ጥቅምት ሁለት- የአፄ ምኒሊክ ክተት ጅማሬ በጉዞ አድዋ መነፅር

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጥቅምት 2 ፣ 2014
City: Addis Ababaዜና
ጥቅምት ሁለት- የአፄ ምኒሊክ ክተት ጅማሬ በጉዞ አድዋ መነፅር

“. . .እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም. . . የሀገሬን ከብት ማለቅ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር . . . ያገሬ ሰው . . . ዘመቻዬ በጥቅምት ነው እና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።”

ይህ ቃል መስከረም 17 ቀን 1888 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በመውረር በቀኝ ግዛቱ ስር ለማዋል ማሰቡን በማረጋገጣቸው፤ በጣሊያን የወረራ ዝግጅት በመቆጣት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ያሳሰቡበት የክተት አዋጅ ነበር። 

አዋጁም ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩትና በሚያስተዳድሩት የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እንዲሁም በየግዛቱ ባሉ የጦር መሪዎቻቸው፣ መኳንንቶች፣ የጦር አበጋዞች፣ በራሶች እንዲሁም በደጅ አዝማቾች በኩል በዛው ወቅት በየአካባቢው ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲነገርም አስደረጉ። ከዚያም የንጉሡን የክተት አዋጅ ሰምቶ ከየአካባቢው የተሰባሰበው ጦር ወደ ሰሜን ዘመቻ ለማድረግ ጥቅምት 2 ቀን 1888 ኹለት ሰዓት ሲል ከአዲስ አበባ የአራዳ ጊዮርጊስ መናገሻ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት በመያዝ ወደ ዘመቻው ለመትመም ተነሳ። 

ዛሬ ዛሬ አያቶቻችን የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ወደ አድዋ ዘመቻ ጉዞ የጀመሩበትን የጥቅምት 2 ታሪካዊ ቀንን ለማስታወስ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ልዩ ልዩ መሰናዶዎች ይሰናዳሉ። ከእነዚህም መሰናዶዎች መካከል ላለፉት 8 ዓመታት ወደ አድዋ የእግር ጉዞ ያደረገው ጉዞ አድዋ ይገኝበታል። 

ባሳለፍነው አመት በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰዉ ግጭት ምክንያት ተጓዦቹ ወጣቶቹ ወደ ዋናው መዳረሻቸው ሳይደርሱ  መመለሳቸው የሚታወስ ነው።

የዝግጅቱን ዋና አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ “ዘንድሮ ጉዞ ይታሰባል ወይ?” ስትል አዲስ ዘይቤ ላቀረበችለት ጥያቄ “አዎን የ2014 ጉዞ ዓድዋ መርሐ ግብር የድሉን 126ኛዓመት በመዘከር ለ9ኛ ጊዜ ለመጓዝ የካቲት አንድ ለመጀመር ታቅዷል፣ ይህንንም ዛሬ ከሰዓት በሚኖረን ልዩ ዝግጅት እናሳውቃለን” የሚል ምላሽን አግኝታለች።

በመሆኑም “ታዲያ ለጉዞው ወቅታዊው የአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ተግዳሮት አይሆንበትም ወይ፣ ከአምናው አንጻርስ እንዴት ታዩታላችሁ” በማለት ለጠየቅነው ጥያቄ ያሬድ ሲመልስ “አምና ካጋጠመን ሁኔታ አንፃርም ሆነ አሁን ያለውን ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው ወደ መዳረሻው አድዋ ላንገባ እንችላለን ነገር ግን ወረኢሉ ለመክተም እቅድ ይዘን እንጓዛለን” ብሏል።

እንደ ያሬድ ገለጻ ምንም እንኳን ተጓዦቹ ከዚህ ቀደም ወደ ወረኢሉ ተጉዘው አለማወቃቸው እና ቦታው ለጉዞ የሚኖረው አስቸጋሪነት ግልፅ አለመሆኑ እንደ ተግዳሮት ሊታይ ቢችልም ይህ ጉዞ ግን ከዓመት ዓመት መቋረጥ ስለሌለበት እና ባሉት ሁኔታዎች ሁሉ እንዲቀጥል መደረግ ስላለበት ዘንድሮ በዚህ መልኩ ይዘከራል።

ከዘንድሮው ጉዞ እና አከባበር ጋር በተያያዘ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ እና ሰራዊታቸው የታላቁን ዓድዋ ዘመቻ “ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት!” ታውጆ ወደ ዓድዋ ጉዞ የጀመሩበት 126ኛ ዓመት መታሰቢያ ልዩ መሰናዶ በግዮን ሆቴል ግሮቭ ጋርደን ዎክ መናፈሻ ዛሬ  ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ከ10 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው ፕሮግራም ስለጉዞው ሁኔታ መግለጫ መሰጠቱን አዲስ ዘይቤ አጣርታለች።

በፕሮግራሙም ልክ በየዓመቱ እንደሚደረገው የአምና ጉዞ አድዋ ተጓዦች የክብር አርበኝነት ማዕረግ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አግኝተዋል። በተጨማሪም እለቱን የሚያወሱና የሚዘክሩ የሙዚቃ፣ የስነግጥም እና የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን የጋቢ ቻሌንጅ መርሐ ግብርም በይፋ ተከፍቷል። 

የጋቢ ቻሌንጅ በ2013 ስምንተኛው ጉዞ አድዋ ላይ የተጀመረ ሲሆን የሀገሪቱን ውብ ባህል ለዓለም ከማስተዋወቁ እና በራስ ምርት ማማር እንደሚቻል ከማሳየቱ ባሻገር ለሸማ ሙያተኞች ተጨማሪ የገበያ እድልን በየአመቱ የሚጨምር፣ የዓድዋ ዘማቾች በጊዜው የነበራቸውን አለባበስ የሚያወሳ እና የባህል ዘርፍን ማትጊያ እንቅስቃሴ መሆኑን ያሬድ ይናገራል።

አያይዞም ስለ ዘንድሮው ጉዞ ምልከታውን ሲያስቀምጥ የመጀመሪያው የጉዞ ዓድዋ መርሃ ግብር 5 ተጓዦችን፣ በኹለተኛው 6፣ በሦስተኛው 12፣ በአራተኛው ሀገሪቱ ላይ ሁከት የነበረበት ወቅት ስለነበር 8፣ በአምስተኛው 25፣ በስድስተኛው 48 ፣ በሰባተኛው 63 እና በ2013ቱ እና በሰባተኛው 86 ተጓዦች በጉዞው መሳተፋቸውን በመጥቀስ የአሁኑም አመት የተጓዦች ቁጥር ሊያድግ እንጂ ሊቀንስ እንደማይችል ተስፋ እንዳለው ይናገራል።

“የጉዞ ዓድዋ ግብና ስኬት ምን ይመስላል? ወደ ዓድዋ ተራራ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚፈለገው ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል ወይ” ስንል ላነሳንለት ጥያቄም ‹‹አንድ ትንሽዬ ጠጠር አንድ ኮረት ትነካለች፣ ያ ኮረት አንድ አሎሎ ነገር ይነካል፣ አሎሎው ድንጋይ ይነካል እያለ ትልቁ አለት መጨረሻ ሊንቀሳቀስ ይችላል። ስለዚህ ክብሪቱን እንደመለኮስ ጉዞ አድዋ፤ ለዚህ ላለንበት ዘመን እንቅስቃሴ የአድዋ ድል የበለጠ ክብር እና የበለጠ ቦታን እንዲይዝ ለማድረግ፤ በትውልድ ውስጥ የወጣቱ ርዕሰ ጉዳይ ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው ብለን እናምናለን።  ባሰብነው ልክም በየዓመቱ እያደገ መሄዱንም አስተውለናል። ግን እኛ ብቻ ነን ይሄን ያደረግነው ብለን አናስብም። ምክንያቱም እኛ ይሄን ጉዞ ከጀመርን በኋላ ብዙ ሰዎች ውስጥ መነሳሳት በመፈጠሩ የሁሉም ድምር ውጤት ነው። ከኛ በቀደመው ጊዜ በተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች የአድዋ ድል በየትውልዱ ላይ እንዲኖር ያን ችቦ እንዳይጠፋ እያቀጣጠሉ ያቀባበሉ አሉ፣ በመሆኑም ሁሉም ባደረገው ቅብብሎሽ የአድዋ ድል በዓል የበለጠ ትኩረት እያገኘ እየሄደ ነው” ይላል።

በሌላ በኩል የጉዞ አድዋ ቀንደኛ ተሳታፊ የሆነው እና በባዶ እግሩ በመጓዙ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው ወጣት ኤርሚያስ መኮንን ለዚህ ጉዞ ተግዳሮት ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አድዋን ለመበሻሸቅ የሚጠቀሙበት ሰዎች መኖራቸው ነው ይላል፣ “የአድዋ ድልን የኔ ብቻ ድል ነው በማለት ሁሉም ወደ ሰፈሩ ለመጎተት የመሞከር ነገር መታየቱ የጎንዮሽ ጉዳት አለው” የሚለው ኤርሚያስ ድሉ የሁላችንም በመሆኑ የእኛ ነው የሚል መንፈስ አሁንም መነገር ያለበትና ሊባል የሚገባው ነገር መሆኑን እና ዳግማዊ አፄ ሚኒልክን የምናደንቅበት ብልህነታቸውን የምናሞግስበት አንደኛው ምክንያት እነዛን ሁሉ ታላላቅ የጦር ጀብደኞች አንድ ቦታ ማሰለፍ በመቻላቸው ነው ይላል። 

“በጉዞ አድዋም ከክተት አዋጁ ጀምሮ ጥቅምት ሁለት ጉዞ መጀመሩን በማውሳት ማክበሩ የሁሉም ጀግኖች ድርሻን የሚያጎላ መልክ አለው ብዬ አስባለሁ” ሲል ጉዞ አድዋ ላይ ሁሉም ተጓዥ ጉዞውን በሚጨርስበት ጊዜ ካነበበው፣ ከተማረው በመንገዱ ላይ ካገኘው እውቀት እና ታሪክ በመነሳት አንድ የጀግና ሥም እንዲወስድ እና ራሱን በመሰየም እንዲያስተዋውቅ ለማድረግ እንደሚሞከር እና አድዋ የሁሉም መሆኑን ለማሳየት ሁሉንም የሚያጠቃልል ታሪክ እንደሚሰራ አብራርቷል።

በመሆኑም ዋና አስተባባሪው ያሬድ አሁን ያለንበት ትኩሳት አልፎ ቢያንስ በአስረኛው ጉዞ ላይ የአድዋ ድል የአፍሪካዊያን ድል በመሆኑ ሌሎች አፍሪካዊያን ሀገራት እንዲሳተፉበት ማድረግ እቅዳችን ነው ይላል  “የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት እድልን እራሱ ብዙዎች እየፈለጉት ሳለ እኛ አግኝተነው አልተጠቀምንበትም። ስለዚህ የጀመርነውን ዝግጅት አጠናክረን አስረኛው ጉዞ ላይ ከጥቅምት ሁለት ጀምሮ ከአፍሪካውያን ጋር እናከብረዋለን” ሲል ለወደፊት የተሰነቀውን ግብም ነግሮናል።

“ጥቅምት ሁለትን መዘከር የጀመርነው የአድዋን ድል ያገኘነው አንድ ሆነን ስንነሳ በመሆኑ ነው” የሚለው ያሬድ ድሮ መዘጋጃ ሜዳ የሚባለው ስፍራ ላይ ተከልሎ የነበረውን ቦታ በመቀበል አሁን ወደ የአድዋ ማዕከልነት እንዲቀየር እየተሰራበት እንደሚገኝ በማውሳት ለዚህ ግንባታ ይህ ቀን መዘከሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው እና በቦታው ላይ ማዕከሉ እንዲገነባ የመሠረት ድንጋይ የተጣለውም 2012 ዓ.ም በዚሁ ታሪካዊ ቀን ጥቅምት ሁለት መሆኑንም ያስረዳል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.