ኅዳር 11 ፣ 2014

በአማራ ክልል ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች መሰረታዊ የሰብዓዊ ድጋፎች ባለመቅረባቸዉ ዜጎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል ተባለ

City: Addis Ababaዜና

በአማራ ክልል ህወሓት የያዛቸው አካባቢዎች መሰረታዊ የሰብዓዊ ድጋፎች መቅረብ ባለመቻላቸው ዜጎች የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በአማራ ክልል ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች መሰረታዊ የሰብዓዊ ድጋፎች ባለመቅረባቸዉ ዜጎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል ተባለ

በአማራ ክልል ህወሓት የያዛቸው አካባቢዎች መሰረታዊ የሰብዓዊ ድጋፎች መቅረብ ባለመቻላቸው ዜጎች የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

የዋግኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ዞን በከፊል በእዚህ ወቅት በህወሓት የተያዙ አካባቢዎች ሲሆኑ መሰረታዊ የምግብና መድኅኒት ድጋፍ ባለመኖሩ ለሞት፣ ለአስከፊ ረሃብና ከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ አካባቢዎች ናቸው ተብሏል።

“በአንድ ሀገር ውስጥ ያለመድልኦና ያለመገለል አገልግሎት መስጠትን መርሃቸው አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ የሚጠበቁት መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከዓላማቸው በተቃራኒ መቆማቸው ሰብዓዊ ቀውሱን አባብሶታል” ሲሉ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ህዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ የተገለጸውን እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱንና አብዛኛውን ድጋፍ ህወሓት መጠቀሙን ዋቢ ያደረጉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው እርዳታው መልካም ቢሆንም ያለመድልዎ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።

ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ በርካታ ተፈናቃዮች በደቡብ ወሎ በደሴ ከተማ መጠለላቸው የሚታወስ ነው። የጦርነቱ መስፋፋት በመቀጠሉ በደሴ ከተማ የነበሩ ተፈናቃዮች ከሞላ ጎደል ተበታትነዋል ያሉት ኃላፊው አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ፈልሰዋል ብለዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በአማራ ክልል ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት የምግብና መድኅኒት ድጋፍ እስካሁን አላቀረቡም።

ይሁን እንጂ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የተሻለ ነው ተብሏል።

“ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች ከሰብዓዊነት ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎት የሚተገብሩበት አሰራር መከተላቸው አሳዛኝ ነው” ያሉት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ የሰብዓዊነት መርህን መከተል የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን መርሃቸው በመሆኑ በተለይም የምግብና መድኅኒት ድጋፍ ማድረግ ይደር የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ህወሓት ከያዛቸው አካባቢዎች ውጭ ባሉ ስፍራዎች አየተስፋፋ በመጣዉ ግጭት ቁጥር ወደ 2.1 ሚልየን አድጓል ያሉት አቶ እያሱ መስፍን በደብረ ብርሃን ከተማ 218,955 ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም ጦርነቱ እስካልቆመ ድረስ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል ብለዋል። ተፈናቃዮችን በመደገፉ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጡ የሚገኙት የክልሉ ነዋሪዎች ሲሆኑ 98 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በዘመድ አዝማድና በፈቃደኛ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ተጠልለው ይገኛሉ።

ቀሪው 2 በመቶ ማለትም ከ41 ሺህ የማይበልጡት ተፈናቃዮች ደግሞ በክልሉ በሚገኙ 32 ጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ።