ጥቅምት 30 ፣ 2011

“ለምን አይደውልም?”

ወቅታዊ ጉዳዮችአዝናኝ መጣጥፎች

(የዶርቲ ፓርከር ዘ ቴሌፎን ኮል የተሰኘ ዝነኛ አጭር ታሪክ የታተመው ከ88 አመታት በፊት፣ እንደ እነሱ አቆጣጠር (እእአ) በ1930 ዓ.ም ነው፡፡ ግን…

“ለምን አይደውልም?”
(የዶርቲ ፓርከር ዘ ቴሌፎን ኮል የተሰኘ ዝነኛ አጭር ታሪክ የታተመው ከ88 አመታት በፊት፣ እንደ እነሱ አቆጣጠር (እእአ) በ1930 ዓ.ም ነው፡፡ ግን ዛሬም ድረስ በአፃፃፍ ስልቱ ለብዙዎች ስሜት ቅርብ በመሆኑ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ አጫጭር ታሪኮች  መሃከል በግንባር ቀደምነት ይቀመጣል)…አምላኬ ሆይ፣ እባክህ አሁን እንዲደውልልኝ አድርግ፡፡ አምላኬ፣ አሁን እንዲደውል አድርግ፡፡ ሌላ ነገር አልጠይቅህም፡፡ እውነት እልሃለሁ ከዚህ ወዲህ አንድም ሌላ ነገር አላስቸግርህም፡፡ …ደግሞ እኮ ይሄ ላንተ ትልቅ ልመናም አይደለም፡፡ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አድራጊ እና ፈጣሪ ለሆንከው ላንተ ይህቺ ሚጢጢ ነገር ናት….ኢምንት…፡፡ …እና እስቲ አሁኑኑ እንዲደውልልኝ አድርግ፡፡ እባክህ አምላኬ፣ እባክህ…እባክህ…..….ለነገሩ እንዲህ መሆኔን ትቼ….ዝም ብዬ ‹‹ደወለ አልደወለ›› እያልኩ መብሰልሰሌን ባቆም እኮ ስልኬ በራሱ ጊዜ ይጮህ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ እንደዛ ነው የሚሆነው፡፡ ዝም ብዬ ስለሌላ ነገር ባስብ…ስለምንም ሌላ ነገር ባስብ….ወይ ደግሞ አምስት…አስር…አስራ አምስት እያልኩ…አምስት አምስት እየዘለልኩ እስከ አምሰት መቶ ብቆጥር ስልኬ ሊጮህ ይችላል፡፡ ቀ…ስ ብዬ እቆጥራለሁ….ቁጥር ሳላጭበረብር …ሳልዘል…ቀስ ብዬ እቆጥራለሁ….ቆጥሬ ቆጥሬ ሶስት መቶ ላይ ስደርስ ስልኬ ቢጮህ እንኳን መቁጠሬን አላቋርጥም…አምስት መቶ እስክደርስ ድረስ ስልኬን አላነሳም….አምስት..አስር…አስራ አምስት…ሃያ…ሃያ አምሰት…ሰላሳ…ሰላሳ አምሰት…አርባ…አርባ አምሰት…ሃምሳ…..ውይ! ስልኬ በናትህ ጩህ! በናትህ!…ከዚህ ወዲህ ሰአቴን አላይም፡፡ ደግሜ አላየውም፡፡ አንድ ሰአት ከአስር ሆኗል፡፡ አስራ አንድ ሰአት ላይ እደውላለሁ ነበር ያለኝ፡፡ ‹‹አስራ አንድ ሰአት ላይ እደውላለሁ፣ የኔ ማር›› ነበር ያለኝ፡፡ ያኔ መሰለኝ የኔ ማር ያለኝ…እርግጠኛ ነኝ ያኔ ነበር ያለኝ…ከተገናኘን ወዲህ የኔ ማር ያለኝ ሁለቴ እንደሆነ አውቃለሁ…ከዚህ ሌላ የኔ ማር ያለኝ አንድ ቀን ቻው ሲለኝ ነበር. …‹‹ቻው የኔ ማር››….ለነገሩ እኮ ስራ ይበዛበታል….ቢሮ ሆኖ እንደፈለገ ማውራትም አይችልም…ያም ሆኖ ግን ሁለት ጊዜ የኔ ማር ብሎኛል…ሁለት ጊዜ!….ብደውልለት ቅር የሚለው አይመስለኝም…አውቃለሁ ወንዶች ስልክ እየተደወለ ሲጨቀጨቁ አይወዱም…ሴት ልጅ አስሬ እየደወለች ስታስቸግራቸው ቀኑን ሙሉ ስለእነሱ እንደምታስብ ያውቁና ይጠሏታል፡፡ ግን እኮ እኔ ካወራሁት ሶስት ቀን ሆኖኛል..ድፍን ሶስት ቀናት! ስደውልለትም የምጠይቀው ስለደህንነቱ ነው….ማንም ቢደውልለት እንደሚጠይቀው…መቼም በዚያ ቅር ሊሰኝ አይችልም…ቆይ…ራሱ አይደል ‹‹አረ አልረበሽኝም›› ያለኝ? ራሱ አይደል ‹‹እደውልልሻለሁ›› ያለኝ? እንደዚያ እንዲል ያስገደደው የለም…እኔም በጭራሽ እንደዚያ እንዲል አላስገደድኩትም…መቼም እደውላለሁ ብሎ ሳይደውል ይቀራል ብዬም አላሰብም…እንደሱ የሚያደርግ አይመስለኝም….አምላኬ ሆይ፣ እባክህ እንደዚያ እንዳያደርግ አድርግልኝ…. እባክህ፡፡ሁለት ጊዜ የኔ ማር ብሎኛል….‹‹አስራ አንድ ሰአት ላይ እደውልልሻለሁ፣ የኔ ማር›› ‹‹ቻው ..የኔ ማር››…..እርግጥ ነው ስራ ይበዛበታል….ብዙ ጊዜ እንደተቻኮለ ነው…በዛ ላይ ሁሌም ቢሮ ውስጥ ከሰዎች ጋር ነው….ያም ሆኖ ግን ሁለት ጊዜ የኔ ማር ብሎኛል….ያ ማንም የማይወስድብኝ ሃቄ ነው….ከዚህ ወዲህ አይኑን ባላየው እንኳን እነዚያን ሁለት የኔ ማሮች የሚነጥቀኝ የለም፡፡… ግን እኮ…ግን እኮ ይሄን ሁሉ ጊዜ ቆይተን ሁለት ጊዜ  የኔ ማር መባል  በጣም ትንሽ ነው….ሁለት የኔ ማር በጣም ትንሽ ነው….አይበቃም…አይበቃኝም….በተለይ ከዚህ ወዲህ ካላየሁት…አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ደግሜ እንዳየው አድርግ፡፡ እባክህ…በጣም እፈልገዋለሁ…በጣም ያስፈልገኛል….መልካም ሰው እሆናለሁ አምላኬ….የተሻለች ሴት ለመሆን እጥራለሁ…ደግሜ እንዳየው ከፈቀድክልኝ….እንዲደውልልኝ ካደረግክልኝ…..እና እባክህ…ስማኝና አሁን እንዲደውልልኝ አድርግ……አምላኬ ሆይ፣ ፀሎቴን አሳንሰህ አትየው…አንተ በብርሃን እና በመላእክት ተከበህ…በቀኝ እና በግራህ በከዋክበት ታጅበህ፣ አንፀባራቂ ዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ..እኔ ደግሞ ይህችን ሚጢጢ የምወደው ሰው እንዲደውልልኝ አድርግልኝ ልመናዬን ይዤ እግርህ ስር ስወድቅ…አምላኬ ሆይ አትሳቅብኝ፡፡…አየህ…ስሜቴን አታውቀውም….ወትሮስ አንተ ምን አለብህ…?በዙፋንህ ላይ በምቾት ተቀምጠህ…ማን ይነካሃል…? እንደ ሚስኪኒቷ ፍጡርህ …እንደኔ ማንስ ልብህን ጢባጢቢ ይጫወትበታል…? ይሄ ስቃይ ነው…ታላቅ ስቃይ…አምላኬ፣ በጣም የከፋ ስቃይ ውስጥ ነኝ፡፡ አትለመነኝም? በልጅህ ስም አትለመነኝም?  እባክህ ለልጅህ ስትል እርዳኝ፡፡ በልጄ ስም የለመኑኝን አላሳፍርም አላልክም? አምላኬ ሆይ፣ በአንዱና በተወደደው ልጅህ.. በጌታችን፣ በመድሃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተለመነኝ፡፡ አሁኑኑ እንዲደውልልኝ አድርግልኝ፡፡…ይሄን እብደት አሁኑኑ ማቆም አለብኝ…እንዲህ መሆን አይገባኝም….አንድ ወንድ አንዲትን ሴት እወድልልሻለሁ ብሏት የሆነ ነገር ተፈጥሮ ባይደውልላት ይሄን ያህል ትልቅ ነገር ነው እንዴ? አይደለም፡፡ በዚህች ደቂቃ  እንኳን በአለም ላይ ስንት እንዲህ ያለ ነገር እየተካሄደ ነው….ብቻ… ብቻ… እኔ በአለም ስለሚከናወነው ነገር ምን አገባኝ?ቆይ ስልኬ ግን ለምንድነው ማይጮኸው? አንተ ስልክ….…ምን ቆርጦህ ነው የማትጮኸው?...ብትጮህ አያምህ…ምንም አይቀንስብህ…እና ለምናባህ ነው ማትጮኸው? አንት የማትረባ ስልክ…አሁኑኑ አንስቼ ከግድግዳ ጋር ሳላጋጭህ ጩህ…ጩህ ብያለሁ ጩህ! …አይ አይ…አሁንስ አበዛሁት፡፡ ማቆም አለብኝ….ስለሌላ ነገር ማሰብ አለብኝ…እንደውም እንደዚህ ነው የማደርገው…ሰአቴን ካጠገቤ አንስቼ ሌላ ክፍል አደርገዋለሁ….እንደዛ ካደረግኩ አሁንም አሁንም አላየውም…ማየት እንኳን ብፈልግ መኝታ ቤት ድረስ መሄድ ይኖርብኛል…ያ ደግሞ ራሱን የቻለ ስራ ነው….ምናልባት ሰአቴን ደግሜ ከማየቴ በፊት ይደውል ይሆናል….ሲደውል ደግሞ ለስላሳ እና ጣፋጭ ነገር ነው የምሆንለት….ከደወለልኝ….‹ዛሬ ላገኝሽ አልችልም› ቢለኝ እንኳን ‹‹ አይ…አትጨናነቅ ..ጣጣ የለውም›› ነው የምለው…ልክ መጀመሪያ ስንገናኝ እንደነበርኩት ነው የምሆነው…ምናልባት ያኔ እንደበፊቱ ይወደኝ ይሆናል…ያኔ ለስላሳና ጣፋጭ ነበርኩ….በፍቅር ከመያዝ በፊት ሁሌም ለስላሳ እና ጣፋጭ መሆን ቀላል ነው……ግን እኮ አሁንም ቢሆን ትንሽ ትንሽ እንኳን ቢሆን እንደሚወደኝ እርግጠኛ ነኝ…ባይወደኝ ኖሮ ሁለት ጊዜ የኔ ማር አይለኝም ነበር….ፍቅሩ ሙጥጥ ብሎ አላለቀም….ትንሽ…የትንሽ ትንሽ እንኳን ቢሆን ፍቅሩ ጨርሶ አላለቀም፡፡ አየህ አምላኬ….አንተንም እንደገና ከማስቸግርህ ዛሬ እንዲደውልልኝ ብታደርግ ትገላገል ነበር…እንደድሮው አሪፍ እሆንለታለሁ…እንደ ድሮው ይወደኛል…ከዚያ አንተን በምንም አላስቸግርህም…አምላኬ፣ አልገባህም? ለዚህ እኮ ነው እንዲደውልልኝ አድርግ ብዬ የምለምንህ…አረ ተው እባክህ…እባክህ……ቆይ ቆይ….እየቀጣኸኝ መሆኑ ነው? አምላኬ ሆይ መጥፎ ሰው በመሆኔ ቅጣቴ ይሄ ነው? ተናደህብኝ ነው? ግን እኮ ከእኔ የባሱ ብዙ እኩይ ሰዎች አሉ…መቼም እኔን ብቻ ለይተህ አትቀጣኝም…ደግሞ እኮ ሰው የምር መጥፎ የሚሆነው በምግባሩ ሌሎችን ሲጎዳ ነው…አይደለም? እኔ አንድም ሰው ጎድቼ አላውቅም…ታውቀዋለህ…እና ለምንድነው እንዲደውልልኝ የማታደረገው?…አሁን ካልደወለልኝ እግዜር እንዳዘነብኝ አውቃለሁ…እስከ አምስት መቶ አምስት አምስት እየዘለልኩ እቆጥራለሁ…እስከዚያ ካልደወለ እግዜር እስከወዲኛው እንደማይረዳኝ አውቄ አርፌ እቀመጣለሁ…አምስት…አስር…አስራ አምስት…ሃያ …..በቃ፡፡ ይሄው ነው፡፡ እግዜር ጨክኖብኛል፡፡ ጨክነህብኛል አይደል አምላኬ? እሺ…..ይሁንልሃ! ሲኦል ጨምረኝ….ከእኔና ካንተ ሲኦል የማን እንደሚብስ እናያለን…..…ግን አጉል መጨናነቁን ሳላበዛው አልቀረሁም….ምናልባት ለመደውል ዘግይቶ ቢሆንስ? እንዲህ የሚያቀውስ ነገር አለው? ምናልባትም ላይደውል ይችላል…መደወሉን ትቶ ቀጥታ እየመጣ ቢሆንስ? ሲደርስ እያለቀስኩ እንደቆየሁ ሲያውቅ ቢናደድብኝስ? ወንዶች እኮ የምታለቃቅስ ሴት አይወዱም፡፡…..ምናልባት ይሄኔ ወደእኔ እየመጣ መንገድ ላይ ነው…. አረ ቆይ….እኔ ጋር እየመጣ የሆነ ነገር ሆኖስ ቢሆን? አደጋ ደርሶበት ቢሆንስ? መኪና ገጭቶት…ሞቶስ ቢሆን?ወይኔ ጉዴ! ሞቶስ ቢሆን?!....ለነገሩ ቢሞት ይሻለኛል..ያኔ የትም መቅበዝበዙን ትቶ የኔ ብቻ ይሆናል…ሞቶ በሆነ…! በሞተ…!ውይ…ውይ! ምን አይነት ክፉ ሴት ነኝ…..?ሰው እንዴት በሚያፈቅረው ሰው ላይ ሞትን ይመኛል…..?ለነገሩ ሞኝ ነገር ነኝ…ቂል!  አንድ ሰው እደውላለሁ ባለበት ደቂቃ ስላልደወለ ሞቷል ብሎ ማሰብ ከቂልነት ውጪ ምን ይሆናል…..? ወይ ደግሞ…ወይ ደግሞ ሰአቴ ቀድሞ ይሆን እንዴ? ይሄኔ እኮ ትንሽ ይሆናል የዘገየው….ወይ ደግሞ ቢሮ መቆየት ኖሮበት…ስራ በዝቶበት ቢሆንስ? ….ወይ ቤት ሄዶም ሊሆን ይችላል…ከቤት ሊደውልልኝ ፈልጎ….. ከዚያ ልክ ሊደውልልኝ ሲል እንግዳ መጥቶበት ይሆናል….ሰው ፊት ሆኖ ወደ እኔ መደወል እንደማይወድ አውቃለሁ….ምናልባት ይሄን ያህል ጊዜ ስላስጠበቀኝ ተጨንቆም ይሆናል…ምናልባት…ምናልባት እሷ በደወለች ብሎ እየተመኘም ሊሆን ይችላል…..ህም…ለካ…ለካ ልደውልለት እችላለሁ! እኔ ራሴ ልደውልለት እችላለሁ…..!አይ….አይ….አልደውልለትም፡፡ መደወል የለብኝም፡፡ አምላኬ ሆይ….! እባክህ እንዳልደውልለት አድርገኝ…እጄን ያዝልኝ….ሁሉን ነገር አቅልልልኝ አልልህም ግን እባክህ እንዲህ ሆኖ ይሆናል እያልኩ ሰበባ ሰበብ እየደረደርኩ ራሴን እንዳቄል አታድርገኝ…አበርታኝ አምላኬ…አበርታኝ….አልደውልለትም…እስክሞት ድረስ አልደውልለትም፡፡ ለምን ተንፈራፍሮ ድብን አይልም? …ለምን መቀመቅ አይወርድም….…አምላኬ ሆይ፣ በሃሳቤ እንድፀና አበርታኝ…ቢፈልገኝ ያገኘኝ ነበር…የት እንዳለሁ ያውቃል…እየጠበቅኩት እንደሆነ ያውቃል….ቸል ብሎኝ ነው…እንደምጠብቀው ስላወቀ ቸል ብሎኝ ነው…ሁሌም በእጃቸው እንዳስገቡን ሲያውቁ ቸል ይሉናል…ሁሌም…..ግን ደግሞ ብደውልለትና ቁርጤን ባውቅ ሳይሻል አይቀርም……ቆይ ግን…. ደውሎ ደውሎ ስልኬ አስቸግሮት…ኔትወርክ እምቢ ብሎት ቢሆንስ…? አንዳንዴ እኮ እንዲህ አይነቱ ነገር ይፈጠራል….አምላኬ ሆይ…እባክህ ክብሬን እንድጠብቅ እርዳኝ…እንዳልደውልለት እርዳኝ…..አሁን ይሄን ትቼ ስለሌላ ነገር  ማሰብ መጀመር አለብኝ….አለ አይደል….? ዝም ብዬ፣ ፀጥ ብዬ ቁጭ እላለሁ፡፡ ወይ መፅሃፍ ላንብብ እንዴ? ምን ዋጋ አለው…? የዘመኑ ደራሲያን የሚፅፉት ሁሉ በፍቅር ስለከነፉ ደስተኛ ጥንዶች ነው….አሁን እስቲ ማን ይሙት የሚፅፉት ሁሉ በእውኑ አለም ላይ የሌለ ውሸት እንደሆነ ሳያውቁ ቀርተው ነው? ብሽቆች፡፡…አሁን ዝም ብዬ እቀመጣለሁ….ይገርማል ብቻ….የፍቅር ነገር…ይሄኔ እኮ እንዲህ ያደረገችኝ ሴት ጓደኛዬ ብትሆን ደውዬ ‹‹አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው እደውላለሁ ብለሽ ያልደወልሽው?›› እላት ነበር….ፍቅር ግን እንዲህ ያለውን እንደልብ መሆን…ነጻነትን አይፈቅድም…..….አምላኬ ሆይ፣ በቃ እንዲደውል አታደርግልኝም ማለት ነው? እርግጠኛ ነህ…? በቃ…ይሄው ነው ወሳኔህ? አትራራልኝም? እስቲ አሁን በዚህች ደቂቃ ይደውልልኝ ብዬ አልጎተጎትኩህ….እንዲያው ትንሽ ቆይቶ እንኳን እንዲደውልልኝ አታደርግም? ይሄውልህ…ባንድ ነገር እንስማማ.….እኔ አምስት አምስት እየዘለልኩ እስከ አምሰት መቶ…ቀ….ስ….ብዬ …ረ…ጋ ብየ እቆጥራለሁ….እስከዚያ እንደደውል ካላደረግልኝ ግን እኔ እደውልለታለሁ….እሺ? ተግባባን?…አባቴ ሆይ፣ በሰማይ የምትኖር፣ ስምህ ትቀደስ…መንግሰትህ ትምጣ….ከዚያ በፊት ግን እንዲደውልልኝ አድርግ፡፡ እባክህ አምላኬ…እንዲደውልልኝ አድርግ…አምስት…አስር….አስራ አምስት….ሃያ…ሃያ አምስት….ሰላሳ……ሰላሳ አምስት….

አስተያየት