መስከረም 13 ፣ 2015

የደሴው የዛፎች አባት አባ መፍቅሬ ሰብ

City: Dessieየአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

ልጅ ሆኜ የቆሎ ተማሪ እያለሁ እርሳቸው የሚተክሉትን ችግኝ ከወንዝ ውሃ እያመጣን በማጠጣት እናግዛቸው ነበር። ተግባሩን ልማድ አድርጌው አሁን ድረስ ችግኝ እተክላለሁ ~መሪጌታ እዝራ በአምላኩ

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የደሴው የዛፎች አባት አባ መፍቅሬ ሰብ
Camera Icon

ፎቶ፡ እድሪስ አብዱ እና ከማህበራዊ ሚድያ

“ደሴን በአራቱ ማዕዘን ስታዩአት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ የለፉበት ነው። ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው። አይከፈላቸውም፣ አልተመደቡም፣ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፣ እርሳቸው ግን 'የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው' ብለው ደን ሲተክሉና ሲንከባከቡ ይኖራሉ” በማለት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ፅሁፉ ስለ ጉምቱው የወሎ አባት ተምሳሌታዊ ስብዕና አድናቆቱን ሰንዝሯል።

የደሴ ከተማ በተለያየ ዘመን ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል ተፈጥሮን አብዝተው በመንከባከብ ችግኞችን በመትከል በርካታ ሰው ሰራሽ ደኖችን በመፍጠር የሚታወቁት ታላቁ አባት አባ መፍቅሬ ሰብ አንዱ ናቸው።

የስማቸው ትርጓሜ እንደሚያስረዳው “መፍቅሬ ሰብ” ማለት ሰውን የሚወድ በሰዎችም ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ማለት ሲሆን ስማቸውንም ከተግባራቸው ተነስቶ ህዝብ አወጣላቸው፣ እርሳቸውም ተቀበሉት። “መፍቅሬ ሰብ ማለት ሰው የሚወደው ማለት ሲሆን ዋናው ስምም የክርስቶስ ስም ሲሆን (ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር) የሚል ትርጓሜም ስላለው ስያሜውን ልቀበለው ችያለሁ” በማለት አባ መፍቅሬ ሰብ ይናገራሉ። 

አባ መፍቅሬ ሰብ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ በድፍን የደሴ ከተማ ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ካደረጓቸው ተግባራት አንዱ ነው። የታመመ በመጠየቅ፣ የሞተን በመቅበር፣ ሀዘን በመድረስ፣ በደስታ ጊዜ ሰርግ ላይ በመገኘት፣ በበዓላት “እንኳን አደረሳችሁ” ለማለት ሰዎች ቤት በመሄድ፣ በወሎና በአካባቢው በሚከበሩ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ህዝባዊ በዓላት ላይ በማስተባበርና በማስተማር የሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች ለሌሎች የኃይማኖት አባቶች እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። 

አባ መፍቅሬ ሰብ በአሁኑ ሰዓት እድሜያቸው 80ዎቹ አጋማሽ ላይ የደረሰ መሆኑን የሚገልፁት አባ፣ የእድሜያቸውን 60ውን አመታት ከኃይማኖት ትምህርት ጎን ለጎን ዛፍ በመትከልና ተፈጥሮን በመንከባከብ እንዳሳለፉ ይናገራሉ። “ዛፎችን መትከል የጀመርኩት በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሃይማኖታዊና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ህዝብ የሚሰባሰብበት ስፍራ በመሆኑ ማረፊያ ጥላ እንዲሆን በማሰብ ነው” ይላሉ።

አባ መፍቅሬ በጌምድር (ጎንደር) ክፍለሃገር ውስጥ በአገልግሎት በነበሩበት ጊዜ ደን ያለአግባብ ሲጨፈጨፍ በማየታቸው ከ 1943 ዓ.ም ጀምሮ 'ደን መጠበቅ አለበት' የሚል እሳቤ በመያዝ ዛፎችንም መትከል መጀመራቸውን ያስረዳሉ። “የደን መጨፍጨፍ ለተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች ይዳርጋል። ዝናብ ይጠፋል፣ ድርቅ ይከሰታል፣ ሙቀት ይጨምራል። በመሆኑም ያለአግባብ ዛፍ የሚቆርጡትንና ደን የሚጨፈጭፉትን ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ በተለያየ ጊዜ ትምህርት እሰጣለሁ። ከዚህ አልፈው በእኩይ ተግባራቸው የሚቀጥሉትንም የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ እገዝታቸዋለሁ” በማለት ለፈጥሮ ያላቸውን ስስት ይናገራሉ።

በደሴ ከተማ የሚገኙትን አብዛኞቹን አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፣ ቁስቋም፣ አማኑኤል እና ኪዳነ ምህረት አብያተ ክርስትያናትን ካሳነጹት አባቶች መካከል አንዱ አባ መፍቅሬ ሰብ በመሆናቸው ምዕመኑ ሁልጊዜም ያስታውሳቸዋል። በሌላም ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ የልማት ስራዎች ላይ ነዋሪውን በማሳተፍና በማስተባበር ብዙ በጎ ተግባራትን ማከናወን የቻሉ አባት ናቸው።

መሪጌታ እዝራ በአምላኩ በልጅነት እድሜያቸው የቤተክህነት ትምህርት ለመከታተል በ1979 ዓ.ም ከትውልድ ሃገራቸው መቄት ወረዳ ወደ ደሴ ከተማ ከመጡ ጀምሮ ከቆሎ ተማሪነት ጊዜያቸው አንስቶ አባ መፍቅሬን የሚያውቋቸው ሲሆን ከእርሳቸው መለኮታዊ እውቀትን ከመማራቸው በተጨማሪ ችግኝ መትከልና የመንከባከብ ልምድ መውረሳቸውን ይናገራሉ። 

“ልጅ ሆኜ የቆሎ ተማሪ እያለሁ እርሳቸው የሚተክሉትን ችግኝ ከወንዝ ውሃ እያመጣን በማጠጣት እናግዛቸው ነበር። ተግባሩን ልማድ አድርጌው አሁን ድረስ ችግኝ እተክላለሁ። አብዛኞቹን ደሴ ከተማ ውስጥ ያሉትን የቤተክርስቲያን አጸዶች ያሳመሩት እርሳቸው ሲሆኑ ለዚህም የቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አንዱ ማሳያ ነው” ይላሉ መሪጌታ እዝራ።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ስለአባ መፍቅሬ ሰብ “የተሸጡት አባት” በሚል ርዕስ በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ላይ ባሳተመው ጽሁፉ ስለ አባ መፍቅሬ ሰብ የስብዕና ከፍታ እና የህዝብ ፍቅር እንዲህ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፤

“ለእርሳቸው ዘርና ሃይማኖት ሰውን ለመርዳት መመዘኛዎች አይደሉም። ሰውነት ብቻ ይበቃቸዋል። ይህ ርዳታቸው ከመከራ ያወጣቸው፣ ከችግር የታደጋቸውና ሕይወታቸውን ያቀናላቸው ሰዎች ስለ እኒህ አባት ሲያወሩ ከማያቋርጥ ዕንባ ጋር ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ከንግግር ይልቅ እርሳቸውን እያሰቡ ዝም ብለው በማልቀስ ይገልጧቸዋል። መቼም ለአንዳንዱ አብዝቶ አይደል የሚሰጠው። እርሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አርበኛም ናቸው።

ዳንኤል በፅሁፉ ስለ አባ መፍቅሬ ሰብ የረዥም ዓመታት የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ውጤታማነትን ከመግለፁ ባሻገር የአባ መፍቅሬ ሰብን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ በማድነቅ፤ በራስ ተነሳሽነት ለሀገር ስላደረጉት ትልቅ ተግባር እንዲህ ይላል፦  

“በዚህ የእርጅና እድሜያቸው እንኳን መኮትኮቻና መቆፈሪያ፣ አካፋና ባሬላ ይዘው በደሴ ተራሮች ላይ ዛፍ ሲተክሉ ይውላሉ። ደሴን በአራቱ  ማዕዘን ስታዩዋት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ የለፉበት ነው። ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው። አይከፈላቸውም፣ አልተመደቡም፣ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፣ እርሳቸው ግን 'የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው' ብለው ደን ሲተክሉና ሲንከባከቡ ይኖራሉ።”

አባ መፍቅሬ ሰብ ከተከሏቸው ደኖች መካከል ከደሴ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተ የሚነገርለት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቅጥር ግቢ አይነተኛ ማሳያ ነው። ገዳሙ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚመጡ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ትምህርት ይሰጥበት የነበረ ሲሆን አንዳንድ ምሁራንና አበው “የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ስነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ” በማለት ይገልፁታል። 

አባ መፍቅሬ ሰብ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቅጥር ግቢን የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል አካባቢውን ባላበሱት ግርማ ሞገስ፣ በጣም ማራኪ፣ የአይን ማረፊያና የመንፈስ ምግብ ብሎም የቱሪስት መስህብ መሆኑ ለታላቅ ተግባራቸው ቋሚ ምስክር ሆኗል።

ውልደታቸው ሰሜን ሸዋ ልዩ ስሙ ተጉለት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሆነው አባ መፍቅሬ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ ደሴ ከተማ ላይ መኖር የጀመሩ ሲሆን ረዥሙን የእድሜያቸውን ጊዜ ደሴ ላይ አሳልፈዋል፣ አሁንም ደሴ ከተማ ውስጥ ይኖራሉ። 

“የደሴ ከተማ ህዝብ ከህዝበ ክርስቲያኑ ባልተናነሰ ሙስሊሙ ማህበረሰብም ለኔ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ይገልጽልኛል። ያገኙኝ ሁሉ 'አላህ ረዥም እድሜ ያኑርህ' እያሉ ይመርቁኛል” በማለት የከተማውን ነዋሪ ስለሚለግሳቸው ፍቅር እና አክብሮት ይናገራሉ።

አቶ ሰኢድ ሀሰን የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አባ መፍቅሬ ሰብን ከ30 ዓመት በላይ እንደሚያውቋቸው ገልጸው ሰለ ማህበራዊ ተሳትፏቸው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ “የአባ መፍቅሬ መገለጫ የሆነው ዋናው ባህሪያቸው ሰውን በሃይማኖቱና በማንነቱ ሳይመዝኑ በደስታውም ይሁን በሃዘኑ ጊዜ ፈጥነው ከጎኑ በመገኘት 'አይዞህ' የሚሉ አባት ናቸው። በሃይማኖቶችና በአማኙ መካከልም መተባበርና መከባበር እንዲኖር የሰሩት ተግባር ሁልጊዜም ከሰዎች ልብ ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል” ይላሉ።

ግሸን ደብረ ከርቤ እንደ ዛሬው መንገዱ ሳይሰራና ለተጓዦች ምቹ ሳይሆን ብዙዎች ቦታው ላይ ተገኝተው የነፍስ ርሃባቸውን ለማስታገስ በምኞት ብቻ በሚኖሩበት ጊዜ የህዝብን ስሜት ተረድተውና የቦታውን ታላቅነትና አለም እንዲመሰክር፣ የተራቡትም ርሃባቸውን ያስታግሱ ዘንድ በወቅቱ ለነበሩ ባለስልጣናት አባ መፍቅሬ ሰብ ያቀረቡት ምክረ ኃሳብ አመኔታ አገኘ። በዚህም እንኳን ለሰው ለዝንጀሮም ያሰቸግራል የሚባለውን 17 ኪሎ ሜትር ተራራ በ1973 ዓ.ም መንገድ እንዲሰራበት በማድረግ እልፎችን ከምኞታቸው ጋር ያገናኙ፣ ታሪክ በደማቁ ከወርቅ መዝገብ ላይ ያሰፈራቸው፣ የግማደ መስቀሉ ማረፊያ ግሸን ደብረ ከርቤ በነገሰች ቁጥር ስማቸው አብሮ የሚነሳ ውዱ የኢትዮጵያ ልጅ አባ ፍቅሬ ሰብ ናቸው። 

ዛሬ ላይ ግሸን ደብረ ከርቤ በአመታዊ የንግስ በዓሉ ላይ ሚሊዮኖች የሚገኙበት ስፍራ በመሆኑ ከሃይማኖታዊ ስፍራነቱ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለዞኑ የገቢ ምንጭ ሆኖም እያገለገለም ይገኛል። ዲያቆን ናሁሰናይ ወልደሚካኤል ስለ አባ መፍቅሬ ሰብ ተፈጥሮንና ልማት ወዳድነታቸውን ሲገልጽ “ማንኛውም ሰው አካባቢውን እንዲያለማ፣ ዛፎችን በመትከል ተፈጥሮን መንከባከብ እንዳለበትና የሃገር ቅርሶችን መጠበቅ እንደሚገባው በአውደምህረት ላይ ሳይቀር ትምህርት የሚሰጡ ድንቅ አባት ናቸው” ይላል።

“ዛፎቼ እንደሰው የማወራቸው ልጆቼም ጭምር ናቸው። ከእነርሱ ጋር በምሆን ሰዓት ሳልበላ ሁሉ እጠግባለሁ” የሚለው ንግግራቸው አባ መፍቅሬ ሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ጥልቅ ቁርኝት ማሳያ ነው።  

አባ መፍቅሬ የእድሜ ዘመናቸው ሙሉ ዛፍ በመትከል ተፈጥሮን መንከባከባቸውን፣ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ የልማት ስራዎችን መስራታቸውንም ለመዘከር “አባ መፍቀሬ፣ የደን ገበሬ/ አባ መፍቅሬ ሰብ፣ የዛፎች ቤተሰብ” የሚል የአድናቆት መጠሪያ ስንኝ ማህበረሰቡ እስከማውጣት የደሠሰ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም በዞንና በክልል ደረጃ በርካታ የእውቅና ሽልማቶችን አግኝተዋል። 

የደሴ ከተማ ማህበረሰብም ለአባ መፍቅሬ ሰብ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ ባዋጣው ገንዘብ ወጭያቸውን ችሎ ሃይማኖታዊ ፀሎትና እንዲያደርሱና ጉብኝት እንዲያደርጉ ወደ እየሩሳሌምና ግብጽ ደርሰው እንዲመጡ አድርጓቸዋል።

አስተያየት