎችን ለመሳብ ምንም ጥረት አለመደረጉ ነው ሲሉ ያብራሩልን በቅጥር ግቢው ያገኘናቸው ቀሳውስት ናቸው።

Author: undefined undefined
ጦማሪጌታሁን አስናቀ

Getahun is Addis Zeybe's correspondent in Gondar.