ነሐሴ 22 ፣ 2012

“ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም”

ፊቸር

ህግጋት በእለት ተእለት ኑሯችን ላይ በምንከውናቸው ተግባራት ዙርያ ትልቅ ስርአትን የመፍጠርን ሚና ይጫወታሉ። ይህም ተገነዘብነውም አልተገነዘብነውም…

“ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም”
ህግጋት በእለት ተእለት ኑሯችን ላይ በምንከውናቸው ተግባራት ዙርያ ትልቅ ስርአትን የመፍጠርን ሚና ይጫወታሉ። ይህም ተገነዘብነውም አልተገነዘብነውም በማህበራዊ ህይወታችን ላይ ህግጋት ትልቅ ስፍራን እንዲይዙ አስችሏቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በቀን ተቀን ተግባሩ ላይ የሚተገብራቸው ድርጊቶች ህጋዊ ሆነው ከተጠያቂነት ቡድን እንደሚመረጥ ማሰብ ያስፈልጋል። የሰዎችን የአስተሳሰብ ማህደር ለማስፋትና ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በስፍራ መታገት  በቀረበት ዘመን ላይ ደግሞ ህግጋትን የመረዳት ዋጋ ከፍ ያለ ነው። ማንኛውም ግለሰብ ያልተገባውን ከማድረግ ለመጠበቅም ሆነ የተገባውን ባለማወቅ መጠቀሙ እንዳይቀር ከህግጋት ጋር መተዋወቅ ግድ ይላል። ስለዚህም ህግን “ሀ” ብሎ ማውጋት መጀመሩ ለመንግስትም ስራን ማቅለል፣ ለህዝቡም ባለማወቅ ግዴታን ከመዘንጋትም ሆነ መብትን ካለመጠቀም ለመታደግ ወሳኝ እርምጃ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።በምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ኢትዮጵያ በወቅቱ የምትተዳደረው በፌደራላዊ የአመራር ስርአት ሲሆን በውስጧ አስር ክልላዊ መንግስታትንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን አዋቅራ ይዛለች። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ከታወጀበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ህግ እንደሆነ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ንኡስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ ተቀምጧል። ይህም ማናቸውም የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ህግጋት፣ ልማዳዊ አሰራሮች እንዲሁም የመንግስት ባለስጣናት ውሳኔዎች ከህገ መንግስቱ ጋር የሚፃረሩ ሆነው ከታዩ ተፈፃሚነት አይኖራቸውም ወይም ህጋዊ ህግጋት አይደሉም እንደማለት ነው። ከህገ መንግስቱ በተጓዳኝነት በቅርቡ ክልልነቱን ካወጀው የሲዳማ ክልል በስተቀር ዘጠኙም የክልል መንግስታት የራሳቸው የሆነ ህገ መንግስት አውጥተው ህዝብን በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ። ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የህግ መዋቅር ስር ስድስት የተለያዩ ዋና ዋና የህግ አይነቶች አሉ። በእነዚህ የህግ አይነቶች ላይ የሰፈሩት አንቀፆችም በነጋሪት ጋዜጣ አማካኝነት ለህዝብ ይፋ ይደረጋሉ። ክልሎችም ከፌደራል መንግስት ትይዩ ከህገ መንግስቱ ጋር ባልተፃረረ መልኩ በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ህግጋትን ይደነግጋሉ። የኢትዮጵያ ህግጋት በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡ በኋላ ታድያ ሁሉም ህዝብ እንደሚያውቃቸው ይታሰባል። በዚህም የህግ መርህ መነሻነት በወንጀልም ሆነ በፍትሀ ብሔር መዝገቦች ላይ ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም። የህግ ባለሙያው አቶ ሰመረ ጥሩነህ እንዳሉት ከሆነ “ይህ መርህ ያስፈለገበት ምክንያት ግልፅ ነው። ይህም ሰዎች በወንጀልም ሆነ ፍትሀ ብሔር መዝገቦች ላይ “ህጉን አላውቅም” በማለት ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ከማስቻሉ አንፃር ነው። መርሁ ባይኖር ህግን ማስፈፀም ይከብዳል። ከዚህም በተጨማሪ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ መጠን የትምህርት አድማስ ውስጥ ከገቡ ጥቂት የማህበረሰቡ ክፍሎች በስተቀር ብዙሃኑ ህዝብ ከተጠያቂነት ለመዳን ሲል ህግን እንዲያውቅ ይህ መርህ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።”ይህ እንዳለ ሆኖ ግን እንደ አቶ ሰመረ አገላለፅ ከሆነ ቅጣት በሚሰጥበት ወቅት ግን ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ማጣርያ በማድረግ እውነትም ህጉን ባለማወቅ የተፈፀመ ድርጊት ከሆነ ቅጣቱን በህጉ መሰረት የማቅለል ስራ ሊሰራ እንደሚችል አክለው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።በአገራችን በርካታ ሰዎች ክስ በሚያቀርቡበትም ሆነ በሚቀርብባቸው ወቅት የት መሄድ እንደሚጠበቅባቸው ካለማወቅ አንስቶ የተለያዩ የፍትህ ምህዳሩን ያለመረዳት ችግሮች ይታዩባቸውል። ህግን አውጥቶ ከማንበብ ይልቅ በሙያው የተሰማራን ወዳጅ በጉዳዩ ላይ የተወሰነ ምክርን መጠየቅ የብዙ ኢትዮጵያውያን ምርጫ ሲሆን ይስተዋላል። ምንም እንኳን በፍርድ ቤት ተገኝቶ በአንድ ጉዳይ ላይ ከተቀናቃኝ ጋር ተከራክሮ መርታት የጠለቀ የህግ እውቀትና የሙያው ልምድ ያለው ጠበቃ ቢያስፈልግም ፣ መብትን ለማስከበርና በቀን ተቀን ኩናቴ ላይ ህግን አክብሮ ለመንቀሳቀስ ግን ይህ ጥልቅ እውቀት አስፈላጊ እንዳልሆነ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው በህግ ሙያ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ ባለሙያዎች ተናግረዋል። በህግ ሙያ ላይ የተሰማራችው ሄርሜላ ታዬ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀችው ከሆነ ህግጋት የሚደነገጉት ሰፊውን ማህበረሰብ ለማስተዳደር እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ሰው መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል። “ሰዎች ህግን ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም ህግ የሚወጣው ሰዎችን ለማስተዳደር ስለሆነ። በተቀመጠለት የህግ ማእቀፍ የማይተዳደር ሰው ህጉ በሚያስቀምጠው መልኩ ተገቢውን ቅጣት ማግኘትም አለበት።” በማለት ለአዲስ ዘይቤ የተናገረችው ሄርሜላ አክላም በህግ አውጪው በኩል ስላለው ግዴታ “ህግጋት በሚወጡበት ወቅትም ሆነ ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም በምንልበት ወቅት፣ ማህበረሰቡ ለህግጋት ካለው አናሳ ተጋላጭነት አንፃር የተደራሽነት ስራን መስራት ግድ ይላል።” በማለት ሀሳቧን አስቀምጣለች። በህግና በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰራው ብሩክ ነጋሽ ከሄርሜላ ሀሳብ ጋር ይስማማል። “መንግስት ህግጋትን ካወጣ በኋላ የተጠቀሱትን ህግጋት ለህዝቡ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህ አገሪቱ በፈረመቻቸው የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ላይ በግልፅ የሰፈረ መርህ ነው። ለምሳሌ በነጋሪት ጋዜጣ አንድን ህግ ማሳተም በራሱ በቂ ላይሆን ይችላል። በተጨማሪም ቀበሌና ወረዳን የመሳሰሉ የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮችን በመጠቀም ህግጋትን ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።” በማለት ለአገሪቱ ህዝቦች በተለይም በገጠራማው አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህግጋትን ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ብሩክ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

አስተያየት