ታህሣሥ 30 ፣ 2013

ምስሉ ከአዲግራት ጥሕሎ የዘረፈውን የኤርትራ ወታደር ያሳያል?

HAQCHECKFact checking

ሀቅቼክ ምስሉን ከመረመረ በኋላ የፌስቡክ ጽሁፉ ላይ እንደተገለፀው የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሲሰርቅ የሚያሳይ ምስል እንዳልሆነ አረጋግጧል። ስለዚህ የፌስቡክ ጽሁፉ ምስሉን በተሳሳተ መንገድ በማቅረቡ ስላቅ ተብሎ ተፈርጇል።

Avatar: Hagos Gebreamlak
ሓጎስ ገብረኣምላኽ

A fact-checker at HaqCheck, he has worked for Fortune as a reporter previously.

ምስሉ ከአዲግራት ጥሕሎ የዘረፈውን የኤርትራ ወታደር ያሳያል?

ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም Tirhas Tesfay የተሰኘ የፌስቡክ አካውንት በፌስቡክ ገጹ ላይ ከዚህ በታች ያለውን ምስል አንድ የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሰረቀ ከሚል ጽሁፉ ጋር አያይዞ በፌስቡክ ልጥፉ አጋርቷል። በትግርኛ የተፃፈው የፌስቡክ ጽሁፍ “ሰበር ዜና: አንድ የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሲሰርቅ በአይኔ አይቻለሁ” ይላል። ጥሕሎ ከገብስ ዱቄት የሚሰራ በሰሜን ምስራቅ የትግራይ ክፍልና በደቡብ ኤርትራ የሚዘወተር ባህላዊ ምግብ ነው። ልጥፉ በፌስቡክ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቶ ምስሉ እስከተጣራበት ጊዜ ድረስ 184 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አጋርተውታል። ሀቅቼክ ልጥፉን ከመረመረ በኋላ ምስሉ ከአዲግራት ጥሕሎ የሰረቀ የኤርትራ ወታደርን እንደማያሳይ አረጋግጧል። በመሆኑም የፌስቡክ ልጥፉን ስላቅ በማለት ፈርጆታል።

በትግራይ ክልል ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በህወሃት በሚመራው የታጠቁ የክልል ኃይሎችና በፌደራል  መንግስት በሚመሩ ኃይሎች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። የክልሉን አለመረጋጋት ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደርን በመደገፍ የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ላይ ተሳታፊነት እንደነበራቸው የሚገልፁ የተለያዩ ክሶች እና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ቀርበዋል። በተጨማሪም ብዙዎች በጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ውስጥ ዘረፋ እያካሄዱ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው ከአዲግራት ጥሕሎ የሰረቀ ኤርትራዊ ወታደር እንደሆነ የሚገልፅ አንድ የፌስቡክ ልጥፍ ብቅ ብሏል። ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የምስል መመርመሪያ ዘዴን በመጠቀም የምስሉ አመጣጥ ሲጣራ ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ናይሮቢ ኒውስ  Nairobi News በተባለ የኬኒያ የዜና እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋም መሆኑ ታውቋል። በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው (ፎቶ አንሺ ኤቫንስ ሀቢል) የኬኒያ መንግስት  በናይሮቢ ከተማ የተገነቡ  ህገወጥ ቤቶችን በሚያፈርስበት ወቅት ከመኖሪያ ቤቱ ኡጋሊ  (የኬንያ ገንፎ) ያዳነ አንድ የኬንያ ዜጋ ነው። በ Nairobi News  ላይ የታተመው የሰውየውን ታሪክ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይቻላል።

  

ይህ የፌስቡክ ጽሁፉ በወጣበት ወቅት በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት የኤርትራ ጦር በጦርነቱ ላይ ተሳታፊ እንደነበረና በርካታ ዘረፋዎችም እንደነበሩ የሚገልጹ የተለያዩ ክሶችና ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ሲቀርቡ ነበር። ነገር ግን ሀቅቼክ ምስሉን ከመረመረ በኋላ የፌስቡክ ጽሁፉ ላይ እንደተገለፀው የኤርትራ ወታደር ከአዲግራት ጥሕሎ ሲሰርቅ የሚያሳይ ምስል እንዳልሆነ አረጋግጧል። ስለዚህ የፌስቡክ ጽሁፉ ምስሉን በተሳሳተ መንገድ በማቅረቡ ስላቅ ተብሎ ተፈርጇል። 

አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ

አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ

ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

አስተያየት