ኅዳር 4 ፣ 2011

ብርቱ

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

Brilliant, charismatic, thoughtful, dignified, courageous, public-spirited....I always run out of…

ብርቱ
ላመነችበትን እና ለቃሏ ብዙ ርቀት የተጓዘች እጅግ ብርቱ ሴት ናት፡፡ የመርህ ሰውነቷ፣ የፀናና የማይለዋወጥ አቋሟ፣የመሪነት ችሎታና መስዕቧ ምሣሌ ፖለቲከኛ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት መመለሷን አስመልክቶ የአዲስ ዘይቤ ጸሐፊዎች የሆኑት ዳዊት ተስፋዬ እና አቤል ዋበላ የብርቱካን ሚደቅሳን ከባድ ጉዞ እንዲህ ዘግበውታል፡፡ቃሏ“ታህሳስ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. የፌደራል ፖሊስ......ተገኝቼ የተጠራኹት ከይቅርታው ጋር በተያያዘ መሆኑ ሲነገረኝ መጀመሪያ የጠይኩት ጥያቄ “ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሥልጣን አለው?” የሚል ነበር። ምላሾቹ ግን በመነደቅ ፈገግታ የታጀበ “ይሄ እኮ የአካዳሚ ውይይት አይደለም፤ እንዲህ አይነቱን ጥያቄ ብትተይ ይሻላል” የሚል ነበር።”ከላይ የቀረበውን “ቃሌ” በተሰኘ ርዕስ የቀረበ ጽሑፍ ያሰፈረችው፣ሐሙስ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው እና የነጻነት ትግል ተምሳሌት ተደርጋ የምትቆጠረው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። ብርቱካን ይህንን ያለችው በስዊድን ሀገር የተናገረችውን ንግግር እንድታስተባብል አለበለዚያ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ የተፈረደባት ዕድሜ ልክ እስራት እንደሚጸናባት የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በቀረበላት ጊዜ ነበር።“ቃሌ”ና ተያያዥ ጉዳዮቹ በብርቱካን የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ፋይዳ ላይ ደርሶ መመላለሻ አደባባይ የሆነ፣ የቅርብ እሩቅ፣ የሩቅም ቅርብ የሆነ፣ከአንድ የጋዜጣ ፅሁፍ በላይም የሆነ የብርቱካን ድርሳን አንቀፅ ነው። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፍትሕ ጉዳዮች ዙሪያ ስመ-ገናና በመሆን፣እንደመልካም ሽቶ የሚያውድ ስምና ምግባር በመያዝ፣ ትውልድ ተሻጋሪ ዝናን የያዘችው ብርቱካን ሚደቅሳ ደሜ ማን ናት?የፈረንሳይ ሽቶብርቱካን ተወልዳ ያደገችው ሰሜን-ምዕራብ አዲስ አበባ በሚገኘው፣ ጉራራ ተራራን እና የፈረንሳይን ቆንፅላ ጽ/ቤት በሚታከከው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ሰፈር ነው። ብርቱካን እና ፈረንሳይ ለጋሲዮን በፀባይ ይመሳሰላሉ።የፈረንሳይ ልጆች በ27 ዓመታቱ አስከፊና መራር ትግል ውስጥ በአልሸነፍ ባይነታቸው ስመ-ጥር የሆኑ ናቸው። ፈረንሳይ ሲባል ትግል እና እምቢ ባይነት አብሮ ይነሳል። ብርቱካንን በቅርብ የሚያውቋት በዚህ ባሕሪ ከፈርሰንሳይ ልጆች አንዷ እንደሆነች ይገልፃሉ።ብርቱካን ፈረንሳይን፣ ፈረንሳይም ብርቱካንን ትወዳለች። የመጀመሪያ እስሯን አገባዳ ስትወጣ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ነዋሪዎች ገንዘብ ከዚያው ከፈረንሳይ ገንዘብ አሰባስበው መኪና ሸልመዋታል። “እኔ ፈረንሳይ ነኝ ፈረንሳይ ለእኔ መኖሪያ መንደር ብቻ አይደለም። የመተባበር፣ ራስን መስዋዕት የማድረግ፣ የመታገል መንፈስ ነው” ብላለች ያኔ።አብሮ አደጎቿና ቤተሰቦቿ ብርቱካንን ሚሚ እያሉ ነው የሚጠሯት። እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ ስሟ ቤተልሔም የነበረ ሲሆን አባቷ አስር አለቃ ሚደቅሳ ደሜ “ብሩቱካን ነሽ” ብለው ስሟን ወደ ብርቱካን አስቀይረውታል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም የተማረችው ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው ሚያዚያ 27 (ድሮ ሚሽን ተብሎ የሚጠራው) ት/ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በየካቲት 12 መነን ት/ቤት ነው የተማረችው። ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በህግ ከፈረንሳይ በቅርብ በሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ስድስት ኪሎ ግቢ ነው የጨረሰችው። የብርቱካን በማኀበረሰባዊ አገልግሎት የመሳተፍ ዱብ ዱብ መታየት የጀመረው ስድስት ኪሎ ግቢየህግ ትምህርት ቤት ሳለች ነው። በግቢው ውስጥ ብዙ ወዳጆች ነበሯት። ግቢው ውስጥ የሚደረጉ ትምህርታዊና ትምህርታዊ ያልሆኑ የተማሪ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር እና ከተማሪዎች ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠር ትታወቅ ነበር። በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን የተማሪዎች ማኀበር ውስጥም ጉልህ ድርሻ የነበራት ሲሆን ግጥም ጽፋ ታቀርብም ነበር።ነብዩ ባዘዘው በትሬዠሪ ክፈል ውስጥ የባንክ ሰራተኛ ሲሆን በተለምዶ “ፈረንሳይ” እየተባለ የሚጠራው የፈረንሳይ ለጋሲዮን ሰፈር ነዋሪ ነው። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት አባልነት በግሏ ከተወዳደረችበት 1992 ዓ.ም ጀምሮ ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ይተዋወቃሉ። ለምርጫ 92 እራሷን ለማስተዋወቅ ስትሯሯጥ አብረው ዞረዋል፤ የምረጡኝ ዘመቻ በራሪ ወረቀቶች አብረው አድለዋል። ማንነቷ የተገለፀበትን “ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የሕግ ባለሙያ፤ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ” የሚል የማስታወቂያ ወረቀት እየተዟዟሩ ለጥፈዋል።“ከብርቱካን ጋር የምንተዋወቀው በሰፈር ልጅነት ሆኖ፣ በተለይ በደንብ የተዋወቅነው ምርጫ 92 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ስትወስን ሕዝቡን ለማግኘትና ራሷንም ለማስተዋወቅ በምትጥረበት ጊዜ ነው” ይላል። በጊዜው የፖሊስ ግምገማ በየሦሥት ወሩ ይካሄድ እንደነበር የሚያስታውሰው ነብዩ “በየሦሥት ወሩ በሚደረገው ስብሰባ ላይ በደል የፈፀሙ ፖሊሶች፣ ያለአግባብ የደበደቡ፣ ጉቦ የተቀበሉ፣ ሰብአዊ መብት የጣሱ ፖሊሶች ሲኖሩ እየተገኝን በማስረጃ እንከራከር ነበር። በስብሰባዎቹ ላይ በጣም በተደራጀ መልኩ ብዙ እየሆንን ነበር የምንገኘው። ብርቱካን ለመጀመሪያ ጊዜ እዚያ ስበስባ ላይ መጣችና በድንገት ተነስታ በሕግ ጥላ ስር ያለ ሰው መደብደብ እንደሌለበት፣ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በሚያውልበት ጊዜ ክብራቸውን ሳያዋርድ ሕጉን ተከትሎ በአግባቡ መያዝ እንዳለበት፣ ከዚያ ውጪ የሚፈፀሙ ድርጊችና እንገልቶች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ ተናገረች። አብዛኛው የሰፈር ሰው ያወቃት፣ የሕግ ባለሙያ መሆኗንም የተረዳው የዛን ለታ ነው።” ነብዩ በጊዜው ሴትነቷና ድፍረቷ አስገርሟቸውም፣ አስደስቷቸውም እንደነበር በፈገግታ ያወሳል። በዚያ ስብሰባ ላይ የፖሊስ አባል በሆነ የህግ ተማሪ ንግግሯ በተሳሳተ መንገድ ስለተጠቀሰ በተፈጠረ አለመግባባት ብርቱካን ድጋሚ የመናገር ዕድሉን ስትነፈግ ጥለው ወጡ። ስብሰባውን ጥለው የወጡት ነብዩን ጨምሮ በርካታ የሰፈሩ ወጣቶች ብዙ ሳይርቁ ተከትለው ደርሰውባ አናገሯት። ብርቱካን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በግሏ ለመወዳደር መወሰኗን ገለፀችላቸው። እነነብዩም እንደሚደግፏት ከመናገር አልፈው ለመወዳደር የሚያስፈልጋትን የአንድ ሺህ ሰው የድጋፍ ፊርማም በአጭር ጊዜ ውስጥ አሰባሰቡ።ዳኛ ብርቱካንዳኝነት እና ብርቱካን የተገናኙት በሦስተኛ ወንጀል ችሎት ነው። ብርቱካን ከሌሎች ወጣት ዳኞች ጋር በመሆን በትምህርት ቤት የተማሩት ነገር ግን በልማድ በፍርድ ቤቶች የማይተገበሩ ስነ ሥርዓቶችን ለማስተካከል ቁርጠኞች ነበሩ። ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን እንደፈለገ በማሰር የፈለገውን የቀነ ቀጠሮ ጊዜ የመውሰድ ልማድ ነበረው። ብርቱካን ህጉ ከሚፈቅደው የመጀመሪያአስራ አራት ቀን በላይ እንደማትሰጥ ስለሚታወቅ ፖሊስ ስራዬን ማከናወን አልቻልኩም በማለት አቤቱታ ያሰማ እንደነበር በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ ቅርበት የነበራቸው ሰዎች ይናገራሉ። ከብርቱካን ጋር ከዩንቨርሲቲ ጀምሮ የሚተዋወቀው የአዲስ ነገር ጋዜጣ መስራች እና የህግ ባለሙያው ዐቢይ ተክለማርያም ይህንን በቅርብ ካስተዋሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው። ዐቢይ በወቅቱ አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረ ሲሆን፣ አንድ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ባመቻቸውና ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በተግባር የፍትሕ ስርዓቱን እንዲያውቁ ማስቻልን ዓላማው ያደረገ መርሐ ግብር ውስጥ ተሳታፊ ነበር። በወቅቱ ዐቢይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኞች ረዳትነት ቢመደብም ጓደኞች ለማግኘት ወደ እነ ብርቱካን ችሎት ይመጣ ነበር። በዚህ ወቅት በየኒቨርሲቲ የነበራቸው ትውውቅ እንደጠነከረ እና ወደ ጓደኝነት እንዳደገ ይናገራል። ዐቢይ በወቅቱ ብርቱካን የፍርድ ስርዓቱን በማዘመን እና ተጠርጣሪዎች መብታቸው እንዳይጣስ ዘብ በመቆም የነበራት ተጽእኖ ከፍርድ ቤቱ ቅጽር በመሻገር ማኀበረሰቡ ዘንድ የሚደረስ እንደነበር ይናገራል። “ባንድ ወቅት ኳስ እየተጫወትን ካደገን አብሮ አደጌ ጋር ቁጭ ብለን እያለ ብርቱካን ስታልፍ አየናት። እኔ እንደማላውቃት የገመተው ወደጄ ‘አየሃት! ያቺ ልጅ እኮ ምርጥ ዳኛ ናት’ ብሎ የነገረኝ ሁሌ ይገርመኛል።”ብርቱካን እና ሌሎች ዳኞችን እንዲከበሩ ያደረጋቸው እና ፖሊስን ያላስደሰተው የተጠርጣሪዎች በሕግ ፊት እንደ ነጻ የመቆጠር መብት(presumption of innocence) ነው። በፊት በነበረው ልማድ ከፖሊስ ጣቢያ እና ከማረሚያ ቤት ፍርደኞች እና ተጠርጣሪዎችን ይዘው የሚመጡ ፖሊሶች መሣሪያቸውን እንደያዙ በችሎቱ ከፊት ይቀመጡ ነበር፤ብርቱካን ግን ይህ የተጠርጣሪዎችን መብት የሚያጣብብ እና የፍትህ ሚዛናዊነት ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥር ነው በማለት ፖሊሶች መሳሪያ ይዘው ወደችሎት እንዳይገቡ አግዳለች።ብርቱካን ይህንን መብታቸው እንዲጠበቅ ከምታደርገው ጥረት በዘለለ ከፍ ያለ ሀዘኔታ ለእሰረኞች እና ለባለጉዳዮች ታሳይ ነበር። በዚህ ምክንያት በፍርድ ቤት ውስጥ ‘ማዘር ቴሬዛ’ የሚል ቅጽል ስም እንደወጣላት ይነገራል።ዐቢይ ከዪኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በእንግሊዘኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ከሕግ እና ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚጽፍበት ወቅት ከብርቱካን ጋር ወዳጅነታቸው ይበልጥ እንደጠነከረ ይናገራል። “የብርቱካን የማኀበረሰብ አገልጋይነት መንፈስ እጅግ የጠነከረ መሆኑን የተረዳኹት ምርጫ መወዳደር እንደምትፈል በነገረችኝ ጊዜ ነው” ይላል ዐቢይ። ብርቱካን በ1992 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግሏ ተወዳድራ ነበር። በዚህ ምርጫ እንድትሳተፍ መግፍዔ የሆናት በወቅቱ እጅግ ተስፋፍቶ የነበረው ሙስና እና የሞራል መላሸቅ እንደሆነ ዐቢይ ያስታውሳል። ይህ “የኋላ የኋላ ዋጋ ያስከፍለናል” እያለች ትስጋ እንደነበር ያስታውሳል። ለዐቢይ ሌላው ያስገረመው ነገር ብርቱካን ከገዢው ፓርቲ ተወካይ እና ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካ ተሳትፎ ከሚታወቁትና ሰፊ ድጋፍ ከነበራቸው ሻለቃ አድማሴ ጋር በአንድ ምርጫ ክልል መፎካከሯ ነው። ምንም እንኳን በምርጫው ብትሸነፍም ከዚያ በኋላ የማኀበረሰቡን እና የሚዲያ ትኩረት በመሳብ ተራራ ላይ እንደተሰራች ከተማ መሰወር የማይቻላት ሆነች።ብርቱካንና የስዬ ሕግየሀገሪቱ የፍትህ ስርዓትን እንደመጠቀሚያ የማየት ዝንባሌ በነበረበት በዚያን ወቅት በሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ነበር። የሕወሃት እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር በሆኑት በአቶ መለስ ዜናዊ እና በሌሎቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል የነበረውን ቁርሾ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት የጀመረ ቢሆንም ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር። መለስ ዜናዊ ባለጋራዎቻቸውን በ“ቦናፓርቲዝም” በመወንጀል በወሰዱት እርምጃ የኤፈርት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሓ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ወህኒ ወረዱ። አቶ ስዬ አብርሓ የተወነጀሉት ስልጣናቸውን በመጠቀም የኢትጵያ ንግድ ባንክ ለወንድማቸው ምህረተአብ አብርሓ ብድር እንዲሰጥ ተጽእኖ በማሳደር፣ እና  በከፊል የመንግሥት ከሆነው መኪና መገጣጠሚያ “አምቼ” በቅናሽ እንዲገዙ በማድረግ ነበር።በወቅቱ ክስ ሳይመሰረትባቸው ፖሊስ ጥርጥሬያቸዋለኹ ብሎ ፍርድ ቤት ሲያቀርባቸው በሕጉ መሰረት ውሳኔ መስጠት ለዳኞች ፈታኝ ነበር። ብርቱካን ግን ተጠርጣሪውን በማረሚያ ቤት የሚያቆይ በቂ ማስረጃ አልቀረበም በማለት የዋስትና መብታቸውን እንዲከበርላቸው ወሰነች። ምንም እንኳን ተጠርጣሪው ከፍርድ ቤቱ ቅጽር ከወጡ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውሉም ይህ በኢትዮጵያ ፍትህ እና የዳኝነት ስርዓት ተጠቃሽ ውሳኔ ሆኖ ይቆጠራል። የሕግ ባለሙያው ዳንኤል አረጋዊ ይህንን የፍርድ ሂደት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ያስታውሰዋል። ውሳኔው በሀገሪቱ የፍርድ ስርኣት ውስጥ ተጠቃሽ ወሳኔ እንደሆ ያምናል። “ብዙውን ጊዜ ዳኞች እንዲህ ወስኑ የሚል ትዕዛዝ ሳይመጣላቸው ነው ራሳቸውን ሳንሱር በማድረግ (Self censorship) ነው የሚወስኑት፤ እንደብርቱካንዓይነት ውሳኔዎች የሉም ባይባሉም እስካሁን ድረስ እንኳን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው” በማለት የብርቱካንን ቁርጠኝነት ያደንቃል።የብርቱካን ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ፍርድ ግን ስዬን መልሶ ለማሰርና “የስዬ ሕግ” የሚል ቅፅል ስያሜ የወጣለትን ለሙስና ወንጀል ዋስ የሚከለክለውን ሕግ ወልዶ አልፏል።አቶ ስዬ አብርሓም በሀገሪቱ መማረራቸውን ለማጠየቅ ከእስር ቤት ሲወጡ‘ነፃነትና ዳኝነት በኢትዮጵያ’ የሚል መጽሐፍ የፃፉ ሲሆን ለፎርቹን አዲስ ጋዜጣ ሰጡት ቃለመጠይቅ ለብርቱካን ያላቸውን አድናቆት ሳይገልጹ አላለፉም።የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በቶሎ ፈቃድ አውጥተው ወደ ጠበቃነት ሲሸጋገሩ ማኀበረሰቡን ማገልገል መርጣ በፍርድ ቤት የቆየችው ብርቱካንከዚያ በኋላ ግን እዚያ መቆየት አልወደደችም። በግሏ ፈቃድ በማውጣት አብዛኛውን ጊዜ የነጻ ማመከር አገልግሎት በመስጠት ታሳልፍ እንደነበር ዐቢይ ተክለማርያም ያስታውሳል።ምርጫ 97 እና የቅንጅት መንፈስበዚህ ሂደት ነበር ብርቱካን አንድ ልጇን መውለዷ እና የምርጫ ዘጠና ሰባት ትኩሳት አብረው ብቅ ያሉት። ምርጫው ሊካሄድ ሁለት ወራት ሲቀሩት ወደሀገር ቤት የተመለሱት የአሁኑ የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በወቅቱለቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ የተለያዩ ወጣቶች እና ሙያተኞችን በትንንሽ ቡድን እየሰበሰቡ ያወያዩ ነበር። ብርቱካን በእነዚህ ቡድኖች ተሳትፎ ታደርግ ነበር። በሂደት ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ቅንጅት የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል ብሎ በማመኑ የሕግ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ጥረት ያደርግ ነበር። በዚህ ሂደት የነበራት ተሳትፎ ብርቱካንን ወደፊት አመጣት። በአጭር ጊዜ ውስጥም የቀስተ ደመና ለዴሞክራሲ እና ማኀበራዊ ፍትህ ንቅናቄ አባል በመሆን ፓርቲዎቹ ተዋህደው ቅንጅቱንእንደ ፓርቲ ሲመሰረቱ ደግሞ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች። ይህም ከቅንጅቱ አንጋፋ መሪዎች ተርታ እንድትሰለፍ አደረጋት።ብርቱካን በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስትገልጽ “ቅንጀት መንፈስ” ነው ብላ ነበር። ብርቱካን በእስር ላይ ሳለችና ከዚያም በፊት ስለብርቱካን ፅናትና የሞራል ልዕልና ደጋግመው በመፃፍና በመናገር የሚታወቁት የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አስፋ (ፒ.ኤች.ዲ) ግን “መንፈስ በበጎ ነገር ከተተረጎመ በእርግጥኝነት ዋናዋ መንፈስ ብርቱካን ሚደቅሳ ናት” ብለው ያምናሉ።የቅንጅት መሪዎች በእስር ላይ እያሉ ብርቱካን የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብን ትኩረት እንደሳበች የሚናገሩ አሉ። ዐቢይ ተክለማርያም “why has Ethiopia’s regime locked Birtukan in jail?”የሚል ርዕስ ባለውረጅም ጽሑፍ ይህ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ዘንድ ትኩረት ማግኘቷ በ2001 ዓ.ም. ወርሃ ታኅሳስ ለተፈጸመው ዳግም እስሯ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይናገራል።ቪቫ ብርቱካንብርቱካን ከምርጫ 97 በኋላ ከሌሎች የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራሮች ጋር ለሁለት ዓመታት ታስራ ስትፈታ የሰፈሯ የፈረንሳይ ነዋሪዎች አዋጥተው መኪና ሲሸልሟት ሂደቱም ዕለቱም ከብዙ የዝነኛ ሰዎች ሽልማት የሚለይ ነበር። ብርቱካን መኪና የተሸለመችው ባለሀብቶች ድጋፍ አድርገው አልነበረም፤ ወይም ጥቂት ሰዎች በዛ ያለውን ገንዘብ ሸፍነው አልነበረም። ከእስር ስትፈታ ተወልዳ ባደገችበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ምን እናድርግ ብለው የመከሩት የሰፈሯ ልጆች መኪና ገዝተው ለመሸለም ቆርጠው አስር አስር ብር የሚሸጥ ካርድ አዘጋጁ። የፈረንሳይ ነዋሪዎች “ብርቱካን ሚደቅሳ” የሚል ማህተም የተመታበትን በሺህ የሚቆጠሩትን ካርዶች በነብስ ወከፍ ድምፅ እንደመስጠት ገዝተው በጥቂት ቀናት ውስጥ ተሰብስቦ፣ ተገዝቶ መኪና ሊሸልሟት ችለዋል። መኪናው ላይ ሆና የአበባ ጉንጉን አንገቷ ላይ አድርጋ፣ የጥበብ ልብስ ለብሳ፣ በፈገግታ ተሞልታ፣ በጣቶቿ የድል ምልክት (V) እያሳየች የተነሳቸው ዝነኛ የፎቶግራፍ ምስል የዛ ሽልማት ቀን የተነሳ ነው።ሌላ ፓርቲ፣ ሌላ ትግልብርቱካን ከእስርናእንግልት በኋላም ቢሆን ስደትን ወይም እጅ እና እግርን አጣጥፎ መቀመጥን አልመረጠችም። የሁለት ዓመታት እስርን አሳልፋ በ2000 ዓ.ም ዋዜማ ከተፈታች በኋላ አንድ አመት ሳይሞላት ከአንድነት ፓርቲ መስራቾች አንዷ በመሆን ወደ ፖለቲካ ትግል ተመለሰች። የፓርቲው ሕጋዊ ስምን ምርጫ ቦርድ በአቶ አየለ ጫሚሶ ለሚመራው ቡድን ሲሰጥ ሌሎቹ የፓርቲው የቀድሞ አባላት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይወያዩ እንደነበር የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባል ዳንኤል ሺበሺ ይናገራል። በውይይቱ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም አስፈላጊ ነው አይደለም፣ ሰላማዊ ትግል ያዋጣል ወይስ አያዋጣም የሚሉ የጦፉ ክርክሮች በተለያዩ ስፍራዎች ይካሄዱ ነበር።በወቅቱ ብርሃኑ ነጋ(ፒ.ኤች.ዲ) ከሀገር ቤት በመውጣት ድርጅት ለመመስረት ዝግጅት እያደርጉ ነበር። የቅንጅቱ መፍረስን ተከትሎ አንጋፋዎቹ መሪዎች አቶ ኃይሉ ሻውል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን(መኢአድ)፣ አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዴሞክሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓ) ይዘው ተቃዋሚው በትግል ስልት እና በጎራ ተለያይቶ የሚፋጭበት አስቸጋሪ ወቅት እንደነበር ይናገራሉ። መንግስትም የዘጠና ሰባት ዓይነት የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዳግም እንዳይፈጠር ተግቶ ይሰራ እንደነበር ሚስጥር አልነበረም።ብርቱካን በሀገር ቤት እና በባህር ማዶ ያላትን ተጽእኖ በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሰዎችን በማሰባሰብ አንድነት ለፍትህ እና ዴሞክራሲን መሰረተች። በወቅቱ ፓርቲው ከመሰረታቸው አምስት ሀገር አቀፍ ቀጠናዎች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ቀጠና ኃላፊ የነበረው ዳንኤል ሺበሺ፣የመስራች አባላት ፊርማ ከማሰባበሰብ አንሰቶ ሁሉንም የማስተባበር ስራዎች የፋይናስ ምንጮችን መፈለግ፣ ዓለም አቀፉን ማኀበረሰብ ስለ ፓርቲው ዓላማ ማስረዳት በግንባር ቀደምነት ትስራ እንደነበር ይናገራል። በሴትነቷ እነ በብርቱ ታጋይነቷ ብዙዎች ከብርቱካን ጋር የሚያነሷት የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ፣ ጋዜጠኛና ፀሐፊዋ ርዕዮት ዓለሙ ከብርቱካን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ያገኘኋት የቀድሞ የህወሓት ታጋይ የማርውሃ አጽብሀ (የአቶ ገብሩ አስራት ባለቤት) በራሳቸውና በሌሎች የህወሓት ሴቶች ዙሪያ የጻፉትን መፅሐፍ ባስመረቁበት ዝግጅት ላይ ሁለታችንም ታድመን ነበር፤ ተደራጅቶ ሥርዓቱን መታገል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በመወሰኔ እሷ የምትመራው አንድነት ስለመግባት ያለኝን ሀሳብ አጫወትኳት” ብላ ለአዲስ ዘይቤ የነገረችን ርዕዮት በወቅቱ ብርቱካን ያለቻትን ቃል ቃል ታስታውሳለች፡“አንቺን የመሰለች ያንግ ሌዲ አግኝተን ነው እንዴ!” አቀራረቧ፣ ሀሳቧ፣ በአጠቃላይ ሁሉ ነገሯ ማራኪ ነበር። ሃሳብ ተለዋወጥንና የፓርቲውን ስልክ ቁጥር ሰጥታኝ ተለያየን። ወዲያው ወደ ስዊድን ሄደች። ለመታሰሯ ሰበብ የሆነውን ንግግር ያደረገችው ያኔ ነበር።”ዐቢይ ተክማርያም በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ፓርቲውን ማቋቋሟ የበለጠ እንዲያከብራት ቢያደርገውም ይህ በገዢው ፓርቲ በተለይም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘንድ በበጎ አለመታየቱ የሚያመጣው አደጋ ይታየው ነበር። ይህንን ስጋቱን ለወዳጁ ብርቱካን ሚደቅሳ ቢያደርሳትም እርሷ በፓርቲዋ እንቅስቃሴዎች በመዋጥ ትኩረት ልትሰጠው አልፈቀደችም። በ2001 ዓ.ም በስዊድን ሀገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ‘የሽምግልናው መሰረታዊ መንፈስ፣ ሁለቱንም የሚያግባባ ስምምነት አምጥቶ እና የዕርቅን መንፈስ ፈጥሮ የፖለቲካ ሂደቱን ማስቀጠል ነበር።’ በማለት መናገሯ ሊቀመንበሯን ለማጥቃት ምክንያት ሲፈልግ ለነበረው መንግሥት የተደረገላትን ይቅርታ አስተባብላለች በሚል ምክንያት እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል።በዚህ ላይ የብርቱካን የሞራል ልዕልና ሲጨመርበት የተመቻቸ ዒላማ ውስጥ እንዳስገባት መረዳት ይቻላል። በስዊድን ሀገር ያደረገችው ጉዞ በብርቱካን ላይ ድጋሚ እስርን ለማምጣት መንስኤ ይሆናል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። ወደ ሀገሯ ስትመለስ መንግስት ንግግሯን እንድታስባብል፣ ካላስተባበለች ግን መልሶ እንደሚያስራት አሳወቀ።በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት እና የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ታህሳስ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ቢሯቸው ጠርተው ማስተባበያ እንድትሰጥ ማስጠንቀቂያ ሲሰጧት ነገሩ የማይመለስ ደረጃ እንደደረሰ መገመት አያዳግትም ነበር። በሀገር ቤት የነበረው ዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብም ከሀገር እንድትወጣ መንግሥት ቢፈቅድም ብርቱካን ማስተባበሉንም ሆነ ሀገርን ጥሎ መሄዱን እንዳልመረጠችተሰምቶ ነበር። ውዝግቡ ከርሮ ብርቱካንም በሃሳቧ ፀንታ ከመታሰሯ በፊት በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ስለተፈቱበት የሽምግልና ሂደት፣ ስለሽምግልናው ሕጋዊና ሞራላዊ ባህሪ፣ ስለራሷ ዕምነትና አቋም የገለፀችበት “ቃሌ” በሚል ርዕስ የፃፈችው የማይረሳ ፅሁፍ ታትሞ ወጣ። በፅሁፉ “ታህሳስ 1 ቀን 2001 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ የወረዳ 12 ፖሊስ አባላት የሆኑ ሁለት ፖሊሶችን ቤቴ በመላክ ቢሯቸው ድረስ እንድመጣ ሲጠሩኝ ስለ ፓርቲያችን ስለአንድነት ለመወያየት ሊሆን ይችላል በሚል በፅ/ቤታቸው ተገኝቼ” ነበር ብላ ገልፃለች። ግምቷ ልክ አልነበረም። ማስጠንቀቂያ፣ ዛቻ፣ ከዚያ እስር ተከተለ።ዳግም እስር፣ ያውም የብቻ እስር( solitary confinement)ዐቢይ ተክለማርያም በጊዜው የነበረውን ተስፋ መቁረጥ እና የፍርሃት ድባብ ያስታውሳል። ወዳጃችን በርቺ ለማለት ቀርቶ እናቷ እና ልጇ እንኳን እንዲጎበኟት የተፈቀደው ዘግይቶ ነው። ቴሌቪዥን ማየት ጋዜጦችን መከታተል አልቻለችም። አቶ ሽመልስ ከማል በመንግስት ሚዲያዎች ቀርበው ‘የእርሷን ጥሩ ብታነሱ ውርድ ከራሴ’ዓይነት መልዕክት ያለው ንግግር ተናገሩ። መንግሥት የተግባቦት ዳሠሳ ጥናቶች እየደረገ ህብረተሰቡ ስለ ብርቱካን ያለውን አመለካከት እየገመገመ ለመልስ እራሱን ያዘጋጅ እንደነበር የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት በክልሎች ለሚገኙ የማስታወቂያ ቢሮዎች የሰጠውን ትዕዛዝ አዲስ ነገር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሟቹ መለስ ዜናዊ ከታሰረች በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ስለብርቱካን እንዲህ አሉ፡ “ምሕረት አልጠየቅኩም ብለው ሽማግሌ ቢላክ፣ አምባሳደር ቢላክ፣ “አልስማማም፣ አልቀይርም፣ በውጭ ሄጄ የተናገርኩትን አልክድም፣ አልቀይርም” ብለው ያሉት ደጋፊዎቻቸው በሚፈጥሩት ብጥብጥ ወይ በውጪ ኃይሎች ጫና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእስር ወጣለሁ የሚል ጠንካራ አቋም ስለነበራቸው ነው። በወቅቱ ግን በተደጋጋሚ ተነግሯቸዋል። ስህተት እንደሆነ፤ ከገቡ እንደማይወጡ።”ብርቱካን ለዳግም እስር ስተዳረግ ፓርቲዋ እና ሌሎች ሰዎች ካደረጓቸው እንቅስቃሴዎች በቀር በአብዛኛው ፍርሃት የነገሰበት ጊዜ ነበር። በ2001 ዓ.ም በድጋሚ ስትታሰር እሷን ለማሰብ በአንድነት ፓርቲ ግቢ ውስጥ በየወሩ በሚዘጋጀው የሻማ ማብራት ዝግጅት ላይ ብዙ ሰዎች ይገኙ እንደነበርና አብዛኛዎቹ ሰዎች የፈረንሳይ ለጋሲዮን ልጆች እንደነበሩ ነብዩ ባዘዘው ይናገራል። ብርቱካን መስራች የሆነችበት አንድነት ፓርቲ መድረክን ለመቀላቀል ሲደራደር፤ ከዚያም እሷ እስር ቤት እያለች በ2002 ምርጫ ሲሳተፍ የፈረንሳይ ነዋሪዎች በጣም አኩርፈው እንደነበርም ያስታውሳል። ስለብርቱካን ሁለተኛ እስር ሲያወራ በትካዜ ተውጦ ስለነበረው ድብታ፣ ሀዘንና፣ ንዴት የሚገልፅበት ቃላት ለመፈለግ ወሬው ይቆራረጣል። “የደረሰባትን ጉዳት እንረዳለን፤ ይሄ ነው ብለን ልንለው የማንችለው ጉዳት እንደደረሰባትም እንገነዘባለን።”ብርቱካን በእስር ላይ እያለች በርካታ ፅሁፎችን ስለእሷ ትፅፍ የነበረችው ርዕዮት “የመጀመሪያው እስሯ እንደሌሎቹ የቅንጅት መሪዎች እስር ሁሉ ቢያናድደኝም በተለየ መልኩ ስለብርቱካን መጨነቅ የጀመርኩት ግን ብቻዋን በታሰረች ጊዜ ነበር። የይቅርታውን ሂደት ያብራራችበት “ቃሌ” የተሰኘው ፅሁፏም ለሷ ያለኝን ክብር የጨመረ ነበር” ትላለች።ዶ/ር ዳኛቸው“ብርቱካን እና የሁለት እስረኞች ወግ” በሚል ርዕስ በአዲስ ነገር ጋዜጣ ያስነበቡት አንድ ጽሑፍ መጠነኛ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር። መምህሩ በዚህ ጸሑፋቸው የብርቱካን ሚደቅሳን እስር ከፈላስፋው ሶቅራጠስ እና የማርቲን ሉተር ኪንግ እስር ጋር በማስተያየት ስለሕግ ያላቸው ፍልስፍና፣ የሕግ ፍልስፍናቸው የቆመበትን የሞራል መሠረት እና በተሰሙባቸው ክሶች እና በአናዊ ክሶች መንሥኤ መካከል ያለውን ግጭት አሳይተዋል።ስደትና ዝምታብርቱካን ከዳግም እስሯ እንደተለቀቀች ስትሸሸው የነበረውን ከሀገር መውጣት ተቀብላ ለጊዜው ገሸሽ ማለትን መርጣለች። ብርቱካን ከእስር ተፈትታ ወደ አሜሪካ ከሄደች በኋላ ከፖለቲካ መድረክ ሙሉ በሙሉ ራሷን አግልላ ቆይታለች። በፖርቲ ፖለቲካም ሆነ፣ በሰብአዊ መብት ጥያቄ ከመሳተፍ፣ ከመናገርና ከመፃፍም መቆጠቡን መርጣ ኖራለች። የሰፈሯ ልጅ የሆነውና ከፖለቲካ ጅማሮዋ አንስቶ የሚያውቃት ነብዩ ግን ይሄ ውሳኔዋ እንዳላስገረመው ይናገራል፤“ከእስር ቤት ስትወጣ የተወሰነ ሰዓት ተኝታ ስትነሳ ዓይኗ ደም ሞልቶ ጥቁሩ ብቻ ነበር የሚታየው” ብሎ በሁለተኛው እስሯ ስላሳለፈችው መከራ በማንሳት “ብዙዎች ለምን ዝም አለች ብለው ሲጠይቁ ሰማለሁ። አሜሪካ ከሄደች በኋላ ዝም ማለቷ አልደነቀንም። እረፍት ማድረጓ፣ ከዚያ ትውስታ መውጣቷ፣ መማሯ በጣም ደስ ብሎኛል።”በስደት የቆየችባቸውን ጊዜያት የቅርብ ጓደኛዋ ዐቢይ ተክለማርያም በሦስት ከፍሎ ይመለከተዋል። ብርቱካን አሜሪካን ሀገር እንደሄደች በአጋርነት(fellowship) መሥራት የጀመረችው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታን ለመደገፍ በተቋቋመውኔድ( National Endowment for Democracy) በተሰኘው ድርጅት ነው። በዚያ ቆይታዋ በኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርዎችን እንዲዳከሙ ያደረጋቸውን ምክንያቶችና እነርሱን ለማጠናከር ምን ማድረግ እንደሚገባ ስታጠና ቆይታለች። ጎን ለጎንም ስለ አደባባይ ህይወቷ፣ ስለዳግም እስራቷ እና የአፈታቷ ሂደት በማሰላሰል ታሳልፍ ነበር።ሁለተኛው ምዕራፍ ዕውቀትን ከመገብየት ጋር የተያያዘ ነበር። ብርቱካን ከአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛ ከወጣች በኋላ በስራዋ እና በሌሎች እንቅስቃሴዎች በመጠመዷ በመደበኛነት የምትማርበት ዕድል አላገኘችም ነበር። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የመማር ፍላጎት ይታይባት እንደነበር ዐቢይ ይናገራል። ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋምአሜሪካን ሀገር ቦስተን ቤተሰባቸውን ለመጠየቅ ሲሄዱብርቱካንበሃርቫርድ የኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደር ትምህርት በመከታተል ላይ እንደነበረችና ለመማር እና ለማወቅ የነበራትን ጥረት እንደተመለከቱ ይገልጻሉ። “ራሳቸውን እያበቁ ነው (ሃርቫርድ ዩንቨርሲቲ እየተማሩ ስለነበር) በብዙ መልኩ ራሳቸውን እያሳደጉ ነው። ገና ወጣት በመሆናቸው ወደፊት ጠንክረው ብቁሆነው መመለሳቸው አይቀርም ብዬ ነበር” በማለት የተነበዩት እንደሰመረላቸው ይናገራሉ።ከማሰላሰልና ከትምህርት ቤት በኋላ ያሉት የብርቱካን ዓመታት በኢትዮጵያ ከነበረው ሕዝባዊ አመጽ ጋር ገጥሟል። የስርዓት ለውጥ እንደሚኖር የገመቱ የድል አጥቢያ አርበኞች ዕድሉን ለመጠቀም ያሰፈሰፉበት ጊዜ ነበር። ብርቱካን ግን ትልቅ ዋጋ ከፍላ እያለ ከእንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎችንበርቀትስታይ ነበር የቆየችው።  በወቅቱ ብርቱካን ከተለያዩ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ጋር ከሚሰሩ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ አክቲቪስቶች ጋር መተዋወቅ፤ ሀገሪቱ ላይ ያለውን ነባራዊ ኹኔታ መረዳት፤ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ትስስር መፍጠር እና በእስር ምክንያት ከተፈጠረው መነጠል በመውጣት ወዳጅነትን መፍጠር የመሳሰሉትን ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ታከናውን ነበር።[caption id="attachment_1540" align="alignnone" width="632"] Harvard Scholar at Risk and twice-imprisoned Ethiopian judge Birtukan Midekssa prepares to speak in the Thompson Room at Harvard University. Kris Snibbe/Harvard Staff Photographer[/caption]የጠፋብችብን መንፈስአዲሱ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀመሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመሄዳቸው በፊት ከብርቱካን ጋር ግንኙነቶች እንደነበሩት ለማወቅ ተችሏል። በኋላም ዶ/ር ዐቢይ ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅትከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳንአግኘተው እንደተወያዩ በወቅቱ ተዘግቧል። ከምርጫ ቦርድ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ሹመት ልታገኝ እንደሆነ በርካታ መላ-ምቶች ይሰማሉ። የአዲስ ዘይቤ ምንጮችእንዳረጋገጡልንመንግሥት የፍትሕ ስርዓትን ማሻሻል፣ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ እና በምርጫ ዙሪያ የብርቱካንን ድጋፍ እንደሚሻ ገልፆላታል። በማኀበራዊ ሚዲያ ደግሞ ብርቱካን የምርጫ ቦርድን በበላይነት ይዛ ሀገሪቱን ለምርጫ እንደምታዘጋጃት እየተገመተ ነው። አዲስ ዘይቤ ይሄንን ጉዳይ ከራሷ ለማረጋገጥ ብርቱካንን ጠይቋት ነበር። ብርቱካን ለጊዜው ለጥያቄው አዎንታዊም አሉታዊም መልስ እንደሌላት ገልፃለች። (በተለይ ለአዲስ ዘይቤ የሰጠችውን ቃለ-መጠይቁን በገፅ 5 ይመልከቱ)ዐቢይ ተክለ ማርያም ብርቱካን ያላት ሰፊ ልምድ፣ የትምህርት እና የስነ ልቦና ዝግጅት፣ ነገሮችን በሳይንሳዊ መንገድ የመተንተን ብቃት እና በሂደት ያዳበረችው ገለልተኝነት (impartiality) ከላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነቶች ለመሸከም ብቁ እንደሚያደርጋት ጠቅሶ ነገር ግንየዲሞከራሲ ነጻነትን (democratic liberalization) ከዴሞክራሲያዊ ሽግግር (democratic transition) ጋር የማቀላቀል ብዥታ ሥራዎችን ከባድ እንደሚያደርጋቸውስጋቱን ይገልጻል። ይሁንና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብርቱካንን ማሳተፍ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ያምናል። የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አባል፣ በአሁን ሰዓት ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል የሆነው ዳንኤል ሺበሺ ደግሞ ብርቱካን የየትኛውም የኢህአዴግ መንግሥት ሹመትን መቀበል አግባብነቱ አይታየውም። “ከዚያ ይልቅ በሀገሪቱ በሚደረገው ለውጥ ውስጥ የማማከር እና በቅርብ ርቀት ሆኖ የማገዝ ድርሻ ቢኖራት ጥሩ ነው::”በማለት ይመክራል።ዶ/ር ዳኛቸው በወ/ሪት ብርቲካን ወደ ሀገር ቤት መመለስ በጣም ደስተኛ ናቸው። “ብርቱካን መንፈስ ናት።የወ/ሪት ብርቱካን ኢትዮጵያ ውስጥ መመለስ አስፈላጊ የሆነ መንፈስ መሃላችን መገኘት ወይም ትልቅ ክፍተት መሙላት ማለት ነው።ጥሪውን ያደረጉላቸው ዶ/ር ዐቢይ እንደሆኑ ሰምቻለሁ። ለዚህም ጠ/ሚሩን ማመስገን ይገባል። በቀጣይም እነ ፕ/ሮ ጌታቸው[ኃይሌ] የመሳሰሉት እንዲመጡ እና ለሃገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንጠብቃለን” በማለት ተስፋቸውን ይገልጻሉ።የብርቱካን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስንና፣በምርጫ ቦርድ ሊቀ-መንበርነት ወይም ሌሎች ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት ልታገለግል እንደምትችል በማሕበራዊ ሚዲያዎች ስታነብ ዝብርቅርቅ ስሜት እንደፈጠረባት የማትሸሽገው ርዕዮት በአንድ በኩል እንደ ብርቱካን ዓይነት ለፍትህ የቆመ ሰው ለኃላፊነት መመደቡና ብርቱካንም ሳትፈልግ ከተሰደደችበት ተመልሳ ለሀገሯ መሥራት መቻሏ ጥሩ ስሜት እንሚፈጥርባት ገልፃ “በሌላ በኩል የብርቱካን መመለስ የዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግ በፍጥነት እየተጓዘበት ያለው የገጽታ ግንባታ አንዱ አካል ይሆን? የሚል ጥያቄ ይመጣብኝና መጥፎ ጠርጣሬ ውስጥ እገባለሁ። ብርቱካን ኢህአዴግ የጀመረው መጥፎ ስሙን የማደስ ብልጣብልጥ አካሄድ ሰለባ ስትሆን የታየኝና እቆዝማለሁ።” ብላ ተስፋና ጥርጣሬዋን ትገልፃለች።ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች ስለብርቱካንን የጤንነት ሁኔታ ተጠይቀው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በስላቅ “ለመጨረሻ ግዜ እንደሰማሁት ከሆነ በፍፁም ጤንነት ላይ ነው የምትገኘው። ክብደቷ ትንሽ ሳይጨምር አይቀርም፤ እንደሚመስለኝ ከሆነ ያ የሆነው የሰውነት እንቅስቃሴ ባለማድረጓ ነው። ከዚያ በስተቀር በጥሩ ጤንነት ላይ ነው የምትገኘው።…ብርቱካን ተራ የሕግ እስረኛ ነች። እንደ ተራ የሕግ እስረኛ ነው የምትታየው። በአሜሪካ ያሉና ሌሎች የሚፈልጉት በተለየ ሁኔታ እንድትታይ ነው። በተለየ ሁኔታ እንድትታይ የሚፈልጉት ደግሞ “ጠንካራ የውጭ ሀገር ወዳጆች ያሏቸው በኢትዮጵያ ከሕግ ተጠያቂነት የወጡ ናቸው” የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ስለሚፈልጉ ነው። ይሄ የተሳሳተ እንደሆነ ለማሳየት እስከመጨረሻው በእስር እናቆያታለን” ብለው ነበር።የፈረንሳይ ለጋሲዮኑ ነብዩ ብርቱካን ካወራችኝ ሁሉ በትካዜ ተውጣ “እንደ ዕድል ሆኖ ማንዴላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባይፈጠር፣ ጋንዲ ሕንድ ውስጥ ባይመጣ… እያለች አሁን የማላስታውሳቸው ሌሎችም ታላላቅ መሪዎችን ጠቅሳ ‘የኢትዮጵያንም የፖለቲካ ሁኔታ ለማስተካከል እንደዛ ዓይነት ሰው ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ እንደዛ ዓይነት ቀና የሚያስብ፣ ቀና የሚሰራ መሪ እንድታገኝ ዕድል ያስፈለጋታል፤ አለበለዚያ የኢትዮጵያ ሁኔታ አይስተካከልም’ ያለችኝን አልረሳውም፣ ብዙ ግዜም አስታውሰዋለሁ” ይላል።በብርቱካን መምጫ ዋዜማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚገኘውና ብርቱካን ተወልዳ ያደገችበት ቤታቸው ተገኝተን ነበር። የተወሰኑ የቤተሰቡ አባላትና ጎረቤቶች ተቀምጠው ቡና ተፈልቶ እየተጠጣ ነበር። እኛም ቡና ተቀድቶልን ጠጣን። የብርቱካንን እናት ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሕርን ብርቱካንን ጨምሮ የሰፈሩ ሰው ሁሉ አንቺዬ እያለ ነው የሚጠራቸው። በዋዜማው ወገባቸውን አሟቸው መኝታ ቤት ውስጥ የተኙ ቢሆንም ገብተን ሰላም ስንላቸው ሕመማቸውን ቻል አድርገው በደስታ እየተፍነከነኩ ያወራሉ። በጣም ተጫዋች ናቸው። ሳሎኑ ውስጥ ብርቱካን ሁለት እጆቿን ደረቷ ላይ አጣምራ ሕዝብን በትህትና እያመሰገነች ያለችበት ትልቅ ፎቶ ተሰቅሏል። አንቺዬ መኝታ ቤትም ሆነው አልፎ አልፎ በወሬ ይሳተፋሉ።ብርቱካን ከትላንት ወዲያ፣ ሐሙስ ጠዋት ጥቅምት 27 ከስምንት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ስትገባ ግን የብርቱካን እናት ከአልጋቸው ተነስተው፣ የጥበብ ልብስ ለብሰው፣ ነጭ ነጠላ ሻሽ አድርገው እየተፍነከነኩ ነበር። እሷ ዕረፍት ለማደረግ ገብታ ስትትኛ እንኳን እሳቸው ከሰፈርተኛውና ከሌሎች እንግዶች ጋር ሆነው ለረጅም ሰዓታት በረንዳው ላይ ተቀምጠው እየተጫወቱ ነበር። ብርቱካን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ፈረንሳይ ስትደርስ የሰፈሩ ነዋሪዎች ግልብጥ ብለው ወጥተው፤ ከኤምባሲው ፊት ለፊት ካሉት ቀጫጭን የ”ኮብል ስቶን” መንገዶች ወደነብርቱካን ቤት በሚወስደው መንገድ ላይ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው አበባ እየበተኑ፣ ግማሾቹ እየጮሁ፣ ግማሾቹ እያለቀሱ፣ እየሳሟት፣ እየጨበጧት፣ እናቶቹ ደግሞ በእልልታ ነበር የተቀበሏት። ተወልዳ ወዳደገችበት መኖሪያ ግቢያቸው በሕዝቡ ታጅባ ከደረሰች በኋላ ሊቀበሏት ለተገኙትና መምጣቷን ለሚከታተሉት ሁሉ አጭር ንግግር አድርጋለች። በንግግሯም ሕዝቡን ስታመሰግን፣ የፈረንሳይ ልጆችን አወድሳለች። እሷን ሳያቋርጡ የሚያወድሷት ደግሞ በመላው ኢትዮጵያና፣ ከመላው ዓለም የ“እንኳን ለሀገርሽ አበቃሽ” መልዕክቶቻቸውን በማሕበራዊ ሚዲያዎች አጉርፈውታል።ስለመመለሷ አንድምታ ጥርጣሬ እንዳላት ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀችው ርዕዮት ዓለሙ “እግዚአብሔር የኔን ስጋትና ጥርጣሬ ዕውን እንዳይሆን አድርጎ ለሷም ሆነ ለሀገሬ መልካሙን ሁሉ እንዲያመጣ እመኛለሁ” ብላለች። የረጅም ጊዜ የብርቱካን ወዳጅዐቢይ ተ/ማርያምም ብርቱካን በተመለሰችበት ዕለት በትዊተር ገፁ ፅሁፍ አስፍሯል።በ2001፣ ታህሳስ ወር “ቃሌ” በሚል ርዕስ በፃፈችው ፅሁፍ የገለፀችው ሽምግልናውን በተመለከተ ለፖሊሶች የሕግ ጥያቄ አንስታ ሲያጣጥሉባት“ለእነርሱ ያስገረማቸው ጉዳይ እኔ ሁሌም የምኖርለት፣ የምቆምለት፣ አንዳንዴም የምታሰርለት እና የምፈታለት ታላቅ ቁምነገር ነው። የሕግ የበላይነት ወይም ሕገ-መንግስታዊነት።” ይሄንን ከፃፈች አስር ዓመት ሊሞላው ነው። ብርቱካን ሚደቅሳ ደሜ ግን ቃሏን አጥፋ አታውቅም።

አስተያየት