ኅዳር 4 ፣ 2014

የገበሬን ኑሮ የማቅለል ዓላማ ያነገበው “የዛሬ” መተግበሪያ

City: Hawassaቴክ

ገበሬዎች የእለቱን የገበያ ዋጋና የተረጋገጠ የአየር ሁኔታ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችለው ወደሥራ ሲገባ ግን በታሰበው ልክ ለገበሬዎች ተደራሽ ያልሆነው “የዛሬ” የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ከተዋወቀ ከዓመታት በላይ አስቆጥሯል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የገበሬን ኑሮ የማቅለል ዓላማ ያነገበው “የዛሬ” መተግበሪያ

“የዛሬ” የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ከተዋወቀ ከሦስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። የሐሳቡ ዓላማ ገበሬዎች የየእለቱን የገበያ ዋጋ እና የተረጋገጠ የአየር ሁኔታ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። ትኩረቱ ሙሉ ለሙሉ የገጠራማውን አካባቢ ላይ አድርጎ የገበሬዎችን ሕይወት ማቅለል እና የልፋታቸውን ተገቢ ዋጋ እንዲያገኙ ማገዝ ዋነኛ ዓላማው ነው።

“የዛሬ” የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የለማው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ፋርም አፍሪካ ትብብር ሲሆን  አገልግሎቱም በተመረጡ አራት ዞን፤ አምስት ወረዳ ስድስት የገበያ ቀን ለሙከራ ሲተገበር ቆይቷል። “የዛሬ” የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም ለአርሶ አደር መገልገያ የሚውል ሞባይል መተገበሪያ፤ ለገበያ መረጃ መሰብሰቢያ የሚውል ሞባይል መተግበሪያ እና  የበይነመረብ (Website) መቆጣጠሪያ ለመረጃ አስተዳዳሪው ናቸው። ባጠቃላይ ሁለት ሞባይል መተግበሪያ እና አንድ የበይነመረብ ስርዓት አልምቷል።

የገበያው መረጃ መሰብሰቢያ የሞባይል መተግበሪያ ለገበያ መረጃ ሰብሳቢ ባለሞያ የተዘጋጀ ነው። መረጃ ሰብሳቢው የሞባይል መተግበሪያውን በመጠቀም የተለያዩ ሰብሎችን ዋጋ እገበያው ላይ ሆኖ በገበያው ቀን ሰበሰቦ ወደ ሲስተሙ ቋት ያስገባል።

የበይነመረብ (Website) መቆጣጠሪያው ሲስተሙን ለማስተዳደር ይጠቅማል። ይህም ማለት አርሶ አደሮችን እና የገበያ መረጃ ሰብሳቢዎችን ይመዘግባል፤ በገበያ መረጃ ሰብሳቢዎች የሚገቡትን የገበያ ዋጋዎች በተቀመጠው ሕግ መሰረት መግባቱን ይቆጣጠራል፣ ከአርሶ አደሩ የሚላክለተን የአስተያየት መላዕክት ይመለከታል...ወዘተ።

የአርሶ አደሩ የሞባይል መተግበሪያ ለአጠቃቀም ቀላል ሆኖ የተዘጋጀ አንድሮይድ የሞባይል መተግበሪያ ነው። መተግበሪያው ለአርሶ አደሩ አቅራቢያው ያለውን የገበያ ዋጋ መርጦ ለተመዘገበባቸው ሦስት ሰብሎች መነሻ ገፅ ላይ መመልከት ይችላል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ የሌላ አካባቢን የገበያ ዋጋ መርጦ እንዲመላከት እና የሱን አካባቢ የገበያ ዋጋ ከሌላው አካባቢ የገበያ ዋጋ ጋር ማነፃፀር እንዲችል ይረዳል።

ሐሳቡ ዳብሮ፣ የአንድሮይድ ሞባይል ስልክ መተግበሪያው ተሰናድቶ፣… ወደ ሥራ ሲገባ ግን በታሰበው ልክ ለገበሬዎች ተደራሽ ሳይሆን ቀረ። የስማርት ስልክ አተቃቀም እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ማነስ በተፈላጊው መጠን አግልገሎቱ እንዳይዳረስ ምክንያት ሆኗል።

በተግዳሮቱ ተስፋ ያልቆረጡት የፕሮጀክቱ መሪዎች ከስማርት ስልክ መተግበሪያው በተጨማሪ አዲስ መላ ዘየዱ። አገልግሎቱን በጽሑፍ መልዕክት ማድረስ። ለመፍትሔውም አጭር የጽሑፍ መልእክት መላኪያ GSM/GPRS Module የታገዘ ሶፍትዌር አዘጋጅተው ለአርሶ አደሩ በማንኛውም ዓይነት የሞባይል ስልክ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን አድርገዋል። ሶፍትዌሩን ተከትሎ የተዘጋጀው መገልገያ (Device) ጠንሳሾቹ በተለሙት ልክ አገልግሎታቸውን ለገበሬው ለማድረስ አግዟቸዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎቹን ወደ አምስት ሺህ ማሳደግ የቻለው “የዛሬ” መተግበሪያ መቀመጫውን ብሪታንያ ባደረገው ፋርም አፍሪካ እና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቅንጅት ይመራል።  

አቶ ነስረዲን አወል የሀላባ ዞን ነዋሪ ናቸው። የሚተዳደሩት በግብርና ነው። “የዛሬ” እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። “የሀላባ ዞን ወይራ ወረዳ ገበያ የሚለውለው ማክሰኞ ነው። ከዚህ በፊት በላቤ ያመረትኩትን፣ የለፋሁበትን እህል ዋጋውን የሚወስንልኝ ደላላ ነበር። ቢመቸኝም ባይመቸኝም በጠሩልኝ ዋጋ እሸጣለሁ። በእኔ ላብ ተጠቃሚዎቹ እነርሱ ናቸው። ‘የዛሬ’ ከመጣ በኋላ ግን የእለቱ ዋጋ በአጭር የጽሑፍ መልእክት ስለሚደርሰኝ ዋጋውን አውቀዋለሁ። ደላላ ሳይገባበት ግብይታችንን የምንፈጽመው” ብሎናል።

ሌሎችም የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች የአየር ሁኔታ ትምበያን መጠቀማቸው የእለቱን ሥራቸውን እንዲያቀላጥፉ እድል ሰጥቷል።

ወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ የአይዳ ኮይሻ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዳነ ገበሬ ናቸው። የዛሬ ሶፍትዌር ከገበያ ጥናት በተጨማሪ የአየር ሁኔታ ትንበያው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። “ወደ እርሻዬ ከማምራቴ በፊት የአየር ሁኔታውን ተመልክቼ ነው። ይህም በጣም ብዙ ጠቅሞኛል” ብለዋል።

የዛሬ ሶፍትዌር አነሳሽ የሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ረዳት መምህር መቲ ተስፋዬ ይባላሉ። በይዘቱ የመጀመርያ የሆነውን ሶፍትዌር እና አጭር የጽሑፍ መልእክት መላኪያ እና መገልገያ (devise) “ሥራው የተጀመረው በ‘ኢንተርን ሺፕ’ ነው” ብለውናል። በጥቂቱ የተጀመረው በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ሲረዳ በመመልከታቸው ደስተኛ ስለመሆናቸውም ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

እለታዊው የገበያ መረጃ በሶፍት ዌር አማካኝነት ለገበሬዎች ከመላኩ በፊት ዳታዎች ይሰበሰባሉ። በየስፍራው ካሉ ገበያዎች የሰብል እህሎችን ዋጋ የሚያጣሩ ዳታ ሰብሳቢዎች አማካኝነት ከተሰበሰበ በኋላ ለገበሬዎች በስልካቸው ይላካል። በማንኛውም ዓይነት የስልክ ቀፎ መስራቱ ልዩ ያደርገዋል ተብሎለታል። ገበሬው ምርቱን ወደ ገበያ ይዞ ከመውጣቱ በፊት መረጃዎችን ተመልክቶ እንዲወስን ይረዳዋል።

መቀመጫውን ሐዋሳ አድርጎ በደቡብ ክልል ሰባት ወረዳዎች ተደራሽ መሆን የቻለው “የዛሬ” በወረዳዎቹ ውስጥ ከሚገኙ ገበሬዎች መካከል 90 በመቶ ያህሉን መድረስ ስለመቻሉ ተዘግቧል።

ወይራ ዙርያ የሚገኘው ቁሊቶ ገበያ፣ አቶቲ ኡሎ ወረዳ የሚገኘው ጉባ ገበያ፣ ዳሞት ጋሌ ወረዳ የሚገኙት ቦዲቲ እና ሾኔ ገበያዎች፣ ሃደሮ ጡንጦ ወረዳ የሚገኙት ሃደሮ ቅዳሜ ገበያ እና ሌሾ ማዞርያ ገበያ ተጠቃሽ ናቸው። 

አቶ በቀለ በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የአይዳ ኮይሻ ቀበሌ ሊቀመንበር እና የገበያ ጥናት ባለሞያ (Data Collector) ናቸው። መረጃው ስለሚሰበሰብበት መንገድ ነግረውናል።

“የቦዲቲ ገበያ ማክሰኞ ነው የሚውለው እኔም ወደ ስፍራው በማቅናት እያንዳንዱን ምርት በስንት እንደዋሉ በማጥናት ለኃላፊዎቹ ሪፖርት አደርሳለው”

በሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ተስፋዬ ባዩ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን በበላይነት ይመሩታል” የዛሬዋ ሶፍትዌር በፋርም አፍሪካ እና በሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ ፈንድ የተሰራ ፕሮጀክት ነው፤ ለገበሬው ኑሮውን ከማቅለሉ ባሻገር ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ጋር በመቀናጀት የአየር ትንበያን በየዕለቱ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ተደረሽ ይደረጋል” ብለዋል።

በፋርም አፍሪካ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ጥበበ ኒጋኒ “ፋርም አፍሪካ የዛሬን ሶፍትዌር በመጠቀም ከዚህ ቀደም በሰባት ወረዳዎች ተደራሽ የነበረ ሲሆን በቀጣይ ወደ አስራ አምስት የሀገራችን ገጠራማ ስፍራዎች ለመድረስ አቅደናል” ብለዋል።

አስተያየት