መስከረም 11 ፣ 2015

ዱሬቲ እና ጌታዬ፡ ተስፋ የተጣለባቸው ሰዓሊዎች በሐዋሳ

City: HawassaArts/Culture

ሁለቱም ወጣቶች ታዋቂውን ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማን አርአያ አድርገው በተፈጥሮ ገጽታዎች እና የሚያዩትን አመሳስለው በመሳል እውቅናን እያገኙ ነው

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ዱሬቲ እና ጌታዬ፡ ተስፋ የተጣለባቸው ሰዓሊዎች በሐዋሳ
Camera Icon

ፎቶ: ኢያሱ ዘካሪያስ

ዱሬቲ ቤት የደረስነው ሐሙስ እለት ጠዋት 4 ሰዓት አካባቢ ነበር። ጊዜዉ ክረምት እንደመሆኑ የሐዋሳ ከተማ አየሩ ብርዳማ ሆኗል። በተለምዶ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘዉ የዱሬቲ በየነ ወላጆች ቤት ስንገባ የ19 አመቷ ሰዓሊ ብርዱንና ጭጋጉን በሚያስረሳ ሞቃት ፈገግታ ነበር የተቀበለችን።  

ሐዋሳ ያፈራቻት ይህች ወጣት ሰዓሊ የምታያቸውን ነገሮች አስመስላም ሆነ ከምናቧ በማፍለቅ የምትሰራቸው የፈጠራ ስራዎች አሁን አሁን ከተማው ውስጥ ታዋቂነትን እያስገኘላት ነው። 

ገና ወደ መኖሪያ ግቢው ለሚገባ ሰው መጀመሪያ ቀልቡን የሚስበው የተፈጥሮ ዉበት ላይ ተመስርተው የተሰሩና በጥንቃቄ የአጥሩ የውስጠኛው ግንብ ላይ የተሰቀሉ ስዕሎች ናቸው። 

ዱሬቲ ስዕሎቿን ለመሳል የምትጠቀመባቸዉን እቃዎች አስተካክላ ወደ ስራዋ ለመግባት ስትዘጋጅ ነበር ያገኘናት። ቀለሞቿን፣ ብሩሾቿንና በአራት ማዕዘን በተወጠረ ነጭ አቡጀዲ ጨርቅ (ሸራ) አቅርባለች። 

ወደዚህ ሙያ እንዴት ልትገባ እንደቻለች በማንሳት ጨዋታችንን ጀመርን። ወደስዕል ስራ የገባሁት "በአጋጣሚ" ነዉ ትላለች ዱሬቲ።  

"አስረኛ ክፍል እያለሁ የአለም አርት ትምህርት ቤት ባለቤት የሆነችዉ አለም ጌታቸው የተባለች ሰዓሊ በቴሌቪዥን በአጋጣሚ ስራዎቿን ስታቀርብ ተመለከትኩ። ወዲያው ለቤተሰቦቼ በማማከር ወደ አዲስ አበባ ሄድኩኝ እዛም ለሁለት ወራት ተማርኩኝ። ትምህርቱ ከልጅነቴ ጀምሮ ያለኝን የስዕል ፍላጎት በደንብ ማዉጣት እንድችል አግዞኛል" በማለት አጀማመሯን ታስታዉሳለች። 

ዱሬቲ የስዕል ትምህርት ቤት ገብታ መማር ፍላጎቷ ቢሆንም የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዉጤቷ ግን ዝቅተኛ በመሆኑ እንደተመኘችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ገብታ የስዕል ትምህርቷን መከታተል አላቻለችም።  

ይሁን እንጂ ሐዋሳ በሚገኝ አንድ የግል ኮሌጅ የማርኬቲንግ ትምህርት በቅዳሜ እና እሁድ መርሃ ግብር እየተከታተለች ትገኛለች። “ትምህርቱን የምከታተለው የመጀመሪያ ምርጫዬ ሆኖ ሳይሆን በሆነ የትምህር መስክ መማርና ወረቀት ማግኘት ስላለብኝ ነዉ” የምትለው ሰዓሊዋ ዱሬቲ ስዕል (አርት) ለእርሷ ልዩ ቦታ እንዳለው አጫውታናለች። 

ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ እና ከዚህ ቀደም ተስለው ያላየቻቸውን ምናባዊ ምስሎችን በመያዝ የእራሷን ፈጠራ ታክልበታለች። 

"ስዕል በምሰራበት ወቅት አብዛኛዉን ጊዜ የምመርጠዉ ፀጥ ያለ ስፍራ እና ለስለስ ያለ ሙዚቃ ነዉ” ትላለች ዱሬቲ። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ስዕል ሰርታ ለመጨረስ ከሁለት ቀን እስከ አንድ ሳምንት ድረስ እንደሚፈጅባት አጫዉታናለች።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በስዕል ጥበብ አንቱታን ያተረፉ በርካታ ሰዓሊያን እንዳሉ ይታወቃል። ለአብነትም የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ መዝገቡ ተሰማ፣ አለም ጌታቸዉ ተጠቃሽ ናቸዉ። 

ዱሬቲ እንዳጫወተችን መዝገቡ ተሰማ እና ዓለም ጌታቸው ለእርሷ ትልቅ ቦታ አላቸዉ። የእነርሱን ስራ እያየች እንዳደገችና ለሙያዉ ትልቅ ፍላጎት እንዲኖራት እንዳደረጓት አንስታልናለች። እስካሁን ከ300 በላይ ስዕሎችን ሰርቻለሁ የምትለዋ ወጣቷ የሰዉ ስዕል እና ለቤት ዉስጥ ማስዋቢያ የሚሆኑ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸዉ ስዕሎች እንደ መጠናቸዉ ቢለያዩም  ከ 2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በሚደርስ ዋጋ ለስዕል አድናቂዎች እንደምትሸጥ ገልፃልናች። 

ዱሬቲ በዋናነት ለስዕል ከምትጠቀምባቸው እቃዎች መካከል በአራት ማዕዘን እንጨት የተወጠረ (ሸራ) ነጭ አቡጀዲ ጨርቅ ፣ የተለያዩ ቀለም ያላቸዉን የመሳያ ቀለማት ፣ ብሩሾች እና ቀለሞች የሚደባለቁበት ዝርግ ሰሃን ይገኙበታል። 

በሐዋሳ ከተማ ለስዕል ስራዎቿ አስፈላጊ የሆኑ እቃዎችን አለማግኘቷ እና በእዛዉ ልክ መወደዳቸዉ ተግዳሮት እንደሆነባት ዱሬቲ አንስታልናለች። "የመሳያ ቀለሞች ማግኘት የሚቻለው አዲስ አበባ ነዉ እዚህ ሐዋሳ ላይ የለም ፤ ስድስቱ አክሪሊክ ቀለሞች የሚሸጡት 750 ብር ሲሆን መቀቢያ ብሩሽ ደግሞ ከ400 ብር ጀምሮ ነዉ" ትላለች ሰዓሊዋ በአብዛኛው በገንዘብ እንዲሁም በሀሳብ የቤተሰቦቿ ድጋፍ እንዳልተለያት ጨምራ በመግለጽ። 

በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት እና በሰዎች ጥቆማ የስዕል ስራዎቿን በማዉጣት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገቢ ማግኘት እና በትዕዛዝ መሳልም ጀምራለች። 

ጌታዬ ልንገርህ ሌላው ሐዋሳ ውስጥ ያገኘነው ወጣት ሰዓሊ ነው። ትዉልዱና እድገቱ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የሆነው እና በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በማታ ፈረቃ መርሃግብር እየተከታተለ የሚገኘዉ ጌታዬ "የስዕል ስራ ሙያ ብቻ ሳይሆን ተሰጥኦ እና ጥበብ ነዉ" የሚል እምነት እንዳለዉ ይናገራል። 

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ስራዎቹን አስመልክቶ ቆይታ ያደረገዉ ጌታዬ ከአንድ ዓመት በፊት አነስተኛ ቤት በ 3 ሺህ በር ተከራይቶ የስዕል ሙያን ዋና ስራው እንዳደረገ አጫዉቶናል። 

በአቅራቢያው እቃዎችን በመግዛት የሚረዳዉ ደጋፊ ባለመኖሩ የስዕል ሙያዉን ወደ ገንዘብ መለወጥ እንደነበረበት ሲገልጽም "ከጓደኞቼ ላይ ስዕል ለመሳያነት የሚያገለግሉ ብሩሾችን እና ሌሎች አስፈላጊ እቃዎችን በመዋስ አነስተኛ ቤት በመከራየት መስራት ጀመርኩኝ ፤ እነዚህ ስዕሎችን ሰዎች መግዛት ሲጀምሩ በምትኩ እራሴን ማደራጀት ጀመርኩኝ" ብሏል።

ከልጅነቱ ጀምሮ ሲሞገስበት የቆየዉን የስዕል ጥበብ ለማሳደግ ከአንድ ዓመት በፊት በዩቱብ ላይ ለአራት ወራት ያክል እንዴት የስዕል ቀለሞችን መቀላቀል እንደሚቻል እና ብሩሾቹ በምን መልኩ በሸራ ላይ ማረፍ እንዳለባቸው ቪዲዮ እያየ መለማመዱን ያስታዉሳል።

አሁን ላይ ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን ስዕሎችን በመስራት ህይወቱን እየመራ ይገኛል ። የቤት ኪራይ ፣ ለመሳያነት የሚያገለግሉ ዕቃዎችን ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ጨምሮ ሌሎችን ወጪዎች የሚሸፍነዉ ስዕል እየሰራ በሚያገኘዉ ገቢ ነው። ወጣቱ ከሚሰራቸው መካከል ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸዉ ፣ ከፎቶ የተገለበጠ የሚመስል የታዋቂ ሰዎች ምስል እና በቅርቡ ደግሞ በቆዳ ላይ ስዕሎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆን ተመልክተናል።  

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሰዓሊያን መካከል ልክ እንደ ዱሬቲ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማን አርአያዬ ነዉ ይላል። “ከልጅነት ጀምሮ ለተማሪዎች በትምህርት ቤት ዉስጥ የተለያዩ ስዕሎችን ፣ ድርብ ፊደላትን በመስራቴ የወደፊቱ እጣ ፈንታህ ሰዓሊ መሆን ነው ይሉኝ ነበር፣ ምርቃቱ የደረሰ ይመስለኛል” ብሎናል። 

ከዱሬቲ በተለየ ጌታዬ እንደነገረን በአሁኑ ሰዓት በስዕል ስራውም ሆነ በትምህርቱ የሚችለውን እየሰራ ይገኛል። “በአንዱ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን አልፈልግም፤ በትምህርቱም በስዕል ስራዉም ዉጤታማ ለመሆን እፈልጋለሁ" የሚለዉ ጌታዬ በስዕል ስቲዲዮው ካሉት ጋር በአንድ ላይ እስካሁን ከ 200 በላይ የስዕል ስራዎች አሉኝ ብሎናል። 

ጌትዬ በሶስት እና በአራት ወራት ልዩነት በሰዎች ትዕዛዝ አማካኝነት የፈለጉትን ስዕል እንደሚሰራና ዋጋቸዉም ከ 1 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ እንደሚሆን ሰምተናል። 

የስዕል ስራዎችን ማሳየት የሚቻልበት ኤግዚቢሽን (ጋለሪ) በከተማው እንደልብ አለመኖሩ ፣ የቀለሞች መወደድ እና በከተማው አቅርቦት አለመኖሩ ከዚያም ሲያልፍ የገንዘብ ጉዳይ ለወጣቱ ትልቅ ችግር እንደሆነበትም ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረዉ ቆይታ ተናግሯል።

አስተያየት