ኅዳር 2 ፣ 2012

የሀሰት ምስሎችን በእጅ ስልክ ማረጋገጥ

Fact checking

የተሳሳቱ እና አሳሳች መረጃ ስርጭቶችን ለማባባስ ምስሎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ሚስጥር አይደለም፡፡ ምስሎች ስሜታዊ ምላሽ ስለሚያነሳሱ፣ ማህበረሰቡ እውነተኛ…

የተሳሳቱ እና አሳሳች መረጃ ስርጭቶችን ለማባባስ ምስሎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ሚስጥር አይደለም፡፡ ምስሎች ስሜታዊ ምላሽ ስለሚያነሳሱ፣ ማህበረሰቡ እውነተኛ ውክልና እንዳላቸው የመቀበል አዝማሚያ አለው፤ በዚህም ምክንያት ምስሉን ወይም ከምስሉ ጋር የተያያዙ ማስፈጥጠሪያዎችን ለመክፈት እና ለማጋራት ቀላል ይሆናል፡፡ የሀሰት ወሬዎች የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተላለፍ የሀሰት ምስሎችን ይጠቀማሉ፡፡ የሀሰት መረጃዎችን የሚያበረታቱ እና የሚያትሙ ሰዎች ሆን ብለው ምስሎችን ከአውዱ ውጪ ይጠቀማሉ (የድሮ ፎቶዎችን በመጠቀም ወይም ፎቶዎችን በጽሁፍ ያልተገባ ትርጉም በመስጠት) ወይም በዲጂታል የፎቶ ማስተካከያ በመጠቀም አንባቢዎችን ያታልላሉ፡፡

ሀሰት ምስሎችን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል በአትዮጲያ የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው፡፡ በእውቁ የታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት[i]መሠረት በጊዜው በነበረ የፖለቲካ ሽኩቻ የአልጋ ወራሹ ልጅ እያሱ (እ.ኢ.አ 1895-1935) ተቃዋሚዎች አልጋ ወራሹ የሙስሊም ልብስ ለብሰው የሚያሳይ የሀሰት ፎቶ በመጠቀም በክርሲቲያኑ ባላባት እና በእርሱ አስተዳደር መካከል ልዩነት ለመፈጠር ተጠቅመውበት ነበር፡፡ ይሄም ከስልጣን እንዲወገዱ ምክንያት ሆኖአል፡፡ በተጨማሪም ንጉስ ሃይለስላሴ (እ.ኢ.አ 1911-1962) ከስልጣን ሊነሱ አካባቢ የሀሰት ምስሎች ንጉሱን ለማሳጣት ጥቅም ላይ ውለው ነበር፡፡

የሀሰት ምስሎች በዛሬይቷ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ላይም ማታለሎች እንዲፈጸሙ ምክንያት ይሆናል፡፡ ወደ አራት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ በኢትዮጲያ የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ማህበራዊ ሚዲያው ወሳኝ ሚና ነበረው፡፡ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ላይ በነበረው ጠንካራ ቁጥጥር ምክንያት፣ የተቃውሞ ሰልፎቹ የሚደራጁት እና ሪፖርት የሚደረጉት በማህበራዊ ሚዲያ፣ በተለይም በፌስ ቡክ አማካኝነት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጲያ  የማህበራዊ ሚዲያ ጥቅም ወሳኝነት ጨምሯል፣ በሚመጡት ዓመታትም እየጨመረ ይመጣል፡፡ በአዲስ ዘይቤ የተደረገ አነስተኛ ጥናት እንደሚያሳየውሀሰተኛ ምስሎች በዋናነት ለሚከተሉት ጥቅሞች ይውላሉ፡፡ 

1) የመንግስት ኃይልን ማጋነን

የሀሰት ምስሎች መንግስት በሰላማዊ ሰልፎች ላይ የሚሳተፉ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል ለማጋነን ይሰራጫሉ፡፡ የዚህም ዓላማ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ጣልቃ ገብነትንም ለመጠየቅ ነው፡፡ በሀሰተኛ ምስል የመንግስትን እርምጃዎች ማጋነን ተጨማሪ ሰልፎችን ለማደራጀትም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ የሰላማዊ ሰልፎችን ትልቅነትና እና የተሳታፊዎች ቁጥርም የሀሰት ምስሎችን በመጠቀም ተዛብተው ይቀርባሉ፡፡

2) የሰልፎችን ጥያቄ ማዛባት

የሀሰት ምስሎች በሰልፎች ጊዜም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይቻላሉ፡፡ ግለሰቦች በሰልፎች ላይ ተሳታፊዎች የያዙዋቸውን መፈክሮች ይዘት በመቀየር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያሰራጩ ይታያል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አስተዳደር የኢትዮጲያና ኤርትራ ድንበር ኮሚሲዮን የወሰነውን ውሳኔ ለመፈጸም መወሰኑን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሰልፍ ላይ የተቀየረው የመፈክር ይዘት ለዚህ ወሳኝ ምሳሌ ነው፡፡

በሰልፎች ላይ ያሉ መፈክሮችን ይዘት በመቀየር፣ የሰልፈኞቹን ጥያቄ ለማዛባት እና በሰልፈኞቹ እና በተዛባው ፎቶ ምክንያት እሴታችን ተዋርዷል በሚሉ ሌሎች ቡድኖች መካከል ግጭት ለማነሳሳትም ይደረጋል፡፡ ይሄም በብዛት በተሰራጩ የሀሰተኛ ምሰሎች ታይቷል፡፡ 

3) የብሔር ግጭቶችን ማባባስ

በብሔር ማንነቶች ምክንያት የሚደረጉ የቡድን ግጭቶች ለዛሬዋ ኢትዮጲያ ዋነኛ ተግዳሮት ነው፡፡ የብሔር ግጭቶች ለሺዎች ሞት እና ለሚሊየኖች የውስጥ መፈናቀል መንስኤ ሆነዋል፡፡ የሀሰት ምስሎች የአንዱን ቡድን ስቃይ እና ጉዳት አጋንኖ ለማቅረብ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ያልተፈጠሩ ግጭቶችም በሀሰተኛ ምስሎች ይዘገባሉ፡፡ እነዚህ የሀሰት ምስሎች የትኛው ቡድን ግጭቶችን እንደጀመረ፣ የትኛው ቡድን ደግሞ እራሱን ለመከላከል እርምጃ እንደወሰደ ትርክቶችን አቅጣጫ ያስይዛሉ እና የሀሰት ድንጋጤንም ይፈጥራሉ፡፡

የሀሰት ምስሎች ግጭት ጀምሯል በተባለው የብሔር ቡድን ላይ የበቀል እርምጃዎች ያነሳሳሉ፡፡ ይሄ አካሄድ በመንግስት ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ተስተውሏል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ስለተደረገ ጥቃት የተሰሩ ዘገባዎች በአንቦ ዩንቨርሲቲ የአማራ ተማሪዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጥር ምክንያት መሆናቸው ይታወሳል፡፡

4) የሀሰት ስኬቶችን አጋንኖ ማቅረብ

የመንግስት እና አጋር የመገናኛ ብዙሃኖች እውነት ያልሆኑ ስኬቶችን፣ ለእውቅና በሚል በተሳሳተ ምስል ያቀርባሉ፡፡ አዲስ እና የተጠናቀቁ የመንግስት ፕሮጀክቶችን በሚመለከት የተለያዩ የዜና ዘገባዎች ይቀርባሉ፡፡ በእነዚህ የዜና ዘገባዎች የሌላ ሀገር ፕሮጀክቶች በኢትዮጲያ ውስጥ የተፈጸሙ ለማስመሰል ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በስር የተገለጸው ምስል አንድ ምሳሌ ነው፡፡

5) የሚያላግጡ/በብዛት የሚታዮ ይዘቶች

አንዳንድ የሀሰት ምስሎች፤ ከስር የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ጭንቅላት በመቀየር እንደተደረገው፤ ለቀልድ ጥቅም ወይም ለማሾፍ በብዛት የሚታዩ ይዘቶችን የሚፈጥሩ እና የሚያሰራጩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  

እነዚህ የሀሰት ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ በብዛት በመሰራጨታቸው ምክንያት የመጀመሪያውን ምንጭ ለማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ማህበረሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ምስሎችን በፍጥነት እና በቀላሉ የሚያጣራበት አካሄድ ያስፈልገዋል፡፡ ከስር በእጅ ስልክ ላይ ምስሎች እንዴት እደሚጣሩ/እንደሚፈለጉ የሚያሳዩ ሁለት አካሄዶችን እናብራራለን፡፡

በእጅ ስልኮች ላይ ሀሰተኛ ምስሎችን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል

የምስል መፈለጊያ ማለት አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ምስሎች በሌላ ቦታዎች ላይ መታተማቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው፡፡ ይሄም ሁሉም አይነት ምስሎች የታተሙበትን ጊዜ ለማረጋገጥ እና፤ ምስሉ ከአውድ ውጪ ጥቅም ላይ መዋሉን ወይም ከዋነኛው ምስል መቀየሩን ማየት ይቻላል፡፡

ቲን አይን

ከስር ቲን አይን በሚባል አካሄድ ፎቶዎችን እንዴት ማጣራት አንደሚቻል ደረጃ በደረጃ ይብራራል፡፡     

1) ማጣራት የሚፈልጉትን ምስል ዋውረድ ወይም ማስቀመጥ፡፡ (አስቀምጥ የሚለው አማራጭ እስከሚመጣ ድረስ ምስሉ ላይ ተጭኖ መቆየት)

2) በአንድሮይድ ስልክ፤ ክሮም መክፈት ወይም ሌላ ማንኛውም የኢንተርኔት መጠቀሚያ መክፈት፣

3) ወደ www.tineye.com መሄድ እና ምስል ጫን የሚለው ላይ መጫን፣

4) ዶክመንት የሚለውን መምረጥ (ወይም በአንዳንድ አንድሮይድ ስልክ ላይ ፋይል የሚለውን መምረጥ)፣

5) በግራ በኩል ከሚገኘው ቦታ ጋለሪ የሚለውን መምረጥ እና የጫኑት/ሊጣራ የሚፈልጉትን ፎቶ መምረጥ፣

ለማሳያነት ጥቅም፣ ከታች ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከዘፋኟ ቤብስ ወዶሞ ጋር የሚደንሱበትን ፎቶ (የሀሰት) ተጠቅመናል፣

6) በመጡት ውጤቶች መሀል መሄድ እና ምስሉ ላይ የተለየ ይዘት ያካተቱ ምስሎችን መጎብኘት፡፡ የተገኙት ውጤቶች የተለጠፉበትን ጊዜዎች ማየት፡፡ የቆየው ፎቶ ዋነኛው ፎቶ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡

7) እንደምትመለከቱት በኖቪንበር 2016 ዓ.ም የተገኘው ምስል ያልተቀየረው ዋነኛው ፎቶ ነው፡፡

ጎግል ምስል

ምስል ካላቹህ እና ዋነኛው መሆኑን ለማወቅ ከፈለጋቹ፣ ሌላ ወሳኝ አካሄድ የጎግል ምስል መፈለጊያ ነው፡፡ ይሄ አካሄድ በኮምፒዩተር ላይ ለመጠቀም በበለጠ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ጎግል በስልክ ላይ ለመጠቀም የሚያስችልም አዘጋጅቷል፡፡ የሚቀጥለው ደረጃ በደረጃ አካሄድ በእጅ ስልክ ላይ ጎግል ምስልን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ያብራራል፡፡

1) ማጣራት የሚፈልጉትን ምስል ማውረድ ወይም ማስቀመጥ፡፡ (አስቀምጥ የሚለው አማራጭ እስከሚመጣ ድረስ ምስሉ ላይ ተጭኖ መቆየት)፣

2) በአንድሮይድ ስልክ፤ ክሮም መክፈት ወይም ሌላ ማንኛውም የኢንተርኔት መጠቀሚያ መክፈት፣

3) ከላይ መፈለጊያ ላይimages.google.comመጻፍ፣

4) ከላይ በስተቀኝ ላይ የሚገኘውን መቼት የሚለውን መጫን (3ቱን ነጥቦች) 

 5) እና ወደታች በማድረግ "የዲስክቶብ ሳይትን" ማጣራት፣

6) አሁን ፎቶ የመጫኛውን አማራጭ ይመጣል፡፡ የካሜራ ምልክቷን መጫን፣

7) ፎቶውን መጫን ወይም ማስፈንጠሪያ ማስገባት፡፡ ፎቶ መጫን የሚለውን መምረጥ እና ለማጣራት ያስቀመጡትን ፎቶ መምረጥ፣

8) ውጤቶቹን ወደታች እያሉ መመልከት እና ሌላ የተለየ ፎቶ መኖሩን ለማጣራት መሞከር፡፡

በብዛት የተጋሩ ይዘቶች ያሉት ምስሎችን በማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያቹህ ላይ በሚመለከቱበት ጊዜ፤ እውነቱን በእጅ ስልኮ ላይ እራሶ ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ቲን አይን እና ጎግል ምስል የሚባሉት አካሄዶች የተሳሳቱ እና የሚያሳስቱ መረጃዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ስለሚረዳዎት በኢንተርኔት መጠቀሚያዎ ላይ በማኖር (bookmark በማድረግ) በቀላሉ የሚያገኙበት ቦታ ላይ ያስቀምጧቸው፡፡ 

ይሄ ጽሁፍ የጥላቻ ንግግርን እና ሐሰተኛ መረጃ በኢትዮጲያ ያለበትን ሁኔታ ቅርጽ ለመስጠት በሰባ ደረጃ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኃላ.የተ.የግል ማኅበር፣ የአዲስ ዘይቤ እና ጎበና መንገድ አታሚ እና በኢንተርኒውስ፣ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ዜናዎችን እና መረጃዎችን እንዲያዘጋጁ ማገዝን አላማው ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ አለም አቀፍ ድርጅት ትብብር የሚዘጋጁ ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚዲያ ውጤቶች አካል ነው፡፡©በሰባ ደረጃ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኃላ.የተ.የግል ማኅበር2012 ዓ.ም.

[i]Pankhurst, R. 1992. The Political Image: The Impact of the Camera in an Ancient Independent African State. In Anthropology and Photography, 1869-1920 (ed.) E. Edwards. New Haven & London: Yale University Press in association with The Royal Anthropological Institute.

አስተያየት