ነሐሴ 19 ፣ 2012

ታላቁ የጤና ባለሙያ - ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ

ዝክርግለ ታሪክ

በአለማችን ላይ ቀን ከቀን እየጨመረ የሔደው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የሰው ልጅ ወደ የህክምና ባለሙያዎች ጋር የሚያደርገውን ምልልስ ጨምሮታል። የጤና…

ታላቁ የጤና ባለሙያ - ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ
በአለማችን ላይ ቀን ከቀን እየጨመረ የሔደው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የሰው ልጅ ወደ የህክምና ባለሙያዎች ጋር የሚያደርገውን ምልልስ ጨምሮታል። የጤና ባለሙያዎችም አቅማቸው በፈቀደ መጠን የሰው ልጆችን ህይወት ለማትረፍ እየተረባረቡ ይገኛሉ። በሀገራችንም ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎች የበኩላቸውን አስተዋፅዎ እያደረጉ ይገኛሉ። ለወራት ከቤተሰቦቻችው እና ከሚወዷቸው ተለይተው የራሳችውን ህይወት አደጋ ላይ ጥለው የሌላውን ለማትረፍ ቀን ከለሊት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። የእነዚህ ጤና ባለሙያዎች ትጋት ለማዘከር በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸውን ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ እናንሳ። አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዶክተር ሲሆኑ ከህክምና ሙያቸው ባለፈ ለሀገር ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከአባታቸው አዛዥ እሸቴ ወ/ማርያም እና ከእናታቸው ወ/ሮ ደስታ በ1857 ዓ.ም. በጎንደር አካባቢ የተወለዱት አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ገና የሦስት ዓመት ጨቅላ ሳሉ ነበር ከቤተሰቦቻቸው የተለዩት በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ከእንግሊዝ ጋር ለመዋጋት ወደ መቅደላ የዘመቱት የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ወላጆች ዳግም አልተመለሱም።ከንጉሱ እልፈት በኋላ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፣ አለማየሁ ቴዎድሮስ እና ወርቅነህ እሸቴ ተማርከው ነበር፡፡ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ቻርለስ ቻምበርሊን ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ወስነው በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወደ ነበረችው ህንድ ወሰዷቸው፡፡ ሕፃን ወርቅነህ በሕንድ አገር ለአራት ዓመት እንደተቀመጡ አሳዳጊያቸው ቻርለስ በሞት ስለተለዩ ኮለኔል ማርቲን የተባለው ሰው ተቀብሎ ከአንድ የሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ እሳቸውም ኮኖሬል ማርቲን የዋሉላቸወን ውለታ በማሰብ ስማቸውን ወደ ቻርለስ ማርቲን ለውጠው ነበር። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፑንጃብ በምትባለው ከተማ ተከታትለው ሲጨርሱ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ስለነበራቸው በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን በዚያም በህክምና ሙያ ተመርቀው በረዳት ሐኪምነት ሰርተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄደው በግላስኮ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በቀዶ ጥገና ሙያ በታላቅ ክብር ተመርቀዋል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የሀኪሞች ማሕበር “የበቃ ጥቁር ሀኪም” የሚል ሽልማት ተበረክቶላቸዋል።ሀኪም ወርቅነህ እንደተመረቁም የእንግሊዝ መንግስት ራሳቸውን ችለው የቀዶ ጥገና ስራቸውን እንዲያከናውኑ በጊዜው በእንግሊዝ ስር ወደነበረችው በርማ ላካቸው፡፡ በወቅቱ ለአጼ ምኒልክ ቅርበት ከነበራቸው ምሁራን መካከል አለቃ አጽሜና አለቃ ታዬ የሚባሉት ስለሃኪም ወርቅነህ ዝና አውሮፓ ሳሉ የሰሙትን አንድ በአንድ ነገሯችው፡፡ አጼ ምኒልክም ሐኪም ወርቅነህ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የህክምና ሥራ እንዲሰሩ እንዲፈቅዱላቸው ለእንግሊዝ መንግሥት ደብዳቤ ጻፉ:: የእንግሊዝ መንግሥት “በሁለታችን መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጥበቅ ቻርልስ ማርቲንን ስንልከው ለእርስዎም ያለንን አክብሮት ለመግለጥ ነው” በማለት መፍቀዳቸውን በመግለፅ ሐኪም ወርቅነህን ልኳቸዋል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ጥቂት ዓመታት ያህል እንዳገለገሉ በ1894 ዓ.ም ኦጋዴን ውስጥ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር በተደረገ ጦርነት፤ በጦርነቱ ቁስለኞችን ከቦታው ድረስ ሄደው ያከሙት ሐኪም ወርቅነህ ናቸው፡፡ በ1895 ዓ.ም እንደ ገና ወደ እንግሊዝና በርማ ሄዱ፡፡ በዚያም አምስት ዓመት ሲቀመጡ ከእንግሊዛዊትና ባለቤታቸው ሴት ልጆችን አፍርተዋል።በ1903 ዓ.ም በመጡበት ወቅት ከወ/ሮ ቀፀላ ወርቅ ቱሉ ጋር ትዳር የመሠረቱ ሲሆን ትዳራቸው ሰምሮ አምስት ወንዶችና ስምንት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህ በድጋሚ በመጡ ጊዜ አጼ ምኒልክ የአውሮፓን ስልጣኔ ወደ አገራቸው እያስገቡ ነበር፡፡ ሐኪም ወርቅነህም በማስተማርና በህክምና የቻሉትን ያህል አጼ ምኒልክን ደግፈዋል፡፡አጼ ምኒልክ በታመሙ ጊዜ በመጀመሪያ ሙሴ ሃርማኒየር የተባሉት ሲያክሙ ቆይተው በኋላ ሐኪም ወርቅነህ በቦታው ተተክተው ማከም ቀጠሉ፡፡ በ1906 ዓ ም (ከአጼ ምኒልክ እረፍት በኋላ ሐኪም ወርቅነህ ወደ በርማ የተመለሱ ሲሆን በአጠቃላይ በሕንድና በበርማ ለ32 ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ጣልያን ኢትዮጵያን እስከ ወረረበት ድረስ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል።ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፍልውሀ ድርጅት አቋቁመዋል፤ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል፤ የየካቲት 12 ሆስፒታል(የቀድሞው ቤተ – ሳይዳ)፣ የጅማ መንገድ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቋቋሙ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በ1927 ዓ.ም በአባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ግድብ እርዳታ ለማሰባሰብ ወደ አሜሪካ የተጓዘውን ቡድን መርተዋል ፣ በ1920 ዓ.ም ለቆመው ዘመናዊ ፍርድ ቤት አዛዥ ተብለው በተሰጣቸው ሹመት በቅንነት አገልግለዋል፣ የጨርጨር አውራጃ ገዢ በመሆን የሰሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በነበረባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የተለያዩ ሙያ ያላቸው 21 ህንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ የግል ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም ሰርተዋል። በአንድ ወቅት በኢትዮጲያ ቴሌቪዝን ላይ ቀርቦ በነበረው ዘገባ ሀኪም ወርቅነህ የጨርጨራ አውራጃ ገዢነታችውን ሲቀበሉ አበጋዝ በሚል ማእረግ አንዲጠሩ ባለመፈቀዳችው የደች አዝማች ማእረጋቸውን ተጠቅመውበት እንደማያውቁ ልጆቻቸው ይናገራሉ። ያከናውኑት የነበረውን መልካም ስራ አቶ ፍስሐ ተከስተ “ታሪክ እና ባለታሪክ በጨርጨር እና በአሰበ ተፈሪ” የተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረውታል። ከነዚህም ውስጥ ዘሩን ከህንድ ሀገር አስመጥተው ያስተከሉት የማንጎ ተክል እስካሁን በሀገሪቱ አንድ አንድ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ይህን ጨምሮ ለከተማው ነዋሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የንፀህ ውሀ ተጠቃሚ አድርገዋቸዋል። ሐኪም ወርቅህ የሚያደርጉትን የተቃውሞ ትግል ለመበቀል ጣሊያኖች ዮሴፍ ወርቅነህና ቢንያም ወርቅህ የተባሉ ልጆቻቸውን በ1929 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ገደሉባቸው።አንዳንድ የቤተሰብ አባልት “አላርፍ ብለህ ልጆቹን ወደ ሀገር ቤት ልከህ አስገደልካችው” የሚል ትችት ቢያድርስባቸውም የሳቸው ምላሽ ግን “ከልጆቼ መሞት በላይ ያሳሰበኝ የሀገሬ መሞት ነው” ብለዋል። ከሐኪም ወርቅነህ ታዋቂ ልጆች መካከል ዶ/ር ዮሃንስ ወርቅነህ፣ አስቴር ወርቅነህና ኤልሳቤጥ ወርቅነሀ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከነጻነት መልስ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ህንድ ሄደው የቆዩ ሲሆን በመጨረሻ ከቤተሰባቸው ጋር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ ቆይተው በማረፋቸው በአዲስ አበባ በሚገኘው የየካው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ዘመድ እና ቤተሰቦቻችው በተገኙበት ወደ ዘላለም ቤታቸው ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

አስተያየት