You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
ይህ ጽሑፍ የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙ እንግዶች በተበተነችው ልዩ ኅትማችን የቀረበ ሲሆን ለሰፊው አንባቢ መድረስ እንዳለበት በማመናችን በድጋሜ በዚህ ኅትም ላይ ላይ አካተነዋል::ትዝታ ሲፈርስበአንድ ወቅት ለሥራ ጉዳይ ወደማላዊ ተጉዤ ነበር። አንዱን እሁድ ከሰዓት በኋላ ባረፍኩበት ሆቴል (ሊልንጉዌ መሃል ላይ ሲገኝ ‘ሰን በርድ’ ይሉታል) ራት ለመብላትና ቢራ ለመቀማመስ ወደ በረንዳው ወጣሁ፡፡ ለአንድ ጎልማሳ ጀርባዬን ሰጥቼ ተቀምጬ ቢራዬን ያዝኩ፡፡ ጥቂት እንደቆየሁ ከሩቅ የማውቀው የሚመስል ዘፈን በጣም ዝቅ ባለ ድምጽ ይሰማኝ ጀመር፡፡ ከየት ነው የሚመጣው በማለት ትንሽ ቆየሁ፡፡ ዘፈኑ አላቆመም፡፡ ድንገት ወደኋላዬ ስዞር የዘፈኑ ድምፅ የሚመጣው ጀርባዬን የሰጠሁት ጎልማሳ ካጠለቀው ሄድፎን እንደሆነ ተሰማኝ። ዞሬ አየሁት- ሰውዬውን፡፡ ደመቅ ያለ ጠይም ነው፡፡ ጸጉሩም ድሬድ (ራስታ) በሚባለው መልኩ ተገምዷል፡፡ መጀመሪያ ጃማይካዊ መስሎኝ ነበር፡፡ በድጋሚ ስመለከተው ከዘፈኑ ጋር ከንፈሩ ይንቀሳቀሳል፡፡ ተነስቼ ዞርኩና ፊቱ ካለው ወንበር ላይ ተቀምጬ “ኢትዮጵያዊ ነህ” ከማለቴ ቀና አለ፡፡ እያለቀሰ ነበር፡፡ ደነገጠ፡፡ ምንም ሳይመልስልኝ ወደ መታጠቢያ ቤት ሄደ፡፡ ሄድፎኑን አንስቼ ጆሮዬ ላይ ጣድኩት፡፡ የቆየ የጌታቸው ጋዲሳና የበዛወርቅ አስፋው ሙዚቃ ነበር፡፡ዋለለ ዋለለ ዋለለ…ዋለለ ዋለለ ዋለለ ዋለለ ዋለለ ዋለለማዶ ነው ማዶ ነው ማዶ ነው፤ ማዶ ነው ማዶነው፤ ማዶ ነው ማዶ ነውዋለለ ልቤ ዋለለ፤ ዋለለ ልቤ ዋለለአንችን ሲያይ ድንገት አብሮ እየዋለማዶ ነው ልቤ ከማዶ፤ማዶ ነው ልቤ ከማዶአንተን ሲያይ ድንገት በፍቅርህ ነዶበማለት ይቀባበላሉ፡፡ የጌታቸውና በዛወርቅን ዘፈን ሲጨርስ የአረጋኸኝ ወራሽና የነጻነት መለሰ “ኧረ ተይ ውቢት ኧረ ተው ሸጋ” ቀጠለ፡፡ በማላዊ ምድር…ጎልማሳው ፊቱን ታጥቦ ተመለሰ፡፡ ግርማ ያደታ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ኃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ነው፡፡ አሁን ኑሮው ስደት ነው፡፡ አገሩን ከለቀቀ ወደሃያ አንድ ዓመት ግድም ሆኖታል፡፡ ከአንዲት የዚምባብዌ ተወላጅ ጋር ተጋብቶ የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው፡፡ ሥራቸው ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ ቋሚ የሆነ መኖሪያ የለውም፡፡ በቅርቡም ለሥራ ጉዳይ ኢትዮጵያ ደርሶ መመለሱን አጫወተኝ፡፡ ለምን እንዳለቀሰ አልጠየቅኩትም፡፡ በጨዋታችን መሃል ግን ”I’m too much nostalgic“ መሰለኝ አለኝ፡፡ እንዲያ ስሜት ውስጥ የገባው ምንም ተፈጥሮ ሳይሆን፤ ሲያደምጠው የነበረው ሙዚቃ ወደኋላ ወስዶት የተማረበትን መድኃኔአለም ትምህርት ቤትን፤ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ መንገድ ላይ ቆሞ ሙዚቃ ሲሰማባቸው የነበሩትን ሙዚቃ ቤቶችን፤ ለስላሳዋ የአዲስ አበባ ጸሃይን፤ቆነጃጅቶችን፤ የጁማኣ ሰላትን፤ የራጉኤል ቅዳሴና ነጠላ የለበሱ ሴቶችን፤ የአንዋር መስጊድ አካባቢ ግርግርን፤ ብቻ ሁሉንም ነገር እየደበላለቀ ወደ አእምሮው እንደሚያመጣበትና፤ የደስታ ይሁን የሃዘን ሊለየው በማይችለው መልኩ ስሜቱ እንደሚጎሽበት አወጋኝ። ከሲኒማ ራስ እስከ አውቶብስ ተራ የነበሩትን የሙዚቃ ቤቶች አንድ ሳያስቀር በተመስጦ ዘረዘረልኝ፡፡በአስቴር አወቀና በኤፍሬም ታምሩ ግዙፍ የፎቶግራፍ ፍሬሞች የተዋበው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት በር ላይ መቆም፤ ሶል ኩኩ ሙዚቃ ቤትን እየታከኩ የኬኔዲ መንገሻን ሙዚቃ መስማት ምን ያክል እንደናፈቀው አወራኝ፡፡ ዓለም፤ ዋልያ፤ አክሱም፤ አምባሰል፤ ዜድ እያለ ያልጠራልኝ ሙዚቃ ቤት የለም፡፡ልጅ ሆኖ በየሙዚቃ ቤቱ በር ላይ አዲስ የወጡ ካሴቶችን ሲያዳምጥ ያመሽ ነበር፡፡ ”በዚያን ወቅት ቤት ውስጥ ካሴት(ክር) የሚያጫውት ቴፕ አልነበረንም፡፡ ዛሬ ግን የዓለምን ሙዚቃ ሁሉ ጀርባዬ ላይ ባለ ላፕ ቶፕ ይዤው ነው የምዞረው፡፡ ግን ያ የእጦትና የችግር ጊዜዬ ይናፍቀኛል“ ሲል ጨመረ፡፡ ሁሉም ትዝ እያለው የኋሊት መጓዙን አላቆመም፡፡ ገርሞኝም ግራ ገብቶኝም እኔም ‘ኧረ ተይ ጉብል ኧረ ተይ ሸጋን’ ይዤ በትዝታ ወደ ራሴ ጥንት ተመለስኩ፡፡ለግርማ ይህ ነገሩ ለራሱ ሱስ ሆኖበታል፡፡ ”ለቅሶው ደስታ ቢጤ አለው“ አለኝ፡፡ ይህ ልምዱ ለባዕድ አገር ባለቤቱ ብዙም ምቾት ስለማይሰጣት ወይም ስለማትረዳው ብቻውን ነጠል ብሎ እንደሚያደርገው አወጋኝ፡፡ ኢትዮጵያ ሄጄ ነበር አለ፡፡ ”ኢትዮጵያ ሄጄ ነበር ምንም የለም፤ ስንት ዓመት ስናፍቀው የነበረው ድሮዬ ጠፍቷል“ አለና ሌላ የሚያንቅ ስሜት መጣበት፡፡ ”ምንም የለም ስልህ.. ምንም እኮ ነው፡፡ ዞርኩት ከተክለሃይማኖት አንስቼ እስከ አውቶብስ ተራ፤ ቁልቁል ወደሰፈሬ ኃብተጊዮርጊስ እየተደናበርኩ አሰስኩት… ምንም ነገር አጣሁ፡፡ አለቀስኩ። ሁሉም ፈርሶ ወይም በምን እንደሆን ተጀቡኖ ሁሉ ነገር ጠፋብኝ አለና“ የበለጠ አዘነ፡፡ ”እንዴት የትዝታዬን አንድ የሆነ ምልክት አይተዉልኝም ?“ አለ በቁጭት፡፡ምንድነው ትዝታ? ያለፈን መናፈቅ ሰውኛ ነው፡፡ በዚህ ምድር ቋሚ የሆነ ነገር ቢኖር ለውጥ ነው የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ በየቀኑ ሰውም አካባቢም ይለወጣል፡፡ የምርምሩ ውጤት እንደሚለው ከሆነ ደግሞ የሰው ልጅ በመለዋወጥ እስስትን ይወቅሳል እንጂ በየቀኑ በጥቂቱ እየተለወጣ በየአምስት ዓመቱ ደግሞ ሙሉ የሥሪተ-አቶም ለውጥ እያደረገ እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡ በየአምስት ዓመቱ እንደ አዲስ የሚፈጠረው አካላችን እኛነታችንን በውስጡ የሚያስቀርበት መንገድ የትላንት ትዝታው ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ያለፈ ሁሉ ይናፍቀናል? ከደቂቃ በፊት ወይም ትላንት ማታ ያየነው ነገርስ ለምን በናፍቆት አያዋልለንም የሚሉ ጥያቄዎቸ ይነሳሉ፡፡ትውስታ የዕድሜ ምዕራፍ ( Life Span Retrieval Curve ) አለው፡፡ ይህ የዕድሜ መንገድ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡የመጀመሪያው የልጅነት ዓለም (Period of Childhood Amnesia ) ይባላል፡፡ይህ ዓለም ከውልደት እስክ 10 ዓመት ያለው የቀልበ፟ጡሌነት ጊዜ ሲሆን፤ትንሽ ከስድስት በኋላ ይሻል እንደሁ እንጂ፤ ክፉውንም ደጉን ብዙም መዝግበን የማንይዝበት ወቅት ነው፡፡ሁለተኛው የእሸት ወቅት (Reminiscence Bump) ነው፡፡ ይህ ጊዜ እጅጉን ውብ ነው፡፡ ከ10 አስከ 30 ዓመት ይቆያል ቢሉትም፤ የውበቱ ዘመን ሰንደቅ ጎልቶ ከሩቅ የሚታየው ግን 20 ዓመት አካባቢ ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነው ብዙ ውብ ነገሮቸ በአእምሯችን ተቀርጸው የሚቀሩት፡፡ከ30 ወዲህ ያለው በጥቂቱ የምንመዝግብበት ብዙውን ደግሞ ያለፈውን የምናመነዥክበት ጊዜ ነው፡፡ “ ያሳለፍነው ዘመን ደስታን ያየንበት ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምናለበት” እያልን እህህ የምንልበት! ትላንት የተመዘገበው ሁሉ ትውስታ አይሆንም። ጥልቅ ትዝታ ለመሆን ጊዜ ይፈልጋል፟፟፤ረዘም ያሉ ዓመታትን፡፡ለምን ድሮ ይናፍቀናል (Why do we feel nostalgia) በሚል የተሰራ አንድ የአስራ አምስት ደቂቃ ጥናታዊ ፊልም አለ፡፡ እንደፊልሙ ከሆነ ሙዚቃን የምናጣጥምበትና ያለፈ ትዝታን የምናስቀርበት የአዕምሯችን ክፍል ተመሳሳይ ቦታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ በ17ኛው ክፍለዘመን የኖረው የስዊስ ተወላጁ ሐኪም ዮሐንስ ሆፈር nóstos (የቀዬ ናፍቆት) እና álgos (ህመም) የሚሉ የግሪክ ቃላትን አጣመረና Nostalgia (ያለፈን መናፈቅ) የሚል ቃልን ቀመረ፡፡ የቃላቶቹ ሥሮች በትሮይ ጦርነት ወቅት፤ የጦርነቱ ትራፊ የግሪክ ወታደሮች ያሳዩት የነበረው ወደኋላ የሚጎትት የትውስታ ስሜትን መግለጫ ነበር፡፡ ለዮሐንስ ሆፈር በጊዜው ይህ ቃል የተፈለገበት ምክንያት ደግሞ ለግዳጅ ወደበረሃ የተላኩ የስዊዝ ወታደሮች ጠመንጃቸውን ተደግፈው እያንጎራጎሩ ሲተክዙ መዋላቸው ነበር፡፡ ይህ የወታደሮቹ ቤተሰብና ቀያቸውን አለቅጥ እያሰቡ ሲተክዙና እንባ ሲያቀረዝዙ መዋል፤ ለጦር አዛዦች ትልቅ ፈተና ሆነ፡፡ በመሆኑም ያለፈን መናፈቅ ድሮ ድሮ ምድቡ የህመም ጎራ ነበር፡፡ ለጊዜው እንደመፍተሄ የታየውም መድሃኒት ሙዚቃን ከወታደሮቹ አርቆ ማስቀመጥም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃ ዋነኛው የድሮ ናፍቆትን የሚያባብስ ሞገድ ሆኖ በመገኘቱ፡፡ያለፈን ያለፈን መናፈቅ ጣፋጭ የሆነ የግል ህመም ነው፡፡ ያለፈን መናፈቅ ምሉእ ነው ባይባልም ቦታውና ዐውዱ ሰፊ ነው፡፡ ያለፈን መናፈቅ ውስጥ ያለ ሰው አባቱን ወይ እናቱን ወይም የሴት ጓደኛውን አለያም አንድ የቅርብ ወዳጁን ለብቻ ገንጥሎ አይታየውም፡፡ ትልቅ የቦታና አውድ ምስል ነው በአዕምሮ የሚቀመጠው፡፡ በዚያ የቦታና የዐውድ ምስል ውስጥ የሚታየው ብቸኛ ሰው ራሱ ነው፡፡ “we aren’t so much thinking about the person we were with but rather the person we were when we were with him or her” እንዲሉ፡፡ማኀበራዊ ትውስታ (Collective Memory)ትዝታ ጥልቅ የሆነ የግል ስሜት ይሁን እንጂ አንድን ቦታና ዘመን የሚጋሩ ሰዎች የየራሳቸውን ዓለም ይዘው የሚገናኙበት ቦታም ነው፡፡ አንደኛው በሌላኛው ውስጥ የተሳለውን ምስል በአግባቡ ባይረዳው እንኳን የቁዘማው ምክንያት ይገባዋል፡፡ በዚህም አንድ ዘመንን የሚጋሩ ሰዎች በአንድ ነገር ይግባባሉ፡፡ ያለፈ ዘመናቸው ውብ እንደነበረ፡፡ “memoria praeteritorum bonorum, ‘the past is always well remembered” እንዲሉ ሮማውያን፡፡ግርማ ያደታ ይህንን እውነታ አስረጂ ነው፡፡ ዚምባቡዌ ተወልዳ ካደገችው ባለቤቱ ጋር በቦታም ባይሆን በጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ይገናኛሉ፡፡ በ80ዎቹና በ90ዎቹ የተዘፈኑ ዓለም ዓቀፍ የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች ሁለቱንም በጊዜ ወደኋላ ያሳፍሩዋቸዋል፡፡ ለሱ ምን እንደሚታየው ለእሷ ምን እንደሚታያት ባይተዋወቁም ከቁዘማ ውስጥ የሚመነጨው ደስታ ግን ሁለቱም ያውቁታል፡፡ የነዚህ ቢጤ ሰዎች በርክተው ሲታዩ ነው ማኀበራዊ ትውስታ (Collective Memory) የሚፈጠረው፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች አንድን ዘመንና ቦታ በክፉም በደግ የተጋሩት እንደሆነ ቦታ ቢለያያቸው እንኳን ማኀበራዊ ትውስታቸው ጠንካራ ነው፡፡ከመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ጋር የተፋቀው ትውስታላላፉት ሃያ ዓመታት አዲስ አበባ ለ’መልሶ ማልማት’ በሚል ተፈነቃቅላለች፡፡ ግርማ ትውስታዎቼን አፈረሱብኝ በማለት የሚጠቅሳቸው ቦታዎች አሜሪካ ግቢን አንስቶ እስከ አውቶብስ ተራ ያለው ሠፈር የፈረሰው ለመልሶ ማልማትና ለቀላል ባቡር ዝርጋታ ነው፡፡ በመርካቶና በአውቶቢስ ተራ አካባቢ የዘመን ድምፅ የሆኑ ጥዑም ዜማዎችን ለድፍን የሀገሪቱ ሙዚቃ አፍቃሪዎች በማድረስ የዜጎችን መንፈስ አስታመው፣ አስፈንድቀውና አለምልመው የኖሩ ሙዚቃ ቤቶች የትናንት ሁኔታቸው እንኳን ያለው በናፋቂዎቹ ልቦና ውስጥ ነው፡፡ እናም ናፋቂዎቹ ሲያልፉ ጠፍተው ይቀራሉ፡፡ የፌደራሉ ባሕል ሚኒስቴርም ሆነ የከተማው ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሥነ-ልቦናዊ ዋጋ ሊኖራቸው ይችላል ብለው የሚያስቡ አይመስልም፡፡ የከተማ ሕዝብ ያለምንም የፈጠራ ባህል ውሎ የሚያድር፤ ሰንብቶ የሚከርም ይመስል፤ ከተሜው ያዳመጠው ዘፈን፤ ያየው ቴአትርና ሥዕል፤ ያነበበው ግጥምና ልቦለድ ሊጠበቅ እንደሚገባው ሳይታሰብ የትዝታዎቹ አድባር የሆኑ ሥፍራዎች እንደ ተራ የሸቀጥ ገበያ ቦታ በመልሶ ማልማት ሥም ያለ አስታዋሽ ይነሳሉ፡፡ የከተማ ሰው ያለ ጥዑመ ዜማ ኑሮውን ገፍቶ ዛሬ ላይ የደረሰ ይመስል፤ ሙዚቃ ቤቶቹ ፈርሰው ቀርተዋል፡፡ማርክ ክሪንሰን ባዘጋጀው የከተማ ትዝታ (Urban Memory) በተሰኘ መጽሐፉ እንደተገለጸው ከተሞች የትዝታ አምባዎች ናቸው፡፡ እንደ መጽሐፉ ከሆነ የድኅረ-ዘመናዊነት (postmodern) ጸሐፊዎች ትላልቅ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን የሚተክሉት በከተሞች ትዝታና የኋሊት ታሪክ ላይ ነው፡፡ አሁን አሁን የከተማና የሥነ-ህንጻ ባለሙያዎችም ይህን የሰው ልጅ ልብ የሚሸከመውን ትውስት ግምት ውስጥ የከተተ ንድፍን በሥራቸው ውስጥ ሲያካትቱ ይታያሉ፡፡ አልፎ አልፎም ዘመን ተሻግረው የሚታዩ በርካታ ቦታዎች አሉ፡፡ በእውቀቱ ስዩም በአንድ ጽሑፉ አሜሪካ ውስጥ አብርሐም ሊንከን በነበረ ጊዜ የተሰራ ሆስፒታል ዛሬም አለ ይልና፤ በኢትዮጵያ ቋሚ ሆኖ የሚቀር ነገር እንደሌለ እና ሁሉ ነገር ተለዋዋጭ መሆኑን ገልጾ ኢትዮጵያ ውስጥ ተለውጦ የማታገኘው መንግስትን ብቻ ነው ሲል የተለመደ ሽሙጡን ይጨምራል፡፡ማኀበራዊ ትውስታ- “ትዝታን በድንጋይ ይዤልሃለሁ”የማንችስተር ከተማ ጎልማሶችና ባልቴቶች ስለወጣትነት ዘመናቸው ሲያወሱ ከአፋቸው የማይጠፋና በትዝታ ይዞ ሰማይ የሚያደርሳቸው አንድ ቦታ አለ፡፡ ይህ ቦታ “ክለብ አቼንዳ” ይባላል፡፡ ክለብ አቼንዳ በእ.አ.አ. በ1982 ተመስርቶ በ1997 በኪሳራ ተዘጋ፡፡ 18 ወራትን እንዲሁ ቆይቶ ቦታው ለአፓርትመንት ግንባታ ፈረሰ። የመፍረሱ ዜና ለብዙው የማንችስተር ወጣት እጅግ ልብ የሚነካና የሚያሳዝን ነበር፡፡ አቼንዳ የምሽት ክለብ ብቻ አልነበረም፡፡ ለብዙ የማንችስተር ወጣት ክለብ አቼንዳን አፍቅረውበታል፤ ጓደኛ አፍርተውበታል፤ ደስታና ሀዘንን ተጋርተውበታል፤ በሞቅታ ደንሰውበታል፤ በጉብዝናዋ ወራት ማዶናን ሳይቀር ከክለቡ መድረክ ላይ አጣጥመውበታል፡፡ ሁሉ ነገራቸው እዚያ ክለብ ውስጥ ታሽጎበት የተቀመጠ ያህል ይሰማቸው ነበር፡፡አንድ ቀን ጨካኝ ሆኖ መጣ! ያን ኹሉ ዓለም ያሳያቸው የከተማቸው አድባር፤ ክለብ አቼንዳ ሊፈርስ ተወሰነበት፡፡ የዚህን ኹሉ ትዝታቸውን ሽታና ጠረን ከጓዳቸው ማራቅ ያልፈለጉት ማንችስተሮች የህንጻውን ፍርስራሽ ጡቦች ሁሉ በጨረታ እየገዙ ወደቤታቸው እንባ እየተናነቃቸው ሄዱ፡፡ ማንችስተሮች ክለብ አቼንዳን አይረሱትም፡፡ ሊረሱት ቢሉም በክለቡ የሰሟቸው ታላላቅ ሙዚቃዎች ድንገት ሽው ባሉባቸው ቁጥር፤ በጨረታ የሸመቷቸውን ጡቦች ካሉበት አውጥተው አልያም በሳሎናቸው ውስጥ በክብር አስቀምጠው፤ በትዝታ ሃያ ዓመታትን ወደ ኋላ አርቀው ይነጉዳሉ፡፡የማኀበራዊ ትውስታ ጠቀሜታአካባቢው ፈርሶ ሲሠራ ማኀበረሰባዊ አገልግሎት ከሰጠ መንዶች እና ህንጻዎች ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ከተገነቡበት ተጨማሪ ረብ ያለው የማይመስላቸው ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ መሠረታዊ ፍላጎቶች ባልተሟሉበት ሀገር ስለትዝታ እና የቀድሞ ዘመን መናፈቅ ቅንጦት ነው የሚሆነው ብለው ይከራከራሉ፡፡የታሪክ ተመራማሪውና በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ታምራት ኃይሌ (ፒ.ኤች.ዲ) “ማኀበራዊ ትውስታ የአንድን ማህበረሰብ የባህልና የጋራ ሃብቱን የሚያቆይበትና ወደፊት የሚያሻግርበት እንዲሁም ዘላለማዊ የሚደርግበት ትልቅ የማይዳሰስ ኅብቱ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ “ከዚህም በላይ” ይላሉ። “ከዚህም በላይ ማኀበራዊ ትውስታ ያለውን የመንግስት አስተዳደር ወይም የፖለቲካ ዘይቤ የሚታገልበት ወይም ያለመቀበሉን (Resistance or rejection) የሚያሳይበት መሣሪያው ነው፡፡ በዚህም የማይመቹ የፖለቲካና አስተዳደራዊ መንገዶች የሚያመጡትን ጉዳት ሊቀንስ ይችላል” ሲሉ ያክላሉ፡፡በዘፈቀደ የሚደረግ ከተማን አፍርሶ የመገንባት ሒደት ማኅበረሰብን ከትውስታው የሚበጥስ ድርጊት እንደሆነ የሚያወሱት ምሑሩ፤ ማንኛውም ከተማን አፍርሶ የመገንባት ሒደት የታሪክ ባለሙያዎችን ያካተተ ቢሆን ትውልዱን በባህልና በአእምሮ የደረጀ ከድሮው በቀላሉ የሚገናኝ ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡ ማንኛውም የቁስና የግንባታ ትኩረት ትልቁን የሰው ልጅ ልብ ከረሳ ኢላማውን ሊመታ አይችልም ሲሉም ያክላሉ፡፡ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ያሉ ትዝታዎችን በሐውልት ወይም ሙዚየም ቤቶችን በመገንባትም ለማቆየት የሚጥሩ አገራት በርካታ ናቸው በማለት ይደመድማሉ፡፡ግርማ እና መሰሎቹን ያሳዘነው ማኀበራዊ ትውስታን ግምት ውስጥ ያላስገባው ልማት ልብ እየሰበረ መሄዱን የተወ አይመስልም፡፡ በቅርቡ እንኳን በመዲናዋ እምብርት ላይ የሚገኘውን የበጎ አድራጎት ህንጻ ይፈርሳል አይፈርስም የሚለው ክርክር አንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዱን በማንሳት አንዱን በመጣል በመልሶ ማጥፋት የታጀበው መልሶ ልማት መቼ ይሆን የሚገራው?