You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
ትርፍና ኪሳራ ዮሃን ቦርግስታም ባለፈው ዓመት በወርሓ ጥቅምት ማብቂያ አከባቢ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡ አምባሳደሩ የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጡ ሀገሪቱ አብዛኛውን ማኀበረሰብ ያካተተ ሊባል በሚያስደፍር ሕዝባዊ ተቃውሞ ስትናጥ ነበር፡፡ በገዢው ፓርቲው ውስጥ አሸናፊው ማን እንደሆነ የማይታወቅ ውስጣዊ ትግግል የሚካሄድበት ጊዜ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየኹና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እርሳቸው ወክለው ወደመጡበት አህጉር፣ አውሮጳ ህብረት ባሳለፍነው ሳምንት አቅነተው ተመልሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮጳ ታላላቅ ሀገራት መሪዎችን አግኝተው በሚያነግሩበት ቅጽበታት አዲስ ዘይቤ የአምባሳደሩን የአንድ ዓመት ትዝታ ለአፍታ ስትፈትሽ ነበር፡፡ከጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይአሕመድ ሹመት በኋላ በኢትዮጵያ የሆነው ነገር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮጳም ቀልብን የሚጎትት እንደነበር ይናገራሉ፤ አምባሳደር ዮሃን ቦርግስታም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መፈታት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባቦታዊ የሆነው ሙሉዕ የሆነ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማቆም ያሳዩት ቀርጠኝነት፣ የተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ነጻ ለማድረግ መወሰናቸው ለአምባሳደሩ በልዩ ሁኔታ ያስገረሟቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ “በአጠቃላይ በኢትዮጵውያን ዘንድ የሚታየውን የለውጥ ንፋስ መንፈሱን ቀጥሎ፣ ነገ ወደተሻለ ብልጽግና እና ዴሞክሲያዊ ስርዓት ያለምንም ዘውጋዊ አድሎ እንሸጋገራለን፤ የሚል ተስፋ ያለውን የጋለ ስሜት እንጋራለን፡፡” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የጋለውን የለውጥ ስሜት እንደሚጋሩ የመሰከሩላቸው የአውሮጳ መዲናዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተቀብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ጥቅምት 19 2011 ዓ.ም. በፈረንሳይ ፓሪስ የጀመሩት ጉብኝት፤ በጀርመን በርሊንና ፍራንክፈርት የቀጠለ ነበር፡፡ በጉብኝቱ ጠ/ሚ ዐቢይ ከፈረንሳይ፤ ከኦስትሪያና ከጀርመን መሪዎች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፤ ኢኮኖሚ፤ በወታደራዊና በባህል መስኮች ያሏቸውን ግንኙነቶችን ለማጠናከር ሀሳቦች ተለዋውጠዋል፤ ቃሎችም ተገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠ/ሚኒስትሩ የዚህ ሳምንት የአውሮፓ ጉብኝታቸው “አንድ ሆነን እንነሳ፤ ነገንም እንገንባ!” በሚል መሪ ቃል በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በጀርመን ፍራንክፈርት ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡የአውሮፓ ጉዞው በዚህ ሁኔታ ከጥቅምት 19 እስከ 21 2011 ዓ.ም. ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲቀጥል በአገር ውስጥ በተለይ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትጥቅ መፍታት አለመፍታት ጋር በተያያዘ በምዕራብ ኦሮሚያ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በኦነግ ታጣቂ ናቸው በተባሉ ኃይሎች መካከል ግጭት ተከስቶ የሰው ሕይወት እንደጠፋ ልዩ ልዩ የዜና አውታሮች ዘገባዎችን አቅርበዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ለማ መገርሳም ጉዳዩን አስመልክቶ ጥቅምት 20 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥት ከአሁን በኋላ የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር ወ/ሮ አይሻም የአገር መከላከያ ሠራዊት ጸጥታን ከማስከበር ወደ ኋላ እንደማይል አስታውቀዋል፡፡ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡበት ከመጋቢት 24 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ረዣዥም የውጭ ጉብኝቶች ሲያካሂዱ ይህ የመጀመሪያቸው አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል ወደ አፍሪካ ቀንድና ሌሎች አጎራባች አገራት፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ፤ ወደ አሜሪካና ወደ ቻይና ተጉዘዋል፡፡ ጉዞ ባደረጉባቸው በእነዚህ ወቅቶች በአገር ውስጥ በርካታ ቀውሶች ተከስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ ሞትና ተከታታይ የአገር ውስጥ መፈናቀሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኞች እና ታዛቢዎች እንደሚሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በአገር ውስጥ ያለውን የጸጥታና የአስተዳደር መሰረት ማደላደል እንደሆነ በመግለጽ ረዣዥም የውጭ ጉብኝቶችን ማካሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ይደመጣል፡፡ ለመሆኑ የውጭ ጉብኝቶች ምን ጉዳዮች ላይ አተኩረው ተካሄዱ? በጉብኝቶቹ ምን ለማ? ምንስ ጠፋ? ይህ ሪፖርታዥ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መጠነኛ ዘገባ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝትጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን ያደረጉት በሚያዝያ 20 እና 21 2010 ዓ.ም. በጎረቤት አገር ጅቡቲ ነበር፡፡ በጅቡቲ በነበራቸው ጉብኝት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅምና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ስላሉ አጠቃላይሁኔታዎችም መክረው እንደነበር ይታወሳል፤ ወደብን ጨምሮ በተለያዩ የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ላይ ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በተደረሰው የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ መግባባት መሰረት ኢትዮጵያን በጅቡቲ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራት ያደርጋታል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል። ይህም ኢትዮጵያ በወደብ ክፍያ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲኖራት የማስቻል አቅም እንደሚኖረው በወቅቱ ተዘግቧል።ከጅቡቲ በመቀጠል ጠ/ሚ ዐቢይ የውጭ ጉብኝታቸውን ያደረጉት በሱዳን ካርቱም ነበር፡፡ የጅቡቲ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ ከአንድ ቀን በኋላ ማለትም ሚያዝያ 23 2010 ዓ.ም.ወደ ካርቱም ያቀኑት ጠ/ሚ ዐቢይ ከአገሪቱ መሪዎች ጋር በጸጥታ፤ በህዳሴ ግድብ እና በሌሎች የልማት ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ ርእሰ መንግስት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟቸው መሪ የሱዳኑ ጄኔራል አል-በሽር ሲሆኑ አጋጣሚው የተፈጠረው አል-በሽር ሚያዝያ 13 2010 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ ለተዘጋጀው የጣና ፎረም ሥብሰባ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ በሱዳን ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያገናኝ ሦስት አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባትና የምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል የሆነ የባቡር መሥመር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ፍተነግሯል። በተመሳሳይ በድንበሮች አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠርና የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከመግባባት ላይ ተደርሷል። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ አቋም ያላቸውና ግድቡ በተለይም ለቀጣናው አገራት በሚሰጠው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን ታውቋል፡፡ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝታቸውን ቀጥለው ያካሄዱት ወደ ኬንያ ናይሮቢ ነበር፡፡ ጉብኝቱ የተካሄደው በሚያዝያ 28 እና 29 2010 ዓ.ም. ሲሆን ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ናይሮቢ ያቀኑት ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በቀረበላቸው ግብዣ ነበር። የግብዣ ደብዳቤውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ ይዘው የመጡት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማን እንደነበሩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በጉብኝቱም በተለይ የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል ገብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በሶማሊያም አጭር ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ በጉብኝታቸውም በአገሪቱና በቀጠናው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ ከአገሪቱ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡የጠ/ሚኒስትሩ ጉብኝት በጅቡቲ፤ በሱዳን፤ በሶማሊያና በኬንያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ውጪም ዶ/ር ዐቢይ በሰኔ 1 እና 2 2011 ዓ.ም. ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ በማቅናት ከአገሪቱ መሪ ዩሪ ሞሶቬኒ ጋር፣ ከኢጋድ ጋር በተገናኘ በደቡብ ሱዳን ሠላም ሂደትና በሶማሊያ ፀጥታ ላይ ተባብረው መስራታቸውን ስለሚቀጥሉበት ሁኔታ ተነጋግረዋል፤ በኡጋንዳ ብሄራዊ የጀግኖች በዓል ላይ ታድመዋል የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ ከኡጋንዳ ጉብኝታቸው በኋላ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ ያደረጉላቸውን ግብዣ ተቀብለው ወደ ግብጽ ካይሮ ያቀኑት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዚደንቱ ጋር በሁለቱ አገሮች ግንኙነት እና በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡በአፍሪካ ቀንድ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የዶ/ር ዐቢይ ጉብኝት ሐምሌ ወር መግቢያ ላይ የተካሄደው በኤርትራ አሥመራ ነበር፡፡ ሁለቱ አገራት በወሰን መሬት ይገባኛል ሰበብ ከሀያ ዓመታት በፊት ያካሄዱትን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አቋርጠው ቆይተዋል፡፡ ዕለተ እሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዐቢይ በርካታ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮችን አስከትለው አስመራ ሲገቡ የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የኤርትራ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ከተለያየ ህብረተሰብ የተውጣጡ ታዋቂ ኤርትራውያን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በዕለቱ በአሥመራ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ ኤርትራውያውን በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተውጠው እንግዳቸውን ተቀብለዋል፡፡ የዐቢይ የኤርትራ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት የተፈራረሙበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉንም የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በመጎብኘት ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በአዲስ መልክ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለ አሳይተዋል።ወደእነዚህ የአፍሪቃ ሀገሮች ያደረጉት ጉዞ በአብዛኛው በጎ አስተያየቶችን ቢያስተናግድም ከህዝብ ግንኑነት ስራዎች በዘለለ የሀገሪቱን ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ነው ለማለት እንደማያስደፍር የሚናገሩ አልታጡም፡፡ በአዲስ አበባ የኒቨርሰቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ አዳነ አለማየሁ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የሚሄድ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ፖሊሲው ‘ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የወንድማማችነት ግንኙነት ትፈጥራለች’ እንደሚል የሚናገሩት መምህሩ ይህ በዶ/ር ዐቢይ ጉዞዎች ከሞላ ጎደል መሳካቱን ይገልጻሉ፡፡ ሀገሪቱ ወደብ ዐልባ በመሆኗ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ያላት መስተጋብር ጤናማ መሆኑ ጠቃሚነቱ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ሌላው በዚህ ጉዞ እንደስኬት የሚቆጠረው ጎረቤታም ሀገሮች የሚኖራቸው የእርስ በርስ ጣልቃ ገብነት(mutual intervention) አወንታዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የተቃዋሚዎች ማዕከል ከነበረችው ኤርትራ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመስረት መንግስት የነበረበትን የደኅንነት ስጋት በእጅጉ የሚቀንስ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ከኤርትራ ጋር የተደረገው እርቀ ሰላም ዝርዝር መረጃ ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ በተደረገው ስምምነት ላይ ብዙዎች እምነት እንዳይጥሉ አደርጓቸዋል፡፡ በተለይ እንዲሁ በ1983 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ በመነጠል ነጻ ሀገረ መንግሥት ስትመሰርት የተቋጠረ ውል አለመኖሩ የኋላ የኋላ ብዙ ዋጋ ከማስከፈሉ ጋር ተያይዞ ቢያንስ ከታሪክ መማር እንደሚገባ የሚከራከሩ አሉ፡፡ አቶ አዳነ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙት ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ ዝርዝር ነገሮች ሳይታወቁ እንዲሁ ግንኙነቱ መቀጠሉ ለስምምነታቸው መርህ አልባ ገጽታ እንደሚያላብሰው ያላቸውን ፍርሃት ከመግለጽ አልቦዘኑም፡፡ መምህሩ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀድሞ ተሞክሮ ዝርዝር ነገሮችን ከማሳወቅ እንዲቆጠብ ተጽእኖ ሳያደርግበት እንዳልቀረ የሚገልጽ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝትሳውዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በመካከለኛው ምስራቅ የጎበኟቸው አገራት ናቸው፡፡ ከግንቦት 9 2010 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ ለተከታታይ ጥቂት ቀናት በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢንሰልማን ጋር መወያየታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል። ጠቅላይ ሚኒትሩ ወደ ሪያድ ያመሩት የሳዑዲው ንጉስ ቢንሰልማን አብዱልአዚዝ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ነበር፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ ምክንያቶች በሳዑዲ ዓረቢያ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረባቸውንና በምላሹም አንድ ሺህ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲፈቱ ማድረጋቸው ይታወሳል። የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢንሰልማን በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት ወቅት፤ ኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ጥረት ሳዑዲ አረቢያ እንደምትደግፍ ተናግረው ነበር። በጉብኝቱ ሁለቱ አገሮች ትርጉም ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማድረግ፣ በኢነርጂ እና ግብርና ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸውን በግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳጠናቀቁ ጠ/ሚኒስትሩ በቀጥታ ያመሩት ወደ ተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ነበር፡፡ የአቡዳቢ ጉብኝታቸው ውጤት በሌሎች አገራት ካደረጓቸው ጉብኝቶች ሁሉ የተለየ አፋጣኝ ውጤት ያስገኘ ነበር፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት የኤመሬትሱ አልጋ ወራሽና የጦር ኃይሎች አዛዥ ልዑል ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናሂያን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ጊዜ በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ የሚሆንና አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ቀውስ የሚያስታግስ 1 ቢለዮን ዶላር እና ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል 2 ቢሊዮን ዶላር በብድር መልክ መስጠታቸው ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምስራቅ ያደረጉት ጉዞ ስኬታማ እና ሀገሪቱ ያለባትን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ የተደረገ የብልሃት እርምጃ እንደሆነ ብዙዎች ያስባሉ፡፡ ሰፊ ሕዝበ ሙስሊም ያላት ሀገር ከመካከለኛው ምስራቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠሯ ተገቢ እና የእጅ አዙር ጦርነትን(proxy war) የሚያስቀር ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ በጠላትነት የመመልከት አባዜ እንዲለዝብ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ክፍለ ዓለም ጉዟቸው የሀገሪቱ ትርፍ እና ኪሳራው ያልተለካ እንደሆነ የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ፡፡ በተለይ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶች የሚሰጥ 36 ሔክታር መሬት በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንደተዘጋጀ መገለጹ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ ለዚህ ጥርጥር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ያደሩጉትን ስምምነት ዝርዝር ይፋ አለማድረጋቸውን እንደምክንያት ይቀርባል፡፡ ለመምህር አዳነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን ጉዳዮች ይፋ እንዲያደርጉ መጠበቅ የሀገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ “እንደዚህ አይነት ግልጽነት እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው በደምብ በተቋቋመ እና በሚሰራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው፡፡ ሃገሪቱ ባችበት በዚህ ወቅታ ሁኔታ ውስጥ እንደዚህ አይነት ግልጽነትን መጠበቅ ቅቡልነት (legitimate ground) ያለው አይደለም፡፡” በማለት ይናገራሉ፡፡የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት“ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን በማስከተል በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ መጓዛቸው ብዙ የተባለለት ጉብኝት ነበር፡፡ በአንጻራዊነት ረዥም ጊዜ በወሰደው የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በዋሽንግተን፤ በሎስ አንጀለስ እና በሜኔሶታ ከኃይማኖት መሪዎች፤ ከታዋቂ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፤ የማህበራዊ ድረ ገጽ አክቲቪስቶች እና ከመላው ኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተዋል፤ ተወያይተዋልም፡፡ በወቅቱም ለዘመናት በውጭና በአገር ውስጥ ተብሎ በሁለት እንደተከፈለ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሶች ወደአንድነት የመጡበት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው አገራቸውን ሊረዱ የሚችሉበት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ሀሳብ የተጠነሰሰበት ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ረዥም ጉብኝታቸው መጀመሪያ ላይ የሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂኒየር ሥመኘው ከመሞታቸው እና ከቀብር ስነ ስርዓቱ ጋርም በተያያዘ በተለይ መዲናዋ በውጥረት ላይ እንደነበረች ይታወሳል፡፡አሜሪካ ቀድማ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ለተነሳው የለውጥ ኃይል ያላትን ድጋፍ በግልጽ በማሳየቷ ይህ ጉዞ ያስገኘው ጥቅም ብዙም ትኩረት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ይህንን የሚያስረዱ በርካታ ክንዋኔዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት ተስተውለዋ፡፡ አሜሪካ በዋነኛነት በቀጠናው ያላት ፍላጎት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጥያቄዎች መመለስ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ አሜሪካ ኤች.አር128ን (HR128) በማጽደቅ በኢትዮጵያ መንግሥት ጫና እንድታሳድር በሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኀበረሰብ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ከመንግሥት አምባገነናዊ አካሄዶች በመነሳት በሀገሪቱ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ አፍራሽ ሚና የነበረውን የዲያስጶራ ማኀበረሰብ መቀለብስ የዚህ ጉዞ ዋንኛ ዓላማ እንደነበር ብዙዎችን የሚያስማማ ነው፡፡ ይህም በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ከምንጩ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አካል ተደርጎ በብዙዎች ተወስዷል፡፡የቻይና ጉዞጠ/ሚኒስትር ዐቢይ እስከ ነሐሴ ድረስ ባሉት አምስት ወራት ብቻ የውጭ ጉብኝቶቻቸው በአፍሪካ፤ በመካከለኛው ምስራቅና በአሜሪካ የተወሰ አልነበረም፡፡ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኤዥያ በማቅናትም በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ቻይና ተሳትፈዋል፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከየትኛውም አገር የላቀች ስትሆን በኢትዮጵያም ያላት መዋዕለ ንዋይም በአፍሪካ ካሏት 19 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች (Specialized Economic Zones) በመጠኑ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን በመደበኛ የፎረሙ ስብሰባ ላይ ከመገኘታቸው ባሻገር ከቻይና መሪዎች ጋር መወያየታቸው ዲፕሎማሲያዊ ትርጉም ያለው እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከስምንት ወራት በፊት ኢትዮጵያ በአመራር ለውጥ ምክንያት ገብታበት በነበረው የቀውስ ወራት ቻይና ለአገሪቱ ምንም አይነት ብድር እንደማትሰጥ አስታውቃ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዞ እግረ መንገዳቸው ያደረጉት ቢሆንም ከቻይና መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲለሳለስ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከቱ የሚያስማማ ነው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አዳነ አለማየኹ ሀገሪቱ ከቻይና ጋር የነበራት የቀደመ ግንኙት ሀገሪቱ እንድትዳከም፣ ቀውስ እንድትገባ እና በዕዳ እንድትዘፈቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያሰምሩበታል፡፡ ይህ እንዲሆን የቻይና መንግሥት ከሀገራት ጋር ባለው ግንኙነት ምንም አይነት ቅድመ ኹኔታ የማያስቀምጥ፣ ከገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎች ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ያለው፣ በሀገሮች ሉዓላዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ አደገኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ማለሳለስ እና እዳ ቅነሳ ላይ ማተኮራቸው የበሰለ እርምጃ እንደሆነ አቶ አዳነ ያስረዳሉ፡፡የአውሮፓ ጉብኝትከጥቅምት 19 እስከ 21 2011 ዓ.ም. በፈረንሳይና በጀርመን በተካሄደው የውጭ ጉብኝት ጠ/ሚኒስትሩ ከአውሮፓ መሪዎችና ከኢትዮጵያውያን ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ንግግርና ውይይት አካሂደዋል፡፡ የላሊበላን ቅርስ ለመታደግ፤ የኢትዮጵያን ጦር ሠራዊት በላቀ ደረጃ ለማዘመን፤ በኢኮኖሚው ረገድም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ያላቸውን ስምምነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በተለይ ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በማውጣት ፈረንሳይ የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ለማዘመን እንደሚሰሩም ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ቃል ገብተዋል። ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚው ማሻሻያ ከዓለም ባንክ ከምታገኘው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ፈረንሳይም የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም ተነግሯል፡፡ በአውሮፓ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የማቋቋም ጉዳይ ሌላው የአውሮፓ ጉብኝት ግብ ነበር፡፡ በፍራንክፈርት በነበረው የጠ/ሚኒስትሩና የኢትዮጵያውን ውይይት በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ይህ ጉዞ የነበረውን ስኬታማነት ‘ከጠበቁት በላይ’ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ ይህ በሁለት መልኩ ይገለጻል፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ጉዟቸው መልስ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መልክ ይዞ ነበር፡፡ በተለይ የዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል መጨመር፣ በቡራዮ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በነጻነት እና በህይወት የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ መውደቅ ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስሩ የነበረውን አመኔታ እየሸረሸረው እንደነበር የሚታይ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በአውሮጳ የሚኖረው የኢትዮጵያውያን ማኀበረሰብ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊያቀርብባቸው ይችላል የሚል ትንበያ ነበር፡፡ ይሁንና በአውሮጳ የሚኖረው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ድጋፍ በመግለጽ ችግሮች እንዲፈቱ ከእርሳቸው ጋር በጥያቄ እና በሌሎች መንገድ መስተጋብር መፍጠር መሞከሩ እንደታላቅ ድል የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አውሮጳ ከመጓዛቸው በፊት በእምቦጭ አረም መስፋፋት አደጋ ወደተጋረጠበት የጣና ሀይቅ እና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ወደሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መሄዳቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚከራከሩ አልታጡም፡፡ ለፖለቲካል ሳይንስ መምሀሩ አዳነ አለማየኹ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቅቡልነት ስር እየሰደደ እና የማይናወጥ ወደመሆን እያደገ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ሁለተኛው በዚህ ጉዞ እንደስኬት የሚታየው ከፈረንሳይ እና ጀርመን መንግስታት ጋር የነበረው መስተጋብር ነው፡፡ የታላቋ ብሪታንያ በህዝበ ውሳኔ ከአውሮጳ ህብረት መልቀቅን ተከትሎ ወትሮም የፈረጠመ ክንድ ያላቸውን ፈረንሳይ እና ጀርመን ተሰሚነታቸው የበለጠ እንዲጎላ አድርጎታል፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስተሩን ኢትዮጵያ የየትኛውም ሀገር ስጋት እንዳልሆነች ዓላማዋም ሀገሪቱ ያለችበትን ኹኔታ ማሻሻል እንደሆነ በመግለጽ የመንግሥታቸውን ፍላጎት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር መሆኑን በትክክል የማስቀመጥ ብቃት ያረጋገጠ ነበር፡፡አምባሳደር ዮሃን ቦርግስታም ከሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ጋር የተደረገውን የድጋፍ ስምምነት ዝርዝር እንደሌላቸው በመጥቀስ ነገር ግን ህብረቱ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዳብር የሰቪክ ማኅበራት ድጋፉን እንደሚቀጥል እና አጋርነቱ መንግሥትን በመደገፍ ላይ ብቻ እንደማይመሰረት እና ህብረቱ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለውን ቀርጠኝነት እንደሚቀጥል ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጾታ እኩልነትን በኢትዮጵያ ለማስፈን ካቢኔያቸው ሀምሳ በመቶ በሴቶች እንዲሆን ማድረጋቸው እና ክብርት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እንዲሆኑ መምረጣቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከፍተኛ አድናቆትን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ የአውሮጳ ጉዟቸውም ይህንን በጎ ጅምር ከፊቱ ማስቀደሙ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ማድረጉ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይሁንና ይህ ሹመት ከጾታ ባሻገር የተመራጮቹን ብቃት ግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆን የበለጠ ጥሩ ይሆን እንደነበር የሚከራከሩ ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት አይባልም፡፡ አምባሳደር ቦርግስታም በሌሎች ሀገሮች ሹመት አሰጣጥ ጥራት ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈቅዱ ገልጸው በጥቅሉ ግን እነዚህ የካቤኔ አባላት የተሾሙት ሴት በመሆናቸው ሳይሆን ቁርጠኛ እና ብቁ ኢትዮጵያውን በመሆናቸውን እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል፡፡አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ያለውን መልካም ጅምር እርሳቸው የሚወክሉት ህብረት በበጎ እንደሚያየው ይገልጻሉ፡፡ ስትራቴጂካዊ ስፋራ የምትገኘው እና ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያቀፈችው ኢትዮጰያ የሚከሰት ነገር ምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን ህብረቱ ላይም ተጽእኖ እንደሚያሳድር የሚናጋሩት አምባሳደሩ የአውሮጳ ህብረት እ.ኤአ. ከ2014-2020 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ እስከ 65 ሚሊዮን ብር የሚደርስ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሰባት ሀገር ላይ ተስፋ ጥለዋል፡፡*********************************************************************ይህ ጽሁፍ በዘገባ ሂደት በተሰራ ስህተት ምክንያት ታርሟል፡፡ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ስህተቶችን የማስተካከል/ የማረም ሙያዊ ግዴታ አለበት፡፡