ታህሣሥ 13 ፣ 2015

ሙሉ ኢኮሎጅ - የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር

City: Addis Ababaዜናየአኗኗር ዘይቤ

በጮቄ ተራራዎች እና ተክሎች መሀል በወጣቱ አብይ አለም የተመሰረተው 'ሙሉ ኢኮሎጅ መንደር' የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ ተመረጧል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ሙሉ ኢኮሎጅ - የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር
Camera Icon

(ምንጭ፡ የሙሉ ኢኮሎጅ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቢይ አለም)

“ከሁለት አስርት አመታት በፊት የጮቄ ተራራ ከ270 የሚበልጡ ትናንሽ የውሃ ምንጮች እና ከ50 በላይ ወንዞች መነሻ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ የውኃ አካላት አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል” ሲሉ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጮቄ ተራራ ተፋሰስ ጥናትና ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ምግባሩ ወንዴ ይገልፃሉ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአካባቢው ከህዝብ መብዛት ጋር ተያይዞ፣ በስፍራው ያለውን ቀዝቃዛ አየር ለመቀየር ተብሎ በተቆረጡ ዛፎች እንዲሁም አርብቶ አደሮች እና የሚረቡ እንስሳት ቁጥር በመጨመራቸው አረንጓዴ ቦታዎች በስፋት ለግጦሽ በመዋላቸው የአካባቢው መሬት እንቀድሞው ውሃ ከማስረግ ይልቅ አፈር እያጠበ እየሄደ እንደሆነ ይነገራል።

በአንድ ወቅት የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ፣ ለዓባይ ወንዝ ትልቁ ተፋሰስ የሆነው፤ በተራራው የታችኛው ክፍል ለሚገኙ አርሶ አደሮች አየሩን በማቀዝቀዝ ምቹ የአየር ሁኔታ የሚፈጥር ቦታ የነበረው የጮቄ ተራራ ስጋቶች ተጋርጠውበታል። ይሁን እንጂ “የጎጃም ጣሪያ” ተብሎ የሚጠራውን የጮቄ ተራሮች በማልማት የተጀመረው 'ሙሉ ኢኮሎጅ' የጎብኚዎች መንደር የ2022 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር በመሆን ከሌሎች ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ጋር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተመርጧል።

ከ57 አገራት የተመረጡ 136 የቱሪዝም መንደሮች ለውድድር በቀረቡበት የ2022 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ዓለም አቀፍ ውድድር ሙሉ ኢኮሎጅን በውስጡ የያዘው የጮቄ ተራራ ከኢትዮጵያ የተመረጠ ሲሆን በአጠቃላይ ከ18 ሀገራት 32 የቱሪስት መዳረሻዎች አሸናፊ ሆነዋል።

የሙሉ ኢኮሎጅ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት አብይ አለም ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ አድርጓል። “እኔ ከዚህ አካባቢ ተምሮ እንደወጣ ሰው ድሮ በልጅነቴ የማውቀው ብዝኃ ህይወት እና የአካባቢው የአየር ሁኔታ ልዩ ነበር” ሲል የቀደመውን ጊዜ ያስታውሳል። የጮቄ ተራሮች የነበሩበትን ሁኔታ አብይ ሲመለከት በወቅቱ ሁለት አማራጭ እንደነበረው ይገልፃል። የመጀመሪያው ኑሮውን በውጭ ሀገር እንዲገፋ የነበረ እድል ቢሆንም አብይ አለም አካባቢውን የመቀየር ኃላፊነት እንዳለበትም አስቦ ነበር።

አብይ ጊዜውን ሲያስታውስ “አማራጮቼ ኑሮዬን በውጭ ሀገር ማድረግ አልያም ደግሞ ተምሬያለሁ ካልኩኝ እንደ አካባቢው ገበሬ ሆኜ ሌሎችን ገበሬዎች በማስተባበር ሁኔታውን መቀየር የሚል ነበር”። በዚህ ሃሳብ ነበር አሁን ለዓለም አቀፍ እውቅና የበቃው ሙሉ ኢኮሎጅ በጮቄ ተራሮች ላይ ሊመሰረት የቻለው። ሙሉ ኢኮሎጅ “የዓለም ትልቁ የማህበረሰብ መንደር ይሆናል ብዬ ነው የተነሳሁት” ሲል ወጣቱ የህልሙን ስፋት ይገልፃል።

አሁን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቱሪዝም ድርጅት ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው ሙሉ ኢኮሎጅ ጅማሬው በድንኳን ነበር። እየጠፋ የነበረውን ጫካ ከንክኪ ነፃ እንዲሆን ማድረግም ቀዳሚው እርምጃ የነበረ ሲሆን በአምስት ዓመታት ውስጥ በሚልየን የሚቆጠሩ ተክሎች እንዲያድጉ ምክንያት ሆኗል።

የሙሉ ኢኮሎጅ መስራች አብይ አለም እንደሚገልፀው የአካባቢው ህብረተሰብ ለስራው የነበረው ተነሳሽነት አስገራሚ የነበረ በመሆኑ አካባቢው በፈቀደው መጠን ለጎብኚዎች የማረፊያ ቦታ መገንባት ሲጀመር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጎብኚዎችን መጥራት መጀመራቸውን ይናገራል። በአካባቢው የሚሰራው ስራ ጎብኚዎችን ብቻ ሳይሆን ነዋሪ የሆነውን ህብረተሰብም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። 

“የተገነቡት የማረፊያ ጎጆዎች በአካባቢው ከሚገኙ ገበሬዎች ጋር የተሳሰረ ነው። የገበሬዎቹ ቤት የጓሮ አትክልት ያለው፣ በፀሀይ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የውሃ ሀብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም፣ በእርሻም ሆነ በእርባታ ስራቸው ጥራትና ብዛት እንዲያድግ፣ ሁለት ሶስት ዶሮ ክሚኖረው ለምን 50 እና 100 ዶሮ አይኖረውም? በርካታ ኪሎ ሜትሮች አቋርጦ የሚያገኘው ወፍጮ ቤት ለምን አጠገቡ አይኖርም? ህፃናት ቤታቸው ከሚውሉ ለምን አፀደ ህፃናት አይኖራቸውም? የሚሉ ሀሳቦችን እየፈታ ይገኛል። በዚህ ቦታ የተሰራው ስራ ዓለምን የሚያስተምር ነው” ይላል ወጣት አብይ አለም።

በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ኢኮሎጅ በተገነባበት የጮቄ ተራሮች እና አካባቢው የሎጁ መስራች የሆነው ወጣት አቢይ እና ያስተባበራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በርካታ ጠቀሜታዎች እያገኙ ሲሆን በቅርቡም አፀደ ህፃናት እና የቋንቋ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ተዘጋጅተው ክፍት ተደርገዋል።

“ሎጁ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መመረጡን ስሰማ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ” የሚለው አብይ “ሀሳቡ ነው እንጂ አሸናፊ የሆነው፤ ከዚህ የሚበልጡ መንደሮች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። “ብዙ ሰዎች ሞግተውኛል፤ አይሆንም፣ ሌላ ተልዕኮ ከሌላችሁ በስተቀር ይሄ የሚሆን አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ከተማሩ ሰዎችም፣ ከአካባቢውም እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች ተሰጥተውኛል። አሁን ይሄ እውቅና መሰጠቱ ረጅሙን ጉዟችንን ያሳጥርልናል ብለን እናምናለን” ሲል ከዓለም አቀፍ እውቅናው በኋላ ያለውን ተስፋ የኢኮሎጁ መስራች ይናገራል።    

እንደ ሀገር በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ሰላም መሆኑ እና የተሻለ የቱሪዝም መንደር ኖሯት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና መሰጠቱ የሚያኮራ ነው የሚለው አብይ አለም “በወጣትነቴ ይህን አስተዋፅኦ በማድረጌ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል” ብሏል። እውቅና መሰጠቱ የሙሉ ኢኮሎጅ ማሳያ እንዲሆን እንጂ በአካባቢውም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ብዙ መልማት ያለባቸው ቦታዎች ስለመኖራቸው ልብ ሊባል እንደሚገባ አብይ አለም ይመክራል።

ለዉድድሩ ዓላማ የሚሆን መረጃ በማሰባሰብ እና በሰነድ ማጠናከር በኩል ትልቅ ሚና የነበራቸውን አካላት ያመሰገነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር በመጪው ጥር ወር ከመንደሩ ተወካዮች ጋር በመሆን ሽልማቱን እንደሚረከብ አስታውቋል። ባሳለፍነው ዓመት በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የወንጪ ሀይቅ በ2021 ዓመት ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ተመርጦ እንደነበረ ይታወሳል።

አስተያየት