ኅዳር 15 ፣ 2015

ታምራት ነገራ ዳግም ከሀገር ተሰደደ

ዜና

ታምራት ነገራ መንግስት የገባውን የሚዲያ ሪፎርም ቃል መሰረት ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ የጋዜጠኛነት ስራውን ቢቀጥልም የደረሰበት እስር እና መንጋላታት ዳግም ሀገሩን ለቆ እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ታምራት ነገራ ዳግም ከሀገር ተሰደደ
Camera Icon

ፎቶ፡ አዲስ ዘይቤ

የተራራ ኔትዎርክ ሚድያ መስራች እና ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ነገራ እና ባለቤቱ ሰላም በላይ ፣ የተራራ ኔትዎርክ ሚድያ ስራ አስኪያጅ፣ ከኢትዮጵያ መሰደዳቸውን አዲስ ዘይቤ ከምንጮቿ ማረጋገጥ ችላለች። ታምራትና ባለቤቱ ከሀገር የተሰደዱት ሰኞ፣ ኅዳር 12 2015 ዓ.ም. መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ዘይቤ ለታምራት ቅርበት ካላቸው ሰዎች መረዳት እንደቻለችው ታምራት ነገራ ከሀገር የወጣበት ምክንያት ከእስር ከተለቀቀ ሰባት ወራት ያስቆጠረ ቢሆንም በመንግስት በኩል እስካሁን ምንም ዓይነት ክስ አለመመስረቱ አልያም የክስ መዝገቡ ባለመዘጋቱ ይህም በድጋሚ የመታሰር ስጋት ስለተፈጠረበት እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሰራውን በነፃነት መቀጠል ባለመቻሉ ነው፡፡ 

ታምራት ነገራ ታህሳስ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ከእስር መለቀቁ ይታወሳል። 

ታምራት ነገራ ለስደት አዲስ አይደለም። በ2002 ዓ.ም. የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ መዳረሻን ተከትሎ በወቅቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ በመገናኛ ብዙሃንን የማፈን ዘመቻ በጀመረበት ወቅት፣ በምታቀርበው ሂሳዊ እና ጥልቅ ይዘት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘችው አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ታምራት እና የጋዜጣው መስራች ጓደኞቹ ዒላማ ሆነዋል። በዚህም ምክንያት የተፈጠረውን የእስር ስጋት ሽሽት ታምራት የስደት ኑሮውን በአሜሪካ ለማድረግ ተገዶ ነበር።

በ2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች እና ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ታምራት ወደ ሀገሩ መመለሱ አይዘነጋም፡፡ የኖርዌዩ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴም እ.ኤ.አ 2019 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት እውቅና ሲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን እንደመጡ  የሚዲያ ነፃነትን ለማሻሻል እና የሚዲያ ሳንሱርን ለማቆም የወሰዱት እርምጃ አንደኛው ምክንያቱ እንደሆን ጠቅሶ ነበር፡፡ 

ታምራት ነገራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ተራራ ሚዲያ ኔትዎርክ የተባለውን የግል ሚዲያ በማቋቋም በብሄር ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም ስርዓት ላይ ትችትና አስተያየቶችን መስጠት እንዲሁም የጎሳ ፖለቲካ አደገኛነት ላይ ጠንካራ ሂስ ሲያሰማና ትንታኔዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚህም ቀድሞ በአዲስ ነገር ከሚያወቁት አንባቢዎቹ ተጨማሪ አድናቂዎችን አትርፏል፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከቱ በኦሮሚያ ክልል አመራሮች ላይ ይሰነዝር ከነበረው ትችት ጋር ተደምሮ በባለሥልጣናት ጥርስ ውስጥ ሳያስገባው እንዳልቀረ ይታመናል።      

ታምራት ነገራ ባለፈው ዓመት ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ የታሰረ ሲሆን ለሰባት ቀናትም የት እንደነበረ ማወቅ አልተቻለም ነበር። በኋላም በኦሮሚያ ክልል በገላን ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ ለቤተሰቦቹ ተነግሯቸዋል። በተያዘበት ወቅትም የተለያዩ የተራራ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚጠቀማቸው ንብረቶችን ጨምሮ የግል ኮምፒዩተሩ፣ ስልክ እንዲሁም የሚዲያ ፕሮዳክሽን መሳሪያዎች በፖሊስ ተወስደዋል።

ታምራት ለ118 ቀናት በእስር ላይ በቆየበት ወቅት ብዙ የፍርድ ቤት ውሎዎች በታሰረበት ጉዳይ ላይ የተጠሩ ሲሆን ከእስር ሲፈታ ምንም አይነት መደበኛ ክስ አልተመሰረተበትም። የካቲት 24 በዋለው ችሎትም የኦሮሚያ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ሰነድ መሰረት “የኦሮሞን አንድነት መበታተን፣ እስከ እስሩ ድረስ ለዓመት በቆየው ጦርነት ለህወሓት ጥቅም የሚያስገኝ መረጃ ማሰራጨት፣ ስለ ጦርነቱ ሂደት የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት፣ 'ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ክብር ዝቅ በሚያደርግ መልኩ እየሰሩ' ነው በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም በማጥፋት” በማለት ተከሳሹ ህግን ተላልፎባቸዋል ያላቸውን እነዚህ ነጥቦች ዘርዝሯል።  

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ)ን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በታምራት ነገራ መታሰር ላይ ስጋታቸውን በማንሳት በተደጋጋሚ ከእስር እንዲፈታ ሲጠይቁ መቆየታቸውም ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የታምራት እስር በብሔር ወይም በፖለቲካ ምክንያት የተደረገ ነው የሚል እምነታቸውን ሲያንፀባርቁም ይታያሉ።

ሔዋን አለማየሁ የተባለች ፀሃፊ የታምራት ነገራን ጥረት በማድነቅ በፃፈችው ፅሁፍ “ስለ ታምራት የአክቲቪስትነት ስራ እና ትንታኔ ብዙ ማለት ይቻላል፤ አንዳንድ አስተያየቶቹ አከራካሪ ከመሆንም ባለፈ ችግር ፈጣሪ እንደሆኑ ሊታሰብ ይችላል። ነገር ግን የታምራት የምንጊዜም አላማው እና ግቡ ጠንካራ ሀገረ መንግስት እንዲኖር እና በብሄር ምክንያት መገፋፋት የሌለባት ነፃ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ነው” ስትል ተከራክራለች።

አስተያየት