የኢትዮጵያ እና የሱዳን መንግስታት ከአንድ ዓመት በላይ የቆየውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ታዋቂው የአረብኛ ጋዜጣ አሽራቅ አል አውሳት ዘግቧል።
ጋዜጣው በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግባቸውን በሰላም ለመፍታት ተሰማምተዋል።
አምባሳደሩ የሁለትዮሽ ድርድሩ ስለሚጀምርበት ጊዜ ፍንጭ ባይስጡም፣ "ኢትዮጵያና ሱዳን ከዚህ ቀደም የተፈራረሙት የድንበር ስምምነት በመኖሩ የሀገራቱ ባለስልጣናት እነዚህን የቀድሞ ስምምነቶች መሰረት አድርገው የወሰን ማስከበርና የግጭት ማስወገዱን ስራ ያከናውናሉ" ብለዋል።
በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ 2013 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በሚገኝ ኢትዮጵያውያን እና ሱዳናውያን አርሶ አደሮች ከ10 ዓመታት በላይ በጋራ የተጠቀሙት አልፈሻጋ በተባለ መሬት ላይ የአካባቢን ለምነት መሰረት ያደረገ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና "አሁን ባለው የሱዳን ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ጣልቃ አትገባም" ያሉት አምባሳደር ይበልጣል፣ "የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ፍላጎትና ጥያቄ ከሆነ ብቻ ለማደራደር ዝግጁ ናት" ብለዋል።
በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በተመለከተ ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የቀድሞ ስምምነት መሰረት የጋራ ጥቅማቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያ ለሱዳን በዝቅተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቦት እንደምትሰጥ አምባሳደሩ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ግድቡን በተመለከተ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ እንዲለሙ እና እንዲያድጉ ፍላጎቷ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።