የካቲት 30 ፣ 2015

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የመረጃ ነፃነት መብት እንዲያከብር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

City: Addis Ababaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ኔትብሎክስ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት በወጣ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ኢንተርኔት በተዘጋባቸው እያንዳንዱ እለት ቢያንስ 4.5 ሚልየን ዶላር እንደምታጣ ይገልፃል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የመረጃ ነፃነት መብት እንዲያከብር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

የኢትዮጵያ መንግስት ለአንድ ወር በተመረጡ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያዎች ላይ የጣለውን እገዳ በማንሳት የዜጎችን መብት እንዲያከብር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ለአንድ ወር ያህል በፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክን በመሳሰሉ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያዎች ላይ የጣለው እገዳ የዜጎችን መረጃ የማግኘት እና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የጣሰ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)ም በዛሬ እለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ምክኛቱን ለህዝብ ሳያሳውቅ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጡ ተገቢነት የሌለው ድርጊት ነው ሲል ተችቷል። ኢሰመጉ እንዳስታወቀው የሰዎችን መረጃ የማግኘት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መንግስት ከመጋፋቱም ባለፈ “በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ” ይገኛል ሲል አሳስቧል።

ቶፕቴን ቪፒኤን የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ያለፈው 2022 ዓመት ሪፖርቱን ሲያወጣ ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ145 ሚልየን ዶላር በላይ ማጣቷን አስነብቦ ነበር። በሌላ በኩል በ2019 የአውሮፓዎች ዓመት ኔትብሎክስ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት በወጣ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ኢንተርኔት በተዘጋባቸው እያንዳንዱ እለት ቢያንስ 4.5 ሚልየን ዶላር እንደምታጣ ይገልፃል።

“ይህ በተመረጡ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ያለው እገዳ የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና መረጃ የማግኘት መብቶችን በግልፅ ይጥሳል” ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት እና ብሔራዊ ሕጎችን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸውን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የጣሰ መሆኑን ገልጿል።  

“እገዳው ሀገሪቱ በመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ላይ ያላትን አስከፊ ታሪክ የበለጠ ያበላሻል” ያለው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይህን እገዳ ሳይዘገዩ እንዲያነሱት እና በሰዎች ሀሳባቸውን የመግለጽ እና መረጃ የመቀበል መብት ላይ ጣልቃ የመግባት ባህሉን እንዲያቆም ሲል አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ወር በፊት ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ወደ ውጥረት በማደጉ እና የእምነቱ አባቶች እና መሪዎች ለሀገር አቀፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፎች ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ነበር ልክ የዛሬ ወር የተመረጡ የማህበራዊ ሚዲያ መተግብሪያዎች የታገዱት።

ሁለቱ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የመብቶች ተሟጋች ተቋማት የኢንተርኔት እገዳው አሁንም መቀጠሉ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት በአስቸኳይ ችግሩን እንዲፈታ አሳስበዋል። 

አስተያየት