ኅዳር 5 ፣ 2011

የታክሲ አገልግሎትና ዝመናው ሰሞነኛ ተግዳሮቶች

ወቅታዊ ጉዳዮች

በፈረንጆቹ ታህሳስ 2008 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ በበረዶማው ፈረንሳይ ፓሪስ ጋሬት ካምፕና ጓደኞቹ መኪና ከአሽከርካሪው ጋር ተከራዩ፡፡ ለአገልግሎቱም…

የታክሲ አገልግሎትና ዝመናው ሰሞነኛ ተግዳሮቶች
በፈረንጆቹ ታህሳስ 2008 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ በበረዶማው ፈረንሳይ ፓሪስ ጋሬት ካምፕና ጓደኞቹ መኪና ከአሽከርካሪው ጋር ተከራዩ፡፡ ለአገልግሎቱም 800 ዶላር ከፈሉ፡፡ ካምፕ በወቅቱ ይሄን በዛ ያለ ወጪ እንዴት መቀነስ ይቻላል በሚል ሲያብሰለስለው የቆየ ሃሳብ ግዙፉን የታክሲ ቴክኖሎጂ አብዮት ያመጣውን ኡበር የተባለውን ኩባንያ ፈጠረ ፡፡ኡበር የተለመደውን መንገድ ጠርዝ ላይ ቆሞ “ታክሲ፣ ታክሲ” እያሉ በመጮህ ታክሲ የማስቆምን ልማድ  ቀይሮ ሰዎቹ ወደ ታክሲ በመሄድ ፋንታ ታክሲዎቹ ወደሰዎች እንዲመጡ አድርጓል። ኩባንያው በፈጠረውና በየጊዜው በሚያሻሽለው መተግበሪያው(Application) ሂደቱን በማቀላጠፍ ሶስተኛ ወገን ሳይገባ ተሳፋሪውና አሽከርካሪው በቀጥታ እንዲገናኙ ማድርግ ችሏል። ተሳፋሪው የሚቀርበውን መኪና መምረጥ የስልክ መተግበሪያው ላይ በጣቱ መጨቆን ብቻ በቂው ነው። የመረጠው ታክሲ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አጠገቡ እንዲቆም ያደርጋል። አሽከርካሪውም በመረጠው ሰዓት እንዲሰራ የሚፈልገውንና የመረጠውን  የደንበኛ ጥሪ እንዲቀበል ነጻነቱ ተመቻችቶለታል።ኡበር ልክ እንደፌስቡክ፣ ትዊተር፣ አማዞን እና ቢኤንቢ ዓለምን ከቀየሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዱ ነው።ከታክሲ እጦት አጋጣሚ የተወለደው ኡበር ዛሬ ከ60 ሃገራት በላይ  የሚንቀሳቀስ በ68 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ ያለው ኩባንያ ነው። ኡበር ኢትዮጵያ ባይደርስም በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ገበያውን አስፋፍቷል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከኡበር የተቀዳ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ እንደራይድ ያሉ  ኩባንያዎች በመዲናችን ብቅ ብቅ ካሉ ሰንበትበት ብሏል።የሸገር ታክሲዎችና የቴክኖሎጂ በፈረንጆቹ 1930ዎቹ መጀመሪያ ፕሊመዝ(Plymouth)  በተባሉ አሜሪካ ሰራሽ አዉቶሞቢሎች በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር The plot to kill Graziani በተባለ መጽሃፍ ላይ ተጠቅሷል። በወቅቱ ታክሲዎቹ ከአንድ እስከ አምስት ማር ትሬዛ በማስከፈል ከለገሃር ባቡር ጣቢያ እስከ አራዳ ጊዮርጊስ፤ ቤተመንግስትና ጣይቱ ሆቴል ድረስ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። በዚህ መልኩ የተጀመረው የታክሲ አገልግሎት ፊያትና ፔጆ ተሽከርካሪዎችን አስከትሎ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከሩስያ የመጡትን ላዳ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች ይዞ በመጓዝ ዛሬ እንደ አቫንዛ ያሉ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ላይ ደርሷል። ሲጀመር በሁለትና ሶሰት መስመር የተገደበ የነበረው የታክሲ መስመር ዛሬ በእጅ ስልክ  መተግበሪያ እየተመራ ሰዎች ማንኛዉም ቦታ በማንኛዉም ሰዓት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የታክሲ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል። አገልግሎቱ ይህን ያህል ቢዘምንም በመዲናችን ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ማየት እንግዳ ነገር እይደለም።በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የትራንስፖርት እገልግሎትን በመምራት በሃገራችን ቀዳሚ የሆነው ሃይብሪድ ዲዛይን የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ስር የተቋቋመው ራይድ የታክሲ አገልግሎት ነው።ድርጅቱ ከዘጠኝ መቶ በላይ መኪኖችን በመመዝገብ ጥራታቸውን በማረጋገጥ ለተሽከርካሪዎች የአሽከርካሪነት የዲስፕሊን ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዳሰማራ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ግርማ አስማረ በራይድ የታክሲ ሥምሪት አገልግሎት ከተሰማሩና ተጠቃሚ ከሆኑ አሽከርካሪዎች አንዱ ነው። ግርማ ከራይድ ጋር መስራት ከጀመረ በኋላ ገቢው በጥሩ ሁኔታ እንዳደገና አገልግለቱ ለእሱና መሰሎቹ ጥሩ የስራ እድል እንደፈጠረ ይናገራል። በግሉ ካገኘው ጥቅም በተጨማሪ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ  ከተማዋ ጥራት ያለው ራይድን የመሰለ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘቷ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል።ግርማ ደንበኞቹን በተመለከተ አብዛኛዎቹ ከሱ ጋር የሚጓዙ ደንበኞች በአገልግሎቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን እንደሚገልጹለት ይናገራል። የራይድ ተጠቃሚ የሆነው ሳምሶን ወልዳይ የግርማን ሃሳብ ይጋራል። “መኪኖቹ ዘመናዊና ምቹ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በዋጋ በኩልም የተሻሉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም አሰራሩ ዘመናዊና ግልጽነት ያለው በመሆኑ   አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከላዳ ታክሲዎች ጋር ሲገጥመኝ ከነበረው የዋጋ ጭቅጭቅ ገላግሎኛል” ይላል። ተጠቃሚዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ይህን ቢሉም የመንግሥት አካላት በዚህ ደስተኛ የሆኑ አይመስሉም። የትራንስፖርት ጭንቅና የመንግስት ግትርነት በቴክኖሎጂ በታገዘ የታክሲ አገልግሎት ስምሪት ከተሳተፉት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ሃይብሪድ ዲዛይን  ጥቅምት 23፣ 2011 ዓ.ም. በሼራተን አዲስ በሰጠው መግለጫ ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ የመኪና ኪራይ አገልግሎት ለመስጠት ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው ኮድ 3 ተሽከርካሪዎች ስራቸውን እንዳይሰሩ ከመንግስት አካላት ጫናና ወከባ እየደረሰባቸው እንደሆነ አቤቱታውን አቅርቧል።የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን በበኩሉ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ በሦስት ቁጥር  የተሽከርካሪ መለያ ኮድ የታክሲ አገልግሎት መስጠት እንደማይቻል የሚሰራ ካለም ህገ ወጥ እንደሆነ ገልጿል። ሃይብሪድ ዲዛይንን የመሳሰሉ ኩባንያውዎች የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ናቸው እንጂ የታክሲ ስምሪት የመስራት ፈቃድ የላቸውም ብሏል ።ይህን የመንግስትን መግለጫና አካሄድ በተመለከተ የራይድ አሽክርካሪው ግርማ መንግስት ከስምሪት ጋር አያይዞ የሚያነሳው ነገር ከራይድ ስራጋ ፈጽሞ እንደማይገናኝ ይናገራል። እኛ የምንሰራው ልክ እንደኪራይ መኪና ነው። በኮድ 3 መኪና ማከራየት መንግስት ይፈቅዳል። ራይድ ያመቻቸልኝ ከደንበኞች ጋር በቀላሉ እንድገናኝ ረዳኝ እንጂ የምሰራው የኮንትራት  ስራ ነው።” ሲል ይከራከራል።ግርማ መንግስት የከተማዋ የትራንስፖርት ችግር ከአቅም በላይ ሆኖበት ጭንቅ ውስጥ ባለበት ሰዓት ይህን ችግር ለመፍታት አጋዥ የሆነ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ይዞ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን ከማበረታት ይልቅ ወደ ክልከላና ጫና ውስጥ መግባቱ እንደሚያሳዝነው ይናገራል።በተለይም ደግሞ ሴቶች ወደ አመራርና ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲመጡ በሚያበረታታበት በአሁን ጊዜ ሴት ስራ ፈጣሪን መደገፍ ይገባ ነበር  ሲል ያክላል ። መንግስት የሚያነሳውን በኮድ አንድ ታክሲዎች ስራ ማጣት በተመለከተም ሊደረግ የሚገባው የአሽከርካሪዎች የአነስተኛ ወለድ ብድርና የቀረጥ ነጻ እድል በማመቻቸት ወደ ዘመናዊው አሰራር እንዲገቡ ማድረግ እንጂ ተጠቃሚዎች የሚመርጡትን ዘመናዊ አሰራር ወደኋላ በመመለስና በማገድ መሆን የለበትም ይላል።እንደራይድ ሁሉ ኡበር የተባለው ካምፓኒ ኬንያ ሲደርስ የታክሲ ማህበራት ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በኬንያ በመንግሥት በኩል ኡበርን የማውቀው እንደ አንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ስለሆነ በነጻ የገበያ ውድድር ውስጥ ጣልቃ አልገባም ሲል የታክሲ ማህበራቱን አቤቱታ ችላ ብሎት አልፏል።ሳምሶን ሁልጊዜም ህግና ቴክኖሎጂ አብረው መጓዝ ካልቻሉ ህጉን ማሻሻል እንጂ ቴክኖሎጂን ማገድ እንደማይችል በአለም ላይ ያለው የሃገራት ልምድ እንደሚያሳይ ይናገራል። ይህን በተመለከተ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው መንግስቱ በስር አስተያየትም ይህን ያጠናክራል። ባለሙያው የመንግስት የቁጥጥር ተቋማት አዳዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ የመቆጣጠር በቂ እውቀት ስለማይኖራቸው እውቀቱ እስከሚኖራቸው ድረስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማገድ ይልቅ እነሱ የመቆጣጠሩን አቅም እስከሚያዳብሩ ድረስ ቴክኖሎጂውን ቀስ በቀስ በመፍቀድ ነገር ግን ጎን ለጎን አስፈላጊውን የህግና ሌሎች የቁጥጥር ዘዴዎችን ማጠናከር አለም በአሁኑ ወቅት በሰፊው እየተከተለው ያለ አካሄድ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም አካሄድ በምጣኔ ሃብት ጥናት ይህ የሚሞከርበት ደንባዊ የትዝብት እና የክትትል ጊዜ (Regulatory sand box) በመባል ይታወቃል። “ብዙ ጊዜ ተቆጣጣሪ የመንግስት አካላት ይህን መንገድ መምረጥ የሚያዋጣቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መቼና እንዴት እንደሚመጡ ስለማይታወቅ መንግስት አስቀድሞ የህግ ማዕቀፍ ሊያወጣላቸው ስለማይችል ነው።” በማለት አቶ መንግሥቱ ያስረዳሉ።የታክሲ ምጣኔ ሀብትና የተገልጋይ ህዝብ ብዛትየአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ተግባራትና ኃላፊነት ተብለው ከተጠቀሱት አንዱ ‘የተቀናጀ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት ሥርዓት ያደራጃል፣ እንዲስፋፋም ያደርጋል። የሚል ዝርዝር ኃላፊነት ይገኝበታል። ቢሮው እንዲስፋፋ ያደርጋል ሲባል በዋነኛነት የግል ሴክተሩን ተጠቅሞ እንደሆነ ግልጽ ነው። ብዙዎች እንደሚስማሙት ከአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር እድገት ጋር አብሮ የሚሄድ የታክሲ አገልግሎት ማቅረብ አዳጋች እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። የትራንስፖርት እጥረቱ በመባባሱ በማለዳ ወደ ስራ በምሽት ወደቤት መግባት እጅግ አዳጋች እንደሆነባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በምሬት ሲናገሩ ማየት የተለመደ ሆኗል።ይህን የመንግሥትና የአገልግሎት ሰጪዎችን እሰጥ አገባ በተመለከተ  የኢኮኖሚክስ ባለሙያው መንግስቱ በስር ራይድን የመሳሰሉ ዘመናዊ የታክሲ አገልግሎት ከኢኮኖሚ አንጻር ጠቀሜታን ከሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አንጻር ያዩታል። የመጀመሪያው የሸማቾች ያልተገባ ኪሳራ (consumer loss)ን ከምጣኔ ሃብት ኃልዮት በመጥቀስ ያስረዳሉ። ይህም ተጠቃሚዎች ለሚያገኙት ተመሳሳይ አገልግሎት የሚያወጡት ተጨማሪ ወጪ ወይም ብክነት ማለት ነው። በዚህ መሰረትም ባለሙያው “ባለኝ መረጃ ተጠቃሚዎች ለታክሲ አገልግሎት የሚከፍሉት ክፍያ በራይድ ሲሆን ከቀድሞዎቹ ታክሲዎች በጣም ያነሰ ነው። ይህም ዜጎች ለተመሳሳይ አገልግሎት ከፍ ያለ ክፍያ ይከፍሉ እንደነበር ያሳያል። እሱም የሸማቾች ያልተገባ ኪሳራ ነው ይላሉ። እንደራይድ ያሉ አገልግሎቶች መኖር ይህን መሰሉን ብክነት ያስቀራል በማለት ይከራከራሉ።ሌላው ከትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት አንጻር ነው። ይሄውም አሁን ካሉት መሰረታዊ ችግሮች አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ራይድ ያሉ አገልግሎቶች አጠቃላይ አቅርቦትን(supply) ከማሳደግ አንጻር መጠነኛም ቢሆን አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። እነዚህን አገልግሎት ሰጪዎች ማገድ አጠቃላይ አቅርቦቱን ማሳነስና ችግሩን ከማባባስ ውጪ ጥቅም እንደማይኖረው ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከምርታማነት አንጻር የቤት መኪናዎቻቸውን ለታክሲ አገልግሎት የሚያውሉ አሽክርካሪዎች ተጨማሪ ስዓት እንዲሰሩ ጊዜያቸውን በስራ እንዲያሳልፉና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እድሉን ማግኘታቸው ለሀገር ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው በጎ አስተዋጽኦ አንጻር የሚበረታታ እንደሆነ ይናገራል። መንግስትም ራይድን በመሰሉ አገልግሎት ሰጪዎች ካልታገዘ የከተማዋን  የትራንስፖርት እጥረት ችግር ብቻውን መፍታት እንደሚከብደው አስተያየት ሰጪዎች ያሰምሩበታል። በአጠቃላይ ለለውጥ ዝግጁ ያለመሆን በሰፊው ይስተዋላል። ይህ ግን ዛሬ የጀመረ ግትርነት አይመስልም። “ሁሉን ነገር የኔ አገር ሰው ቢያውቅልኝ ደስ ይለኝ ነበር። … ግን በጄም አይሉም።”                                                                      ዳግማዊ ምኒሊክበ1900 አጼ ምኒሊክ በንትሌይ የተሰኘችውን የመጀመሪያ አውቶቢል ከእንግሊዝ አገር ሲያስመጡ በወቅቱ መኳንንቱና ህዝቡ መኪናዋን መጠጋት ቢፈሩም ንጉሱ ግን መኪናዋ ላይ ለመውጣት ብዙም አላመነቱም፡፡ መኪናዋን ተሳፍረውም መኪናዋን ሲያሽከረክር ለነበረው ዌልስ የተባለው እንግሊዛዊ “ከፈረስ ትቀድም እንደሁ አፍጥነህ አሳየኝ ይሉት ነበር፡፡ ምኒሊክ የህዝቡን ሁኔታ ካዩ በኋላ “ሁሉን ነገር የኔ አገር ሰው ቢያውቅልኝ ደስ ይለኝ ነበር። ግን አይሆንላቸውም። በጄም አይሉም።” በማለት የኢትዮጵያውያንን አዲስ ነገር ቶሎ ያለመላመድ ባህል ታዝበው መናገራቸውን ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒሊክ በተባለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል።የራይድ አሽከርካሪው ግርማም ሆነ የራይድ ተጠቃሚው ሳምሶን ኢትዮጵያዊያን አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ቶሎ ያለመቀበል ባህል ችግር እንዳለብን ያምናሉ። አዲስ ቴክኖሎጂን ካለው ሁኔታ ጋር አስመምተን ችግራችንን መፍታት ላይ ይቀረናል ይላሉ። እናም ኢትዮጵያዊያን የኖረው አዲስ ነገር የመቀበል ባህላችን እየጎተተን ይሆን? የአጼ ሚኒሊክ መኳንንት መኪና መጠጋት እንደፈሩት የዘመኑ ባለስልጣናት ቴክኖሎጂን እየፈሩ ይሆን?የኤዲተር ማስታወሻ፡ አዲስ ዘይቤ ለዚህ ጽሁፍ ዝግጅት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መካከል በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬትን እና የራይድ ሥራ አስፈጻሚን ለማነጋገር በአካልና በስልክ ያደረገችው ተደጋጋሚ  ሙከራ አልተሳካም። ፈቃደኛ በሆኑ ጊዜ ግን አስተያየታቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ ነች ።

አስተያየት