መስከረም 11 ፣ 2015

የሰርከስ አዳማ ቢሮ መታሸጉ ታወቀ

City: Adamaዜናኪነ-ጥበብ

በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርጉ ከነበሩት ሰርከስ ጅማ እና ሰርከስ ትግራይ ጋር ሰርከስ አዳማ ስሙ በጉልህ የሚነሳ የሰርከስ ቡድን ነው

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የሰርከስ አዳማ ቢሮ መታሸጉ ታወቀ

ከ29 ዓመታት በፊት በ1985ዓ.ም የተመሠረተው ሰርከስ አዳማ ጽ/ቤቱ እንዲሁም የልምምድ መስሪያ ቦታው መታሸጉን የሰርከስ አዳማ ዳይሬክተር አቶ ፋሲል ገዛኸኝ ለአዲስ ዘይቤ ገለጸ። 

በተጨማሪም ከሰርከስ ቡድኑ ጋር አንድ ግቢ የሚጋሩት ሰንኢኮ አርት ፎር ሶሻል ዴቭሎፕመንት እና የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር አዳማ ቅርንጫፍ የተባሉ ሁለት የበጎ-አድራጎት ድርጅቶች ቢሮዎችም በአንድ ላይ ሊታሸጉ ችለዋል።

የሰርከስ ትርዒት ቡድኑ ንቁ እንቅስቃሴ ያደርግባቸው በነበሩበት አመታት ከተማውን እንዲሁም ኢትዮጵያን በመወከል በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ማትረፍ ችሏል።

ትናንት ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ 5:00 ሰዓት ላይ  የመጡ አምስት ሰዎች  ወደ ጽ/ቤቱ ግቢ ገብተው ቁልፍ እንደጠየቁት የገለጸው ዳይሬክተሩ ሰዎቹ ምንም ዓይነት ደብዳቤ አለመያዛቸውን እና "ግቢውን ልቀቁ ህገ-ወጦች ናችሁ" መባላቸውን ይናገራል። በተፈጠረው አለመግባባት መጨረሻ ግቢው ሊታሸግ ችሏል።

በሰርከስ ቡድኑ ቢሮ መታሸግ ምክንያት ቢሮው የታሸገበት የሰንኢኮ አርት ፎር ሶሻል ዴቭሎፕመንት የአዳማ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ኃ/እየሱስ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጸው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ልቀቁ መባላቸውን ይናገራል። ማህበሩ በስሩ የተለያዩ ስራዎችን የሚያከናውኑ 30 ታዳጊዎች እና ወጣቶች እንዳሉ የሚናገረው አቶ ዳንኤል ሰንኢኮ በአሁን ወቅት በላንቃ እና ከንፈር መሠንጠቅ ላይ የሚሰራው የስማይል ትሬይን አጋር ሆኖ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ቅሬታውን ያቀረበው የሰርከስ አዳማ ዳይሬክተር አቶ ፋሲል ገዛኸኝ የሰርከስ ቡድኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የከተማዋን እና የሀገሪቱን ስም ያስጠራ ተቋም እንደሆነ በማስረዳት በአሁን ወቅት ቡድኑ 50 አባላት እንዳሉትም ገልጿል።

ፎቶ፡ ሰርከስ አዳማ (የሰርከስ አዳማ አባላት ትርዒት)

ለመታሸጉ ግልጽ ምክንያት እንዳልተሰጣቸው የገለጸው አቶ ፋሲል ዛሬ ጠዋት ጉዳዩን ለአዳማ ከተማ ስፖርት እና ወጣቶች ጽ/ቤት ማቅረቡን እና ለአርብ መቀጠራቸውን ተናግሯል።

ከ2003 ዓ.ም በፊት ቡድኑ ለቢሮው ኪራይ ይከፍል እንደነበር የሚገልፀው ዳይሬክተሩ አቶ ፋሲል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ግን ቀድሞ ይደረግ የነበረው የውጭ ፈንድ በመቋረጡ በአዳማ ስፖርት ጽ/ቤት ስር ሆነው ግቢውን በነጻ ያለምንም ክፍያ እየተጠቀሙ መቆየታቸውን ይናገራል።

የቢሮዎቹ ግቢ የታሸገበትን ማህተም ተመልክተን ወደ አዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ በማቅናት በጸሐፊያቸው በኩል ወደ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ የመሩን ሲሆን የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊው በበኩሉ ጉዳዩ የኮሚኒኬሽን እንደሆነ ገልጸውልናል።

የአዳማ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጣሒር ሐጂን ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ያደርግነው ሙከራ ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም። በጉዳዩ ላይ የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤትም ሆነ ከንቲባ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ምላሽ ለማካተት አዲስ ዘይቤ በማንኛውም ሰዓት ዝግጁ ናት።

አቶ አባ ዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ “ተስፋ የተጣለበት የወጣቶች ጅርጅት” ተብሎ የተሸለመው ሰርከስ አዳማ ከሁለት ዓመት በፊት በቱርክ አስር ከተሞች አባላቱን ይዞ በመዘዋወር ትርዒት ያቀረበ ሲሆን የቡድኑ አባል የሆነው ኪሮስ ሀድጉ ደግሞ በጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ ላይ በቴኒስ ራኬት ውስጥ ተጣጥፎ በማለፍ ራሱን እና ሀገሩን በሪከርድ መዝገቡ ማስፈር ችሏል።

በተጨማሪም ድምፃዊ ታደሰ መከተ ያፈራው የከተማው ኡርጂ አዳማ ባንድ ሲቋቋም የባህል ቡድኑ አባላትን ከሰርከስ አዳማ መውሰዱን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባለው ሰርከስ ኢትዮጵያ በመከተል ሰርከስ አዲስ አበባ በ1983 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በመቀጠልም በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርጉ ከነበሩት ሰርከስ ጅማ እና ሰርከስ ትግራይ ጋር ሰርከስ አዳማ ስሙ በጉልህ የሚነሳ የሰርከስ ቡድን ነው። እነዚህ የሰርከስ ቡድኖች ከመንግስትና ከአለም አቀፍ አጋሮች የሚደረግላቸው የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎች እየተቋረጡ በመሄዳቸው ቀስ በቀስ ሊከስሙ ችለዋል። 

አስተያየት