መስከረም 12 ፣ 2015

አስገራሚው የኮንዶም ዋጋ ጭማሪ

City: Adamaጤናወቅታዊ ጉዳዮች

በዲኬቲ ኢትዮጵያ አማካኝነት እ.ኤ.አ እስከ 2020 ድረስ ከ 2 ቢሊዮን በላይ ኮንዶሞች በሽያጭ እና ነጻ እደላ በመላ ኢትዮጵያ ተሰራጭቷል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አስገራሚው የኮንዶም ዋጋ ጭማሪ
Camera Icon

ፎቶ፡ ዲኬቲ ኢትዮጵያ (በዲኬቲ ኢትዮጵያ አማካኝነት በገበያ ላይ ያሉ የኮንዶም ዓይነቶች)

በኢትዮጵያ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣው የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሸቀጦች ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት በአስደንጋጭ ሁኔታ ሁለትና ሶስት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ ማሳየት የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል። ከመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አንስቶ እስከ ቅንጦት እቃዎች ድረስ የሚሰማው የዋጋ ተመን አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

“ምን ያልጨመረ ነገር አለ?!” በሚባልበት በዚህ ወቅት በአስገራሚ ሁኔታ ከፍተኛ የዋጋው ጭማሪ ካሳዩ ሸቀጦች መካከል ኮንዶም አንዱ ነው። ከወራት በፊት በፋርማሲዎች በከፍተኛ የችርቻሮ ዋጋ ከፍተኛ 10 ብር የነበረው የኮንዶም ዋጋ በአሁን ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ30 እስከ 50 ብር ድረስ በፋርማሲዎች ውስጥ እየተሸጠ ሲሆን እስከ 90 ብር ድርስ የሚሽጥባቸው አንዳንድ ቦታዎችም እንዳሉ ይነገራል።

ይህ የዋጋ ጭማሪ በኮንዶም ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የእርግዝና መከላከያ እና የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ላይ ይታያል። በአዳማ ከተማ አዲስ ዘይቤ ያነጋገርነው የፋርማሲ ባለቤት አቶ ብሩክ ግርማ ባለፋት 3 ወራት በኮንዶም ዋጋ ላይ ፈጣን ጭማሪ መታየቱን ይናገራል። 

"በውስጡ 48 የሚይዘውን የኮንዶም ፖኬት ከ3 ወራት በፊት ተወደደ ከተባለ 1 መቶ 80 ብር ነበር የምንረከበው" የሚለው አቶ ብሩክ አሁን ላይ ከ740 ብር እስከ 780 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ይናገራል። ይህ ማለት 10 ብር የሚሸጠው ኮንዶም ላይ ሶስት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ እየተሸጠ ይገኛል። 

ኮንዶም እና ሌሎች የወሊድ መከላከያ ምርቶችን አቅራቢ የሆነው 'ዲኬቲ ኢትዮጵያ' የሚባለው ድርጅት በሚያቀርባቸው የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎች እና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች ላይም የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ይገልጻል።

እ.ኤ.አ በ2022 ዓ.ም ይፋ በተደረገ ጥናት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ መጀመሪያዎች ወዲህ ዲኬቲ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለፉት 30 ዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ኮንደሞች መሸጡን ይገልጻል። በአጠቃላይ እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 2 ቢሊዮን በላይ ኮንደሞች በሽያጭ እና ነጻ መታደላቸውን ጥናቱ ያሳያል።

ፎቶ፡ ዲኬቲ ኢትዮጵያ (በዲኬቲ ኢትዮጵያ አማካኝነት በገበያ ላይ ያሉት የወሊድ መቆጣጠሪያ ምርቶች) 

ሌላው የመድሃኒት መደብር ባለቤት የሆነው አቶ ሔኖክ ይህ የዋጋ ጭማሪ ከጀመረ መሰነባበቱን ይገልጻል። ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያውቅ እንደሆነ የጠየቅነው ሔኖክ “ምክንያቱ ብዙም ግልጽ አይደለም። በፊት በበጎ-ፍቃድ ይደረግ የነበረው ድጋፍ በመቀነሱ እንደሆነ ሲወራ ሰምቻለሁ” በማለት ይናገራል።

ከኮንዶም ምርቶች በተጨማሪ የሌሎች የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ዋጋም አብሮ መጨመሩን የፋርማሲ ባለቤቶቹ ይስማማሉ። ለአብነት ያክል 20 ብር የነበረው ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) ከ20ብር ወደ 50 ብር ከፍ ብሎ በእጥፍ መጨመሩን ይገልጻል። በየቀኑ የሚዋጠው “ቾይዝ” የተባለ የቤተሰብ እቅድ እንክብል ከ5 ብር ወደ 20 ብር ከፍ ማለቱን ይገልጻል።

“የዋጋ ጭማሪው የኮንዶም ሽያጭ እንዲቀንስ አድርጓል” የሚለው የፋርማሲ ባለሞያው አቶ ብሩክ “በየግዜው የሚደረገውን ጭማሪ ለገዢዎች ስንነግራቸው ባለማመን ጥለው ይሄዳሉ” ሲል ይናገራል። “የምርቱ ብቸኛ አቅራቢያችን ዲኬቲ ኢትዮጵያ ነው” የሚለው አቶ ብሩክ “ለዋጋ ጭማሪው ግልጽ ምክንያቱን አናውቅም” ይላል። ከኮንዶም ሌላ በዲኬቲ የሚቀርቡ እንደፖስት ፒል፣ ቾይዝ፣ አይ ፕላን እና መሰል ምርቶች ላይ ባለተለመደ መልኩ ድንግተኛ ዋጋ ጭማሪ መታየቱን አቶ ብሩክ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል። 

ይህ በኮንዶም ዋጋና በቤተሰብ ምጣኔ እንክብሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ለተላላፊ በሽታ የሚያጋልጥ እንዲሁም ያልተፈለገ እርግዝና የመፈጠር እድልን ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ። የመድሃኒት ቤት ባለቤቱ አቶ ሔኖክ እንደሚለው ወትሮውንም ከቅድመ- መከላከል ይልቅ ወደ እርግዝና መከላከያ መንገዶች ያተኮረው የተጠቃሚዎች ምርጫ የዋጋ ውድነቱ ሲታከልበት የኮንዶም ሽያጭ እጅግ ማሽቆልቆሉን ተናግሯል።

ፎቶ፡ ዲኬቲ ኢትዮጵያ 

አዲስ ዘይቤ በተለያዩ ከተሞች ባደረገችው የዋጋ ቅኝት መሰረት የአዳማ ከተማን ጨምሮ በሐዋሳ፣ በደሴ እና በጎንደር ከተሞች ቀደም ሲል 10 ብር ይሸጥ የነበረው 1ፓኬት ኮንዶም 25 እና 30 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል። ከዋጋው መጨመር በተጨማሪ የአንዳንድ ቦታዎች የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም እንዳለ የፋርማሲ ሰራተኞች ገልጸዋል።

የተለያዩ አይነት ኮንዶሞች፣ የእርግዝና መከላከያ እና የወሊድ መቆጣጠሪያ ምርቶችን የአቅርቦትና የዋጋ ጭማሪው በተመለከተ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የዲኬቲ ኢትዮጵያን ኃሳብ ለማካተት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ባለፉት ወራት በሀገሪቱ ትልቁ የቤተሰብ እቅድ ምርቶች አቅራቢው አለማቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በሰራተኞቹ አለአግባብ ተቀነስን በሚል በሚዲያዎች ስሙ ሲነሳ መክረሙም ይታወሳል።

ከድርጅቱ የማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ በሰፈረው ሃሳብ መሰረት ዲኬቲ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1990 የተመሰረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ማህበራዊ ግብይትን በመከተል የቤተሰብ እቅድ አጠቃቀምን ለማስፋፋት፣ ኤችአይቪን ለመከላከል፣ እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምርቶችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል። ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በኮንዶም እና በሌሎቹ የወሊድ መቆጣጠሪያ ምርቶቹ አማካኝነት ከ16 ሚሊዮን በላይ ያልታቀዱ እርግዝናዎችን ማስቀረት መቻሉን ይገልጻል።

አስተያየት