ጥቅምት 28 ፣ 2011

የአዲስ አበባ የጅምላ እስር - የሕግ እይታ

ወቅታዊ ጉዳዮች

ስለ ጅምላ እስር (Mass Arrest) በጥቂቱመንግስታት በሰልፍ የሚካሄዱ ተቃዎሞዎችን ለመግታት የመጀመሪያው አማራጫቸው በሰልፎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ…

የአዲስ አበባ የጅምላ እስር - የሕግ እይታ
ስለ ጅምላ እስር (Mass Arrest) በጥቂቱመንግስታት በሰልፍ የሚካሄዱ ተቃዎሞዎችን ለመግታት የመጀመሪያው አማራጫቸው በሰልፎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸውን እና/ወይም ሰልፎችን የሚያደራጁ ግለሰቦችን ማሰር ነው፡፡ ዓላማውም የተቃውሞ ሰልፎች እንዳይደራጁ ለማዳከም እና የሌሎችን ተሳታፊነት ላለማበረታተት ነው፡፡ ነገር ግን ሰልፎችን በግልጽ የሚያደራጀው አካል በማይታወቅበትና መረጃም ለማግኘት ከባድ በሚሆንበት ጊዜ የጅምላ እስር እንደአማራጭ ይወሰዳል፡፡ የጅምላ እስሮች የሚወሰዱት የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በመክተት ሊሆን ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሰልፎች ከሚካሄዱባቸው ቦታዎች፣ የተቃውሞ መንፈስ አለባቸው ተብለው ከሚገመቱ ቦታዎች፣ በምርጫ ጊዜ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፊ ድምጽ ከተሰጠባቸው ቦታዎች ወይም እንደ እስሩ ምክንያት የተለዩ የማንነት መገለጫዎች ካለባቸው ቦታዎች የጅምላ እስር ሊካሄድ ይችላል፡፡ዋና ከተሞች እና የጅምላ እስርዋና ከተሞች ለጅምላ እስሮች በተለየ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ዋና ከተሞች የማእከላዊ መንግስቱ መቀመጫዎች በመሆናቸው ዋነኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ቦታዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በመንግስታት ላይ ለሚነሱ ማናቸውም አይነት የተደራጁ ጥያቄዎች ዋና ከተሞች ተመራጭ ናቸው፡፡ የመንግስት ተቋማትና ሕዝባዊ አደባባዮች በዋና ከተሞች ውስጥ ስለሚገኙ በሰልፍ የሚደረጉ ጥያቄዎች በፍጥነት ለመንግስታቱ እንዲደርሱ እና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሹም ይሆናል፡፡ መንግስታት በዋና ከተሞች ላይ ያላቸው ቁጥጥር የፖለቲካ ስልጣናቸው ቁጥጥርና መደላደል ዋነኛ መገለጫ በመሆናቸው መንግስታት የጅምላ እስር በማካሄድ ማንኛውንም አይነት ተቃውሞ ከመደራጀቱ በፊት ለማፈን ይጣጣራሉ፡፡አዲስ አበባም በተለያዩ ጊዜያት ለጅምላ እስር ተጋላጭ ሆና ኖራለች፡፡ በአምስት አመቱ የጣልያን ወረራ እና አገዛዝ ዘመን በየካቲት 1929 ዓ.ም. የጅምላ ጭፍጨፋም የተካሄደው እዚሁ አዲስ አበባ ነበር፡፡ በንጉሱ ጊዜ በ60ዎቹ የተፋፋመውን የተማሪዎች ንቅናቄ ለማፈን በአዲስ አበባ ላይ ሰፊ አፈሳ ተካሂዶ ነበር፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስትም በ60ዎቹ መጨረሻ እና በ70ዎቹ መጀመሪያ የከተማ አመጽንም ሆነ የበርሃ ጦርነት ተሳትፎን ለመግታት የታለመ ሰፊ የቤት ለቤት የጅምላ እስር ተካሄዷል፡፡ የቅርብ ታሪካችን በሆነው የ97 ምርጫ ማግስትም ሰፊ የጅምላ እስር በአዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ በፓርላማ የተቋቋመውና 11 አባላት የነበሩት አጣሪ ኮሚቴ ባወጣው ሪፖርት መሠረት 14,248 ወጣቶች ታፍሰው ከከተማው ውጪ በሚገኙ እስር ቤቶች እና የወታደር ማሰልጠኛ ካምፖች ውስጥ ታጉረው ነበር፡፡የዘፈቀደ እስር(Arbitrary Arrest) ምንነት? - የሕግ እይታዜጎች የነጻነት (በዘፈቀደ ያለ መታሰር) መብት እንዳላቸው በአለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ስምምነቶች እና የውስጥ ሀገራት ሕጎችም በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡የዘፈቀደ እስር ክልከላ የአለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ ደረጃ የተጎናጸፈ ሲሆን ሀገራት የአለም አቀፍ ስምምነቶች አባል መሆንም ሆነ በውስጥ ሕግጋታቸው ውስጥ ማካተት ሳይጠበቅባቸው የክልከላው ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ኢትዮጲያ አባል የሆነችባቸው የአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን(አንቀጽ 9) እና የሰው እና ሕዝቦች መብት የአፍሪካ ቻርተር (አንቀጽ 6) ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የኢፌድሪ ሕገ መንግስትም “ማንኛውም ሰው ከሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም” በሚል የዘፈቀደ እስር ክልከላን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡የዘፈቀደ እስርን የተጠቃለለ ትርጉም የምናገኘው በተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(Human Rights Commission) ስር የተመሰረተውና አምስት ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ስብስብ(Working Group on Arbitrary Arrest) በ1995 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት እና በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የተመሰረተውና የአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ድንጋጌዎችን ለመተርጎም የተቋቋመው የባለ 18 አባላቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ(Human Rights Committee) በ1997 ዓ.ም ላይ በሰጠው አስተያየት ቁጥር 35 ላይ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የዘፈቀደ እስር በአምስት ክፍሎች ተከፋፍሎ ተቀምጦአል - 1) ምንም አይነት የሕግ ድጋፍ ሳይኖር የሚደረግ እስር፣ 2) የአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን ላይ የተደነገጉትን፤ አንቀጽ 12 (የመዘዋወር መብት)፣ 18(የሀይማኖትና አመለካከት የመያዝ ነጻነት)፣ 19(ሀሳብን የመግለጽ መብት)፣ 21(የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት)፣ 22(የመደራጀት መብት)፣ 25(የመምረጥና የመመረጥ መብት)፣ 26(የእኩልነት መብት)፣ እና 27(የሕዝቦች እራስን የማስተዳደር መብት) ለመጨፍለቅ የተደረገ እስር፣ 3) በሙሉ ወይም በከፊል ተገቢ የሆኑ የፍርድ ሒደቶችን (due process) ሳይከተል የሚደረግ እስር፣ 4) የአስተዳደርያዊ ወይም የፍርድ ቤት አማራጭን የነፈገ የስደተኞች እስር እና 5) ከግለሰቡ የተለያዩ ማንነቶች(ከትውልድ ቦታ፣ ከብሔር፣ ከሀይማኖት፣ ከኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ከፖለቲካ አቋም፣ ከጾታ…)ጋር በተያያዘ የእኩልነት መርህን በተጣረሰና አድሎዋዊ አካሄድ የሚደረጉ እስሮች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ የጅምላ እስር እናየዘፈቀደ እስርየአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ ስለአዲስ አበባው የጅምላ እስር መግለጫ የሰጡት“…በሕጉ የሚያስጠይቃቸው በሁከቱ የተሳተፉ እና እንደ ዜጋ ቀጣይ ጥፋት ውስጥ እንዳይገቡ በተለያየ መልክ ሰብስበን ለሕንጸት በጊዜው ሠንዳፋ አካባቢ አቆይተን አሁን ግን አጣርተን ለሕንጸት ወደ ጦላይ የገቡ 1,204 ዜጎች እዛ ይገኛሉ” በሚል ነበር፡፡ የፓሊስ ስልጣን ወንጀሎችን የመከላከል፣ ወንጀል ተፈጽሟል ብሎ ሲያስብ ጉዳዩን አጣርቶ ክስ እንዲመሰረት ለዓቃቢ ሕግ የማሳወቅ፣ የፍርድ ቤት ትእዛዞችንና ውሳኔዎችንየመፈጸም እና የተለያዩ ተቋማትንና የመንግስት ኃላፊዎችን መጠበቅ ነው፡፡ ፓሊስ ግለሰቦችን በጅምላ አስሮ ስልጠና የሚሰጥበት የሕግ አካሄድ (ሥነሥርዓት) የለም፡፡ተገቢ የሆነ የፍርድ ሒደት (Due process of law) ባጠቃላይ፤ ግለሰቦች ብቁ፣ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ የፍርድ ተቋም ጉዳያቸው መታየት እንደሚገባው የሚያትት የሕግ ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ተገቢ የሆኑ የፍርድ ቤት ሒደቶች የተለያዩ መብቶችን ያካትታል - እስረኞች የተያዙበትን ምክንያት ወዲያው በሚገባቸው ቋንቋ የማወቅ፣ እስረኞች የተያዙበት ቦታ በሕብረተሰቡ፣ በተለየ በቅርብ ቤተሰቦች የመታወቅ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት የመቅረብና ከዚህ በላይ የሚቆይ እስር በፍርድ ቤት ብቻ የመወሰን፣ ሰብዓዊነት ባለው ሁኔታ የመያዝ፣ በቤተሰብ የመጠየቅ እና ወኪል የሕግ ባለሙያ የማግኘት መብቶች፡፡እስረኞች የተያዙበትን ምክንያት ወዲያው ማወቅ ያለባቸው እስሩ ምክንያታዊ ካልሆነ መቃወም እንዲችሉ ነው፡፡ ፓሊስ ለታሰረ ሰው የተጠረጠረበትን ድርጊት “ይህንን አድርገኻል፣ በዚህ ኩነት ውስጥ ተሳትፈሃል” ብሎ በግልጽ የማሳወቅ ግዴት አለበት፡፡ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው የጅምላ እስሩ ሰለባ የተያዘው በአውቶቢስ ተራ አካባቢ በእግሩ እየሄደ ሳለ መሆኑን ይናገራል፡፡ እንደ እስረኛው ገለጻ በፖሊስ ጣቢያም ሆነ ሰንዳፋ በነበሩበት ጊዜ ለመያዛቸው ይህ ነው የሚባል ምክንያት የነገራቸው አካል አልነበረም፡፡ነገር ግን እስረኞቹ በአዲስ አበባ ከተማ መውጫዎች ላይ ለደረሰው ጥቃት ተቃውሞና የፍትህ ጥሪ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መሳተፋቸው ለእስራቸው ምክንያት መሆኑን ጦላይ የወታደር ማሰልጠኛ በነበሩበት ወቅት እንደተነገራቸው የጅምላ እስሩ ሰለባ ይናገራል፡፡ በዚህም ምክንያት የጅምላ እስሩ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ለመጨፍለቅ የታለመ መሆኑን ያሳያል፡፡፡ ለአዲስ ዘይቤ ስለ እስሩ የሚያስረዳው ግለሰብ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያም፣ ሰንዳፋም ሆነ ጦላይ በነበረበት ጊዜ ቤተሰቦቹ የት እንደነበረ አያውቁም ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሰንዳፋም ሆነ ከሰንዳፋ ወደ ጦላይ የሄዱትበቅጥቅጥ መኪና ከለሌቱ 6 ሰዓት አካባቢ ተነስተው፣ ከህብረተሰቡ ድብቅ በሆነ ሁኔታ መሆኑን ይናገራል፡፡እስረኛ በ48 ሠዓት ውስጥ ወደ ፍ/ቤት መቅረብ የሚኖርበት በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ፍ/ቤት የእስረኞችን ተይዞ መቆየት ሕጋዊነት እና አስፈላጊነት አጣርቶ ለተጨማሪ ጊዜ እስሩ መቀጠል እንዳለበት ፍቃድ እንዲሰጥ ያስፈልጋል፡፡ እስረኞች የታሰሩበትን ምክንያት የመቃወም አጋጣሚም መስጠት ይገባል፡፡ እስረኞቹ በአግባቡ መያዛቸውንም በፍ/ቤት ቀርበው መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ የጅምላ እስረኞች ፍ/ቤት ሳያዩ ከወር በላይ በእስር ላይ እንዲቆዩ ሆኖአል፡፡ የአዲስ አበባ የጅምላ እስር ሰለባዎች የተቀመጡት ለማረፊያ ቤት በተዘጋጀ ቦታ ሳይሆን በወታደር ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ነው፡፡ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቸው ታሳሪ ወጣት የጦላይ ወታደሪያዊ ማሰልጠኛን “ቦታው ያስጠላል፣ ለማንም አልተመቸም” በሚል ይገልጸዋል፡፡ አክሎም የሚሰጣቸው ምግብ ዳቦ እና ሽሮ (በእስረኞች አገላለጽ ደያስ) የሚባለው ሲሆን “በጣም ያስጠላል፣ አይበላም” ይላል፡፡ የመታጠቢያው ውሃም በጣም ቆሻሻ እንደሆነ የሚገልጸው የጅምላ እስሩ ሰለባ፣ የሚጠጡት ውሃ የሚመጣው ግን በቦቴ እንደነበር ይናገራል፡፡ ጨምሮም የታሰሩበት ክፍል ሰፊ ክፍል ሲሆን በአንድ ክፍል ውስጥ 75 ሰዎች እንደነበሩም ይናገራል፡፡ በዚህምየእስረኞች በሰብዓዊነት የመያዝ መብት ተሸርሽሯል፡፡ የጦላይ ካምፕ ከአዲስ አበባ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ቤተሰብ በቅርበት እንዳይጠይቃቸው ምክንያት ሆኖአል፡፡የአዲስ አበባው የጅምላ እስር ወጣቱ በአዲስ አበባ መውጫዎች ላይ የተፈጠረውን ዘውግ ተኮር ግድያ እና ማፈናቀል ለመቃወም ሰልፍ ከመውጣቸው ጋር የተያያዘ በመሆኑ እስሩ ከፖለቲካ አቋማቸው ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የጅምላ ታሳሪዎቹ ወደ ሰንዳፋ ከመሄዳቸው በፊት የተለዩበት አካሄድ በሙያ ዘርፍ፣ የኢኮኖሚ አቅም ጋር የተያያዘ እንደነበር የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከል ኡማ እሰረኞቹ ማን እንደሆኑ ሲጠየቁ ይሄንን የሰራተኞችና ማህበራዊ ጉዳይ ዋስትና ያውቀዋል፣ ማን ስራ እንዳለው ማን እንደሌለው ተለይቶ ይታወቃል በሚል የሰጡት ምላሽ እስሩ የግለሰቦችን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ የከተተ፣ አድሎዋዊ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የጅምላ እስር የዘፈቀደ እስር (Arbitrary Arrest) መሆኑ የማያከራክር ኩነት ነው፡፡ ታዲያ የዘፈቀድ እስር ሰለባ የሆኑ አዲስ አቤዎች ምን መፍትሄ አላቸው?፣ የጅምላ እስር ዳግመኛ እንዳይደገምስ ምን ይደረግ?የመፍትሄ አቅጣጫ ለዘፈቀደ እስር ሰለባዎችየግለሰቦች የነጻነት መብት ሕገ መንግስታዊ እና የሰብዓዊ መብት ናቸው፡፡ ያለተገቢ የሕግ አካሄድ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይሆናል፡፡ ሕገ መንግስት የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማንኛውም የመንግስት መመሪያ ከሕገመንግስቱ ጋር ተቃርኖ ካለው ውጤት አይኖረውም፡፡ የአዲስ አበባው አፈሳ የተካሄደው በመንግስት ኃላፊዎች መመሪያ ነው፡፡ መመሪያዎች ከሕገመንግስቱ መጣጣማቸውን የማጣራት ስልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ወደፊት ተመሳሳይ መመሪያዎች እንዳይደገሙ ጉዳዩ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ዘልቆ ኢ-ሕገመግስታዊ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ የሕግ ባለሙያዎች፤ በግልም ሆነ በቡድን የአዲስ አበባ ጅምላ እስር ሰለባዎችን ወክለው ጉዳዩን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በመውሰድ የፍትህ አገልጋይነት የሙያ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ወንጀል የፈጸመን አካል/ግለሰብ መቅጣት በወንጀል ፈጻሚውም ሆነ በሌሎች አካላት ወንጀሉ ዳግመኛ እንዳይፈጸም ከማበረታታቱ (Deterrence effect) ባሻገር በወንጀሉ ጉዳት የደረሰበትንም ሰላም እንዲሰማውና ከወንጀለኛውም ጋር እንዲታረቅ (Restorative Justice) ምክንያት ይሆናል፡፡ የዘፈቀደ እስር ወንጀል ነው፡፡ የወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 423 “ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ በሕግ ከተመለከተው ውጪ ወይም ሕጋዊ ሥርዓትን ጥንቃቄ ሳይከተል ሌላውን ሰው በመያዝ፣ በማሠር ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኃን ነጻነቱን ያሳጣው እንደሆነ…“ ከ10 ዓመት በማይበልጥ እስራት እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ተጎጂው አቤቱታውን የሚያቀርበው ለፖሊስ ነው፡፡ በኢትዮጲያ የወንጀል የፍትህ ስርዓት ፓሊስ በራሱ ባልደረባ ላይ፣ በተለይ የአለቃውን ወንጀል መርመሮ ማስረጃ ማደራጀት እና ለዓቃቢ ሕግ የማስተላለፍ ገለልተኝነት የለውም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አስተዳደር በተቋማት ማሻሻል ስራው ሊጎበኘው ከሚገቡ ዋነኛ ተቋማት ውስጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አንዱ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች የቁሳዊ ወይም የሞራል ጉዳት ከደረሰባቸው ሊካሱ ይገባል፡፡ ይህ የካሳ አካሄድ ከውል-ውጪ ኃላፊነት ይባላል፡፡ በዘፈቀደ እስር ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ሊፈጸም የሚችል የካሳ መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ የአለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ ቃልኪዳን ይደነግጋል፡፡ ይህ ሀላፊነት በተቋም ወይም መመሪያውን ባስተላለፈው ሃላፊ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለሕግ አግባብ በተፈጠረ እስር ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ካሳ ስለሚከፈልበት አካሄድ ሕጋችን ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ የፍትሃ ብሔር ሕጋችን አንቀጽ 2042 በተዘዋዋሪ ይህን መብት ያካተተ ይመስላል፡፡ ወንጀል ሰርቷን ብሎ ያሰበ ሰው የሌለውን ነጻነት መንፈግ እንደሚችል አስቀምጦ “አስገድዶ ነጻነቱን የነካበት ሰው ወዲያውኑ ለክፍሉ ባለስልጣን ወስዶ ካላስረከበው በቀር በዚሁ ምክንያት ብቻ የሰውን ነጻነት በመንካት ኃላፊነት ያገኘዋል” በሚል ይደነግጋል፡፡ በዚህ አካሄድም ፖሊስ በ48 ሰዓት በጅምላ የታሰሩትንግለሰቦች ወደ ፍርድ ቤት ሳይወስዳቸውከወር በላይ በመቆየታቸው ለደረሰባቸው ጉዳት ሊካሱ ይገባል የሚል ትርጓሜ መስጠት ይቻላል፡፡ ለጉዳተኞቹየካሳ መፍትሔ ለመስጠጥ እና የዘፈቀደ እስርንም ላለማበረታታት ይህ የሕግ ድንጋጌ እስከጠቅላይ ፍ/ቤት ሔዶ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ቢሰጥበት ጥሩ ነው፡፡ የመንግስት እና የሲቪል ማህበራት ድርሻ መንግስት የሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ሶስት ኃላፊነቶች አለበት - የማክበር፣ የመጠበቅ እና የሟሟላት፡፡ “የማክበር” ግዴታ ስንል የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት ያለመጣስ፣ ጣልቃ ያለመግባት ግዴታ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ከዳግመኛ የዘፈቀ አስር መቆጠብ አለበት፡፡“የመጠበቅ” ግዴታ የግለሰቦች ሰብዓዊ መብት በሌሎች ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንዳይጣስ የመጠበቅ ኃላፊነትን የሚገልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ሶስቱም የመንግስት አካላት የዘፈቀደ እስር ሲካሄድ ዝምታን መምረጥ የለባቸውም፡፡ አስፈጻሚው ሲያጠፋ ፍ/ቤቶች እና ፓርላማው ማውገዝ፣ የመብት ጥሰቱንም የማስቆም ሕገ መንግስትዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡“የሟሟላት” ኃላፊነት መንግስት የሰብዓዊ መብትን ለመከላከል የሚጠቅም የተቋም እና የሕግ ማእቀፎችን ማኖር አለበት እንደማለት ነው፡፡ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ በአዲስ አበባ የጅምላ እስር መኖሩን አምነው ለዚህም ምክንያቱን ሲያብራሩ “ያለንን ሲስተም እናውቀዋለን ያለን ሲስተም አጥርቶ የመያዝ ብቃቱ የደከመ ብቻ ሳይሆን ልምምዱም አናሳ ስለሆነ ደምሮ የሆነ ሰዎችን ይዞ ሊሆን ይችላል […] በዚህ ሂደት ውስጥ የተጎዱ ወጣቶች፣ ካላአግባብ የታሰሩ ወጣቶች አስርም መቶም ሀምሳም ካሉ የለውጥ አካል አድርገው ማሰብ አለባቸው” በሚል ለዘፈቀደ እስሩ የተቋማትን ድክመትን እንደምክንያት አስቀምጠዋል፡፡ ለውጡ የተሳካ የሚሆነው ሕብረተሰቡን ሲያሳትፍ ነው፡፡ ለውጥ ዋነኛ ዓለማው የሕብረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ አመቺ የሆነ ተቋማዊ እና ሕጋዊ መዋቅሮችን ማጠናከር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን የሕብረተሰቡ ጥያቄ መታወቅ አለበት፡፡ ሕብረተሰቡ ጥያቄውን ከሚያቀርብባቸው አካሄዶች አንዱ ደግሞ የሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ሕብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲደራጀት እና ጥያቄውን በአደባባይ እንዲያቀርብ መፈቀድ አለበት፡፡ ይሄ ማለት በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ወንጀል ሊፈጸም አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም የተጠናከረና ብቁ የፖሊስ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ የፖሊስ ሰልፍ አያያዝ እራሱን የቻለ ውስብስብ ሙያ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን በማፈላለግ፣ እራሱን የቻለ በጀት ይዞ ፖሊሶች ስለ ሰልፍ አያያዝ ጥልቅ ስልጠና የሚያገኙበትን አጋጣሚ ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ለመብት የተቋቋሙ የሲቪል ማህበሮች በዘፈቀደ የሚደረጉ የጅምላ እስሮችን ወደ አለም አቀፍ ድርጅቶች ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ወደ ተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የአፍሪካ ሕብረት የሰው እና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን የማቅረብ ስልጣናቸውን በመጠቀም፤የዘፈቀደ እስር መኖሩን የሚያትት አቤቱታ በማቅረብ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ ወይም ወደ ተገቢው የፍርድ አካሄድ አቅጣጫ እንዲገቡ፣ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እና ዳግመኛም የዘፈቀደ እስር እንዳይፈጸም የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ በመንግስት ላይ ግፊት እንዲያደረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አስተያየት